ከፍተኛ ሊግ | የ11ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ በ11 ጨዋታዎች ቀጥሎ ሲካሄድ ትኩረት ሳቢ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

በቶማስ ቦጋለ ፣ ጫላ አቤ እና ተመስገን ብዙ ዓለም

የ03:00 ጨዋታዎች

ባህርዳር ላይ የወሎ ኮምቦልቻ እና የሰንዳፋ በኬ ጨዋታ ሲደረግ መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል መጨረሻ ኳሳቸው ደካማ ይሁን እንጅ በቀጥተኛ ኳሶች ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲሞክሩ ተስተውሏል። የጨዋታው የመጀመሪያ የተሻለ ሙከራም 19ኛው ደቂቃ ላይ ሲደረግ የሰንዳፋው ፋሲል ደስታ ከሳጥን አጠገብ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም በግቡ የግራ ቋሚ ለጥቂት ወጥቶበታል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነትም ኮምቦልቻዎች በጥሩ የኳስ ቅብብል በወሰዱት እና ሲሣይ አቡሌ በግንባሩ በገጨው ኳስ የመጀመሪያቸውን ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ አድርገዋል። ጨዋታው እንደነበረው ፉክክር የግብ ዕድሎች ሊፈጠሩበት ያልቻለ ሲሆን 36ኛው ደቂቃ ላይ የወሎ ኮምቦልቻው ሄኖክ ጥላሁን ከረጅም ርቀት አክርሮ መትቶት የግቡን አግዳሚ ታክኮ የወጣው ኳስም ሌላኛው ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።

\"\"

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እጅግ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በአጋማሹም በሰንዳፋ በኬ ከተደረጉ ሁለት ሙከራዎች ውጪ የጠሩ የግብ ዕድሎችን አላስመለከተንም። 51ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲል ደስታ ከቅጣት ምት ድንቅ ሙከራ ቢያደርግም ግብጠባቂው እና የግቡ አግዳሚ ግብ ከመሆን ሲያግዱት ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ የአብሥራ በለጠ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ወደግብ ያደረገውን ሙከራ ግብጠባቂው ታሪኩ አራዱ መልሶበታል። ሆኖም ጨዋታውም ያለግብ ተጠናቋል።

ጅማ ላይ በምድብ \’ለ\’ ንብን ከሻሸመኔ አገናኝቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ ንቦች ሻሸመኔዎች መስርተው እንዳይጫወቱ በማቋረጥ በሚያገኙት ኳስ ወደ ሻሸመኔ የግብ ክልል ቢደርሱም አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። ሻሸመኔዎችም በተመሳሳይ ጥሩ ቅብብል ለማድረግ ቢሞክሩም የጠሩ የግብ ዕድሎችን ግን ለመፍጠር ተቸግረዋል።

ከዕረፍት መልስ ንቦች ተሻሽለው ሲቀርቡ  ለአጥቂዎቻቸው በሚመች መልኩ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ 60ኛው እና 69ኛው ደቂቃ ላይ በአብዱፈታ አደም እና በኤልያስ እንድሪስ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል። ግብ ካስቆጠሩ በኋላም በርካታ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ችለው ነበር። ሻሸመኔዎች በአንጻሩ የመኃል ሜዳ ላይ ብልጫ ለመውሰድ ጥሩ ቢንቀሳቀሱም የተሻለ የግብ ዕድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። ጨዋታውም በንብ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

\"\"

የ05፡00 ጨዋታዎች

ባህርዳር ላይ ሀላባ ከተማ እና ጋሞ ጨንቻን ያገናኘው ጨዋታ ሲደረግ ለተመልካች እጅግ አዝኛኝ የሆነ ብርቱ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል በርካታ የግብ ዕድሎች ሲፈጠሩ በአንጻሩ ግን ጋሞ ጨንቻዎች የተሻሉ ነበሩ። ሀላባዎች ገና በሁለተኛው ደቂቃ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። የጋሞው ተከላካይ ተክሉ ታፈሰ እና ግብጠባቂው ንጉሤ ሙሉጌታ ባለመግባባት በሠሩት ስህተት ኳሱን አቋርጦ ያገኘው ፎሳ ሴዴቦ በቀላሉ ማስቆጠር ችሏል። በሚያገኙት ኳስ ሁሉ አስፈሪ የማጥቃት እንቅስቃሴ በማድረግ የሚታወቁት ጨንቻዎች ቀስ በቀስ በጨዋታው የበላይነቱን መውሰድ ሲችሉ 29ኛው ደቂቃ ላይ ዘላለም ኢያሱ ከቀኝ መስመር ባሻገረውና ፍስሐ ቶማስ በግንባሩ በመግጨት ባስቆጠረው ግብ አቻ መሆን ችለዋል። ጨዋታውን ከጀመሩበት እንቅስቃሴ እየወረዱ የመጡት በርበሬዎቹ 38ኛው ደቂቃ ላይ በሰዒድ ግርማ ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር።

