ከፍተኛ ሊግ | የ10ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 10ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ ዘጠኝ ጨዋታዎች ተቋጭቷል።

በቶማስ ቦጋለ ፣ ጫላ አቤ እና ተመስገን ብዙዓለም

የ04:00 ጨዋታዎች

በምድብ \’ሀ\’ ባህር ዳር ላይ ጋሞ ጨንቻ ከ ወሎ ኮምቦልቻ ባደረጉት ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ቢታይም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ በኩል ግን ጨንቻዎች የተሻሉ ነበሩ። ወሎዎች ገና በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በሰለሞን ጌዲዮን ፣ ሲሣይ አቡሌ እና ሄኖክ ጥላሁን ጥሩ መከራዎችን በማድረግ በተሻለ የጨዋታ ስሜት ቢጀምሩም ቀስ በቀስ ግን ከራሳቸው የሜዳ ክልል ተደራጅተው ለመውጣት ተቸግረዋል። ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው የተመለሱት ጋሞዎችም የተሻለ የማጥቃት ቢኖራቸውም ፈታኝ ሙከራ ለማድረግ ግን ተቸግረዋል።

\"\"

ከዕረፍት መልስም የመጀመሪያው የተሻለ ሙከራ በወሎ ኮምቦልቻዎች ሲደረግ 51ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል በለጠ በግራ መስመር የተሰጠውን የቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ ሞክሮት ግብጠባቂው ንጉሤ ሙሉጌታ በጥሩ ብቃት መልሶበታል። ከዚህ ሙከራ በኋላ ግን የጨዋታው ሚዛን ወደ ጋሞ ጨንቻዎች ሲደፋ በርካታ መከራዎችን ማድረግም ችለዋል። በተለይም 70ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ፍስሐ ቶማስ የሞከረውና ተከላካዩ ሚኪያስ ዓለማየሁ የመለሰበት ኳስ እና በሁለት ደቂቃዎች ልዩነትም ከቆሙ ኳሶች በርካታ ዕድሎችን ሲፈጥር የነበረው ፊናስ ተመስገን ከቅጣት ምት ግሩም ሙከራ አድርጎ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ኳስ ይጠቀሳሉ። ሆኖም ጨዋታው ያለ ግብ ተጠናቋል።

\"\"

ጅማ ላይ ቂርቆስ ክ/ከ እና ንብን ባገናኘው ጨዋታ ቂርቆሶች ጥሩ በሚባል ደረጃ የኳስ እንቅስቃሴ ያሳዩበትን የመጀመሪያ አጋማሽ አሳልፈዋል። ከግብ ጠባቂ መሰረተው በመጫወት ከተጋጣሚያቸው ላይ ብልጫ ቢወስዱም ወደ ተቃራኒ ቡድን የግብ ክልል ደርሰው የጎል ዕድል መፍጠር ለይ ደካማ ሆነው ታይተዋል። ንቦች በተጋጣሚያቸው የኳስ ብልጫ ሲወሰድባቸው በመከላከሉ ረገድ ግን ጠንካራ ነበሩ። በኤርሚያስ ደጀኔ ፣ ፉዐድ ተማም ፣ ኪም ላም እና እዮብ ደረሰ በመልሶ ማጥቃት የጎል ሙከራዎች ሲያደርጉ በቂርቆስ ግብ ጠባቂ ቢኒያም ታደሰ ጥሩ ብቃት የተነሳ ጎል ሳያሰቆጥሩ ቀርተዋል።

ሁለተኛ አጋማሽ ብዙ ለውጦች አና አንቅስቃሴ የተመለከትንበት ነበር። ከጅምሩ ንቦች በዳግም ወንድሙ ጎል ቀዳሚ ሆነዋል። በጨዋታው ንቦች ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ 76ኛ ደቂቃ ላይ በኪያር መሐመድ ሁለተኛ ጎላቸውን አግኝተዋል። በቂርቆሰች በኩል ኳስ በመጫወት ወደ ጎል መሄድ ቢሳነቸውም በ87ኛ ደቂቃ በጥሩ የኳስ ንኪኪ በሆነልኝ ታሪኩ ወደ ጨዋታው የምትመልሳቸውን ጎል አስቆጥረዋል። በተቀሪ ደቂቃዎች ቂርቆሶች ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ በ90\’ ደቂቃ ተመልካችን ያሰደነቀ ጎል በኡሰማን መሐመድ አማካይነት ሲያስቀጥሩ በአጠቃላይ ጨዋታው ለተመልካች ማራኪ ሆኖ 2-2 ተጠናቋል።

