አርባምንጭ ከተማ በአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ ላይ ለውጦች አድርጓል

የአርባምንጭ ከተማ ቦርድ ባደረገው ስብሰባ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት የስንብት እና የሹመት ውሳኔዎችን አሳልፏል።

በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ላይ በድጋሚ አድገው እየተሳተፉ ካሉ ክለቦች መካከል አንዱ አርባምንጭ ከተማ ነው። 2011 ክረምት ወር ላይ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን በመቅጠር የከፍተኛ ሊግ ተሳትፎውን ከሊጉ ከወረደ በኋላ የቀጠለው ክለቡ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ድጋሚ ወደ ሀገሪቱ ትልቁ የሊግ ዕርከን አድጎ እየተሳተፈ ተከታታይ ሁለተኛ ዓመቱን ይዟል።

\"\"

በሊጉ ካደረጋቸው አስራ ሦስት ጨዋታዎች አራቱን ተሸንፎ ሰባት አቻ ወጥቶ በሁለቱ ድል ቀንቶት በደረጃ ሰንጠረዡ 13ኛ ላይ የተቀመጠው አርባምንጭ ከተማ ውጤቱን አስመልክቶ ስብሰባ ተቀምጦ ነበር። የክለቡ ቦርድ አባላት ባደረጉት በዚህ ሰሞነኛ ስብሰባ ክለቡ እያስመዘገበ ካለው ደካማ ውጤት መነሻነት ለዋና አሰልጣኙ መሳይ ተፈሪ የሁለት ጨዋታ ዕድል እንዲሰጥ ሲወሰን ቡድን መሪውን ጨምሮ ሦስት ረዳት አሰልጣኞች ከኃላፊነት መነሳታቸውን እና በቦታውም አዳዲሶች ስለመተካታቸው ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ በላከው መረጃ አመላክቷል።

በዚህም መሰረት ቡድን መሪው መንግሥቱ ደምሴ ፣ ሁለቱ ረዳት አሰልጣኞች ማቲዮስ ለማ እና አበው ታምሩ እንዲሁም የግብ ጠባቂ አሰልጣኙ ስለሺ ሽፈራው እንዲሰናበቱ ተወስኗል።

\"\"

በምትካቸው ደግሞ የቀድሞው የክለቡ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች እና የቡድኑ ከ20 ዓመት በታች አሰልጣኝ የነበረውን በረከት ደሙን እና የቀድሞው የአርባምንጭ ጨርቃጨርቅ ተጫዋች እና ከ15 ዓመት በታች አሰልጣኝ ሆኖ ሲሰራ የቆየውን ገረመው ተበጀን በረዳት አሰልጣኝነት ሾመዋል። የቀድሞው የክለቡ ግብ ጠባቂ እና የሴት ቡድኑ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ሆኖ ሲያገለግል ለቆየው አንተነህ መሳ ደግሞ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝነት ኃላፊነትን መስጠቱን ክለቡ አሳውቋል።