ቻን | አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከመጨረሻው የምድብ ጨዋታ በኋላ ምን አሉ?

👉 \”እኔ ወደ ብሔራዊ ቡድኑ ከመጣሁ በኋላ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ቡድኑን እየገነባን ነው ፤ በተቻለኝ አቅም ቡድኑን ወደፊት ለመውሰድ እየሞከርኩ ነው\”

👉 \”የግብ ጠባቂም ሆነ ሌላ ተጫዋች አልወቅስም ግን…\”

👉 \”ሊቢያዎች ጨዋታውን ማሸነፍ ይገባቸዋል\”


👉 \”የነበርንበት ምድብ ከባድ ነበር ማለት እንችላለን\”

7ኛው የአፍሪካ ሀገራት ሻምፒዮን ሺፕ በአልጄሪያ እየተደረገ የሚገኝ ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጵያም በምድብ አንድ ከአዘጋጇ አልጄሪያ፣ ሊቢያ እና ሞዛምቢክ ጋር ተደልድላ ሦስት ጨዋታዎችን አድርጋለች። ማግኘት ከሚገባው ዘጠኝ ነጥብ አንድ ነጥብ ብቻ ያሳካው ዋልያውም ከውድድሩ ውጪ መሆኑ ምሽት ላይ ተረጋግጧል። አሠልጣኝ ውበቱ አባተም ብሔራዊ ቡድኑ ከምድብ ከተሰናበተበት የምሽቱ የሊቢያ ጨዋታ በኋላ ስለጨዋታው፣ ስለውድድሩ እና አጠቃላይ ስለቡድናቸው መግለጫ ሰጥተዋል።

\"\"

\”እንደ አጋጣሚ ሆኖ ወደቀጣዩ ዙር ለማለፍ የተሻለ ዕድል ነበረን። የራሳችንን ጨዋታ አሸንፈን የአልጄሪያ እና ሞዛምቢክን ጨዋታ ውጤት መጠበቅ ነበረብን። ነገርግን የእኛ ጨዋታ ባሰብነው መልኩ አልሄደም። በተለይ አንድ ለምንም ከመራን በኋላ ወዲያው ቀላል ጎል ተቆጠረብን። ይሄ ተጫዋቾቼ ላይ የተወሰነ ጫና ፈጥሯል። የግብ ጠባቂም ሆነ ሌላ ተጫዋች አልወቅስም ግን ሁለተኛውም ጎል የተቆጠረብን በጣም ቀላል ኳስ ነበር። በዚህ አይነት መልኩ ግብ ማስተናገድ ለተጫዋቾቹ ከባድ ነው።\” በማለት በጨዋታው ላይ ያላቸውን ምልከታ ካጋሩ በኋላ ስለተጋጣሚያች ሊቢያ ተከታዩን ብለዋል።

\”ተጋጣሚያችንን በተመለከተ እንደ ቡድን እኛን ለመጫን ሞክረዋል። መጀመሪያ ወረድ ብለው ነበር ለመንቀሳቀስ የሞከሩት ከዛ ጫና ለመፍጠር እና ለማሸነፍ ወጣ ብለው ተጫውተዋል። ጨዋታውንም ማሸነፍ ይገባቸዋል።\”

አሠልጣኝ ውበቱ አባተ አስከትለው ቡድናቸው በውድድሩ ስላደረገው እንቅስቃሴ ተጠይቀው \”በውድድሩ ጥሩ ለመጫወት ሞክረናል። ለእኛ ጥሩ መሻሻል ነው። በመጀመሪያውም በሁለተኛውም ጨዋታ ጥሩ ተንቀሳቅሰናል። በአልጄሪያው ጨዋታም ያለንን ነገር ለማሳየት ሞክረናል። ዛሬ ደግሞ ጨዋታውን በጥሩ ሁኔታ መቆጣጠር ሳንችል ተሸንፈን ወጥተናል። ይህ ቢሆንም ግን እድገቶች አሉ። ከስምንት ዓመታት በኋላ ነው በዚህ ውድድር የተሳተፍነው ፤ በቀጣይ በየዓመቱ መሳተፍ መቻል አለብን። እኔ ወደ ብሔራዊ ቡድኑ ከመጣሁ በኋላ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ቡድኑን እየገነባን ነው። በተቻለኝ አቅም ቡድኑን ወደፊት ለመውሰድ እየሞከርኩ ነው። በአፍሪካ ዋንጫ እና ቻን ውድድር ላይ ተሳትፈናል። ይህ ሂደት ነው። እየተማረን ነው የምንመጣው። ተጫዋቾቹም ራሳቸውን ደረጃ በደረጃ እያሻሻሉ ነው።\” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

\"\"

በመጨረሻም ውድድሩ ጠንካራ መሆኑን እና የተደለደሉበት ምድብ ጠንካራ መሆኑን ያመላከቱበትን ሀሳብ ለብዙሃን መገናኛ አባላት በተከታዩ መልኩ አጋርተው ሀሳባቸውን ቋጭተዋል። \”የተመደብንበት ምድብ ላይ ያሉት ቡድኖች ከባድ ናቸው። ሦስቱም ቡድኖች ተወዳዳሪ ናቸው። የነበርንበት ምድብም ከባድ ነበር ማለት እንችላለን። ከሌሎቹ ምድቦች አንፃር እኛ ምድብ ላይ የሚገኙት ቡድኖች ቴክኒካሊ እንዲሁም ታክቲካሊ ጥሩ ተጫዋቾች አላቸው። በተጨማሪም እንደ አፍሪካ ዋንጫው በአዘጋጅ ሀገር ምድብ ነው የተደለደልነው። አጠቃላይ ውድድሩ የቻን ሳይሆን የአፍሪካ ዋንጫ ነው የሚመስለው። ጠንካራ ፉክክር ነበረው። በዚህም ብዙ ትምህርቶችን ወስደናል።\”