\"\"

ሆሳዕና ላይ ደሴ እና የካ ክ/ከተማ ሲገባኙ የመጀመሪያው አጋማሽ በተሰሏች ሳይመን የሚመራው ደሴ ከተማ እና ብስራት በቀለ የሚመራው የካ ክ/ከተማ ጥሩ እና ፈጣን እንቅስቃሴ አድርገዋል። በየካ ክ/ከተማ በኩል ከብስራት በቀለ የተነሳችው ኳስ ለግብ የቀረበ ሙከራ የተደረገ ቢሆንም ሳይጠቀሙበት መቅረታቸው የሚታወስ ሲሆን በአንፃሩ ደሴ ከተማዎች የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ተጨማሪ ደቂቃ ሲቀረው በ45ኛው ደቂቃ የየካ ክ/ከተማዎች የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ማናዬ ፋንቱ በማስቆጠር ደሴ ከተማዎች እየመሩ ወደ መልበሻ ክፍል ማምራት ችለዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ የካዎች በተሻለ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ የተስተዋለ ሲሆን ደሴ ከተማዎች በአንፃሩ ያገኙትን የግብ ብልጫ ለማስጠበቅ ቀዝቀዝ ብለው ሲጫወቱ ተስተውሏል። በ68ኛው ደቂቃ በጨዋታ መካከል የደሴ ከተማዎች ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት የካ ክ/ከተማዎች ሳይጠቀሙበት ግብ ጠባቂው ሊያድነው ችሏል። በውጤቱም በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠረች ግብ ደሴ ከተማ ድል ማድረግ ችሏል።

\"\"

የ08፡00 ጨዋታዎች

ባህር ዳር ላይ በምድብ \’ሀ\’ አዲስ ከተማ ክ/ከተማ ከ ሀላባ ከተማ ሲገናኙ ብርቱ ፉክክር በታየበት እና ለተመልካች ሳቢ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጠንካራ የነበሩት ሀላባዎች 16ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በክሬ መሐመድ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ እንደነጠረ ያገኘው ፎሳ ሴዴቦ ዓየር ላይ እንዳለ በእግሩ ማስቆጠር ችሏል። በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት በርበሬዎቹ 29ኛው ደቂቃ ላይ በሰዒድ ግርማ አማካኝነት ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። ከዚህ ሙከራ በኋላ ግን አዲስ ከተማዎች ጨዋታውን እጅግ በጋለ ስሜት አስቀጥለው ተቆጣጥረውታል። 35ኛው ደቂቃ ላይም ያሬድ ዓለማየሁ የሀላባው ግብጠባቂ ስንታየሁ ታምራት በትክክል ሳያርቀው የቀረውን ኳስ አስቆጥሮት ክለቡን አቻ ማድረግ ሲችል በሁለት ደቂቃዎች ልዩነትም ራሱ ያሬድ ዓለማየሁ ሌላ ግብ አስቆጥሮ ክለቡን መሪ አድርጓል።

\"\"

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል ሀላባዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን ቢወስዱም 68ኛው ደቂቃ ላይ ዘኪ አብደላ ከረጅም ርቀት አክርሮ መትቶት የግራውን ቋሚ ታክኮ ከወጣው እና 84ኛው ደቂቃ ላይ ሰዒድ ግርማ ከቅጣት ምት ወደግብ ሞክሮት ግብጠባቂው ከመለሰበት ኳስ ውጪ የተሻለ የግብ ዕድል ለመፍጠር ተቸግረዋል። ውጤቱን ለማስጠበቅ በተረጋጋ አጨዋወት የራሳቸው የሜዳ ክፍል ላይ በቁጥር በዝተው መገኘት የፈለጉት አዲስ ከተማዎች 90ኛው ደቂቃ ላይ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገዋል። ተቀይሮ የገባው አሸናፊ በቀለ ከተጋጣሚ የሳጥን አጠገብ ግሩም ሙከራ ቢያደርግም የግቡን የግራ ቋሚ ታክኮ ወጥቶበታል። ጨዋታውም በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በምድብ ለ የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ጉለሌ ክ/ከ እና ከፋ ቡና ተገናኝተዋል። በሁለቱም ቡድኖች ደካማ እንቅስቃሴ ሲታይ ጉለሌዎች በጥቂቱ ከከፋ ቡና የተሻሉ ሆኑው ቢታዩም ምንም ዓይነት የጎል ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። ከፋ ቡናዎች በመልሶ መጠቃት ወደ ጉለሌ የጎል ክልል ሲደርሱ በ9ኛ ደቂቃ ዘነበ ከበደ በቀኝ መስመር የሞከረውን በግብ ጠባቂ ተመልሶበታል። አንዲሁም በ24ኛው ደቂቃ ለማመን በሚከብድ የጎል ሙከራ ታከለ ታንቶ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኘቶ ወደ ውጭ አውጥቷታል።

ሁለተኛ አጋማሽ ብዙም ሳቢ እንቅስቃሴ ያልታየበት ነበር። ጉለሌዎች ከማዕዘን የተሻገረች ኳስ በ46ኛ ደቂቃ ላይ በቢኞንግ ኪር በግባር በመግጨት የመጀመሪያ ሙከራ ሲያደርጉ ከደቂቃዎች በኋላ ጁንዲከስ አወቀ ለቡድኑ ሁለተኛ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ አደርጓል። በከፋ ቡናም የጎል ሙከራ በቁጥር አነስተኛ ሆኖ የታየበት ጨዋታ ሲሆን በ88ኛው ደቂቃ በቃሉ ተካ ለከፋ ቡና የጎል ሙከራ አድርጓል። በአጠቃላይ የጨዋታው የዓየር ላይ ኳሶች የበዙበት ሆኖ ያለግብ ተጠናቋል።

\"\"

በምድብ ሐ በደማቅ የደጋፊዎች ድባብ የጀመረው የሀምበሪቾ ዱራሜ እና ነገሌ አርሲ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ የነገሌ አርሲዎች የበላይነት የታየበትና ነበር። ግን በሁለቱም ቡድኖች በኩል ይሄ ነው የሚባል የግብ ሙከራ አልተመለከትንም ነበር። ሆኖም በሁለቱም በኩል ያለሸነፍ ባይነት ስሜት የነበረበት ሲሆን የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ምንም ግብ ወደ መልበሻ ክፍል ማምራት ችለዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሀምበሪቾ ዱራሜዎች መጠነኛ ቅያሬ በማድረግ ጨዋታውን ለመቆጣጠር የሞከሩ ሲሆን ጨዋታው የበለጠ ውጥረት የሞላበት እና ግብ ለማስቆጠር ፍላጎት የታየበት ነው። በ80ኛው ደቂቃ ከኳስ ውጪ በተፈጠረ ግብግብ በነገሌ አርሲ በኩል ሲሳይ ሚደቅሳ በቀይ ካርድ ከሜዳ መሰናበት የቻለ ሲሆን ቀሪውን 10 ደቂቃ ሀምበሪቾ ዱራሜ ጫና በማሳደር ግብ ለማስቆጠር የጣሩ ቢሆንም ነገሌ አርሲዎች ባደረጉት ጥረት ግብ ሳይቆጠርባቸው ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቅ ችሏል።

የ10:00 ጨዋታዎች

በምድብ \’ሀ\’ የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ የሆነው የሰንዳፋ በኬ እና የሰበታ ከተማ ጨዋታ ሲደረግ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ የበላይነቱን ለመውሰድ ጥሩ ፉክክር ቢታይበትም የጠሩ የግብ ዕድሎች ግን ያልተፈጠሩበት ነበር። በሰንዳፋዎች በኩል 8ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል አየለ ያደረገው ሙከራ በሰበታዎች በኩል  17ኛው ደቂቃ ላይ ምትኩ ጌታቸው ከተጋጣሚ የሳጥን አጠገብ የመታውና ግብጠባቂው የያዘው ኳስ በአጋማሹ የተሻሉ ሙከራዎች ነበሩ። በሁለቱም በኩል ብቅ እያለ የሚጠፋው የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ግን ጠንካራ አልነበረም።