\"\"

ከዕረፍት መልስ ሀላባዎች እጅግ ተሻሽለው ሲቀርቡ 53ኛው ደቂቃ በፎሳ ሴዴቦ ተጨማሪ ግብ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። የጨዋታውን ሚዛን በቁጥጥራቸው ሥር ያደረጉት ሀላባዎች 72ኛው ደቂቃ ላይም በሙሉቀን ተሾመ የቅጣት ምት ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። በአጋማሹ እጅግ ተዳክመው የቀረቡት ጋሞ ጨንቻዎች 73ኛው ደቂቃ ላይ ሰለሞን ጌታቸው ከሞከረውና ግብጠባቂው ከመለሰው ኳስ ውጪ ፈታኝ ሙከራ ለማድረግ ሲቸገሩ ይባስ ብሎም 75ኛው ደቂቃ ላይ  ተጨማሪ ግብ ተቆጥሮባቸዋል። ግብጠባቂው ንጉሤ ሙሉጌታ በወረደ ውሳኔ በእግሩ መቆጣጠር ያልቻለውን ኳስ ያገኘው ሀብታሙ በየነ ተቀይሮ ወደ ሜዳ በገባበት ቅፅበት በቀላሉ ማስቆጠር ችሏል። ጨዋታውን በማረጋጋት መጨረስ የፈለጉት ሀላባዎች 82ኛው ደቂቃ ላይም በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው ፎሳ ሴዴቦ ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። ጨዋታውም በሀላባ ከተማ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ጅማ ላይ ከፋ ቡናን ከ ቂርቆስ ክ/ከተማ ባገናኘው ጨዋታ ከፋ ቡናዎች ከተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝተው በመገኘት የቂርቆስ ተከላካዮች የሚሠሩትን ስህተት በመጠቀም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ 27ኛው እና 42ኛው ደቂቃ ላይም በዮናታን ከበደ እና በታከለ ታንቶ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። ቂርቆሶች በበኩላቸው የራሳቸው የሜዳ ክፍል ላይ የተሳኩ ቅብብሎችን በማድረግ ወደ ተጋጣሚ ክልል ለመግባት ቢሞክሩም የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ግን ሲቸገሩ ተስተውሏል።

ከዕረፍት መልስ ከፋ ቡናዎች ወደ መከላከሉ በማመዘን በሚያገኙት ኳስ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲሞክሩ 78ኛው ደቂቃ ላይ ዮናታን ከበደ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በግሩም ሁኔታ በግንባሩ በመግጨት ማስቆጠር ችሏል። በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ ተሻሽለው የቀረቡት ቂርቆሶች 63ኛው እና 73ኛው ደቂቃ ላይ በክብሮም ፅድቁ እና አ/መጅድ ሁሴን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ከከፋ ቡና የተከላካይ መስመር ከባድ ፈተና ገጥሟቸው ተስተውሏል። ጨዋታውም በከፋ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

\"\"

በምድብ ነጌሌ አርሲ እና የካ  ክ/ከተማ ተገናኝተዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ በጣም ውጥረት የበዛበት ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች ለመሸናነፍ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። ከዚህም ባሻገር ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ የመድረስ እንቅስቃሴ በሁለቱም በኩል የተመለከትን ነበር። በ19ኛው ደቂቃ ነጌሌ አርሲዎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት በምስጋናው ሚኪያስ አማካኝነት በማስቆጠር መሪ መሆን የቻሉ ቢሆንም ከግቧ መቆጠር በኋላ የካ ክ/ከተማዎች አቻ ለመሆን ተጭነው በመጫወት በ27