ቻን | የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቻን አንዳንድ እውነታዎች

👉 በውድድሩ የኢትዮጵያ ብቸኛ ግብ
👉 ኢትዮጵያ ላይ የተቆጠሩ ጎሎች ብዛት
👉 የውድድሩ ብቸኛ አንድ ነጥብ እና ሌሎች

የሀገር ውስጥ ሊግ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት አፍሪካ ሀገራት ቻምፒየንሺፕ ሊጀመር የቀናት ዕድሜ ብቻ ቀርተውታል። በአልጀርያ አዘጋጅነት የሚካሄደው ይህ ውድድር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሦስተኛው ተሳትፎ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የውድድሩ አንዳንድ ቁጥሮችን እንደሚከተለው አቅርበናል።

– በውድድሩ የተመዘገበችው ብቸኛ አንድ ነጥብ

በ2014 በደቡብ አፍሪካ በ2016 ደግሞ በጎረቤት ሀገር ሩዋንዳ በተካሄዱ ውድድሮች የተሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሁለቱም ውድድሮች ደካማ ውጤት አስመዝግቧል። በአጠቃላይ በውድድሩ ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች አምስት ሽንፈቶች ሲያስተናግድ በአንድ ጨዋታ ባዶ ለባዶ አቻ ተለያይቷል። ሩዋንዳ ቡታሪ ከተማ ላይ ከካሜሩን ብሄራዊ ቡድን በነበረው ጨዋታ ያሳካው አንድ ነጥብም የውድድሩ ትልቁ ውጤቱ ነው።

\"\"

– የብቸኛዋ ግብ ባለቤት ስዩም ተስፋዬ

ኢትዮጵያ በውድድሩ ታሪክ አንድ ግብ ብቻ አስቆጥራለች። የግቧ ባለቤትም የቀኝ መስመር ተከላካዩ እና በሁለቱም ውድድሮች የተሳተፈው ስዩም ተስፋዬ ነው። በወቅቱ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት የነበረው ስዩም ከተጠቀሰው ግብ ውጪ በሌሎች ውድድሮች ከአጥቂዎቹ ልቆ በተከታታይ ለቡድኑ ግብ ማስቆጠሩ ይታወሳል። ግቧም በመጨረሻው የምድብ ጨዋታ ላይ በ74ኛ ደቂቃ ላይ አንጎላ ላይ የተቆጠረች ግብ ነች።

– ብሔራዊ ቡድኑ በውድድሩ ያስተናገዳቸው ግቦች ብዛት

በቻን አፍሪካ ዋንጫ ታሪኩ በሁለት ውድድሮች በድምሩ ስድስት ጨዋታዎች ያከናወነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኑ በተጠቀሱት ጨዋታዎች ዘጠኝ ግቦች ተቆጥረውበታል። ይህም በአንድ ጨዋታ በአማካይ 1.5 ግቦች ተመዝግበውበታል ማለት ነው። ቡድኑ በ2014 አራት ግቦች ስያስተናግድ በቀጣዩ የ2016 ውድድር ደግሞ አምስት ግቦች አስተናግዷል።

– በአንድ ጨዋታ ከፍተኛው የግብ መጠን

እንደ ሌሎች ካፍ የሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ብዙ ግቦች የማይቆጠርበት ውድድር ላይ ብሔራዊ ቡድናችን በአንድ ጨዋታ የተመዘገበበት ከፍተኛው የግብ መጠን ሦስት ነው። በ2016 ዴሞክራቲክ ሪፐብሊግ ኮንጎ በመጀመርያው የምድብ ጨዋታ በኢትዮጵያ ላይ ሥስት ግቦችን ያስቆጠሩበት ጨዋታ ኢትዮጵያ በሰፊ ውጤት የተሸነፈችበት ጨዋታ ነው።

– ኢትዮጵያ የምትደለደልበት ምድብ

በሁለቱም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተሳትፎዎች ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ የነበሩ ቡድኖች የውድድሩ አሸናፊ ሆነዋል።
በ2014 በዘንድሮ ውድድር በኢትዮጵያ ምድብ የምትገኘው ሊቢያ ውድድሩን ስታሸንፍ በ2016 ዴሞክራቲክ ኮንጎ ዋንጫውን አንስታለች።

\"\"

– በሁለቱም ውድድሮች ሀገራቸውን የወከሉ ተጫዋቾች

በሁለቱም ውድድሮች መሃል በሽግግር ጊዜ ላይ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ2016 በመጀመሪያው ውድድር የተሳተፉ ብዙ ተጫዋቾች ሳያካትት ነበር ወደ ስፍራው ያቀናው። ሆኖም የወቅቱን አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌን አሳምነው ለሁለተኛ ግዜ ወደ ውድድሩ ያቀኑ ተጫዋቾችም ነበሩ። ስዩም ተስፋዬ ፣ አሉላ ግርማ ፣ አስራት መገር እና በኃይሉ አሰፋ በሁለት ውድድሮች ሀገራቸውን መወከል የቻሉ ተጫዋቾች ናቸው።

– አልጄሪያ ላይ በሚደረገው ውድድር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የቻን ልምድ ያላቸው ተጨዋቾች…

አስቻለው ታመነ እና ጋቶች ፓኖም በዘንድሮው ስብስብ ውስጥ ከሚገኙ ተጫዋቾች የቻን ልምድ ያላቸው ብቸኛ ተጫዋቾች ናቸው ። ከዚህ ቀደም በ2016 ውድድር የተጫወቱ ሲሆን አስቻለው ሦስቱንም የምድብ ጨዋታ እንዲሁም ጋቶች ፓኖም ሁለት ጨዋታ አከናውነዋል።