\"\"

ከዕረፍት መልስም ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥል 58ኛው ደቂቃ ላይ የበኬው መሳይ ሰለሞን ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችሎ ነበር። ከጨዋታው አንዳች ነገር ለማግኘት ጥንቃቄ በተሞላ የኳስ ቁጥጥር እና የማጥቃት እንቅስቃሴ መጓዝ የቀጠሉት ሰበታዎች 60ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በቀኝ መስመር የተገኘውን የማዕዘን ምት ዮናስ ሰለሞን ሲያሻማ ያገኘው ኤፍሬም ቀሬ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የተሻለ የተንቀሳቀሱት ሰንዳፋዎች 87ኛው ደቂቃ ላይ በመሳይ ሰለሞን አማካኝነት ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። ጨዋታውም በሰበታ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ሰበታ ከተማ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያውን ሦስት ነጥብ አሳክቷል።

ተጠባቂ በነበረው የምድብ ለ የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ሻሸመኔ ከተማ እና ነቀምቴ ከተማ ተገናኝተዋል። በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥንቃቄ የተሞላበት የጨዋታ እንቅስቃሴ የታየ ሲሆን ሻሸመኔዎች ኳስ አንድ ሁለት በመቀባበል ወደ ተቃራኒ ቡድን ሜዳ ለመዝለቅ ቢሞክሩም በነቀምት የመከላከል አቅም ኳሶች በሚፈለጉበት አቅጣጫ እንዳየደርሱ ተደርገዋል።

\"\"

በነቀምት በኩል ከጥንቃቄ ባለፈ ያገኙትን ኳስ በመያዝ ወደ ሻሸመኔ የጎል ክልል ለመሄድ ሲሞክሩ ቅብብሎቻቸው በሚፈልጉት ልክ አጥቂዎቻቸው ጋር የሚደርሱ አልሆኑም። በሁለተኛ አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ሁለቱም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያሳዩን ጨዋታው ያለግብ ተጠናቋል።

ሆሳዕና ላይ የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ በዳሞት ከተማ እና ኮልፌ ክ/ከተማ መካከል ተከናውኗል። የመጀመሪያው አጋማሽ እጅግ አጓጊ እና ፍጥነት የታከለበት አጨዋወት በሁለቱም በኩል የተመለከትን ሲሆን በዳሞት ከተማ በኩል ጥሩ የኳስ ቁጥጥር እና ተደጋጋሚ የግብ ዕድል ተፈጥሯል። በአንፃሩ ኮልፌ ክ/ከተማዎች ኳሶች ሲቆራረጥባቸውና ውጤታማ ያልሆነ አጨዋወት ሲጫወቱ ተስተውሏል። በ23ኛው ደቂቃ ዳሞት ከተማዎች በጥሩ አጨዋወት የፈጠሩትን የግብ ዕድል ሳምሶን ቁልቻ በማስቆጠር መሪ መሆን የቻሉ ሲሆን ከግቧ መቆጠር በኋላም ዳሞት ከተማዎች ጫና መፍጠር ችለዋል። ኮልፌ ክ/ከተማዎችም በተመሳሳይ እንቅስቃሴ በመቀጠል ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

\"\"

ሁለተኛው አጋማሽም የዳሞት ከተማ የበላይነት የታየበት ሲሆን ኮልፌ ክ/ከተማዎች የመጀመሪያ አጋማሽ ድክመታቸውን ማረም ሳይችሉ የቀጠሉበት ጨዋታን ተመልክተናል። በ74ኛው ደቂቃ ዳሞት ከተማዎች ተጋጣሚያቸው ላይ ጫና በመፍጠር ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ሱልጣን አቢዩ በማሽቆጠር የዳሞት ከተማን መሪነት ማጠናከር የቻለ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ አንተነህ ማታዩስ በራሱ ግብ ላይ በማስቆጠር የዳሞት ከተማን ሦስተኛ ግብ በማስቆጠር ጨዋታውም ዳሞት በሰፊ የግብ ልዩነት ማሸነፍ ችሏል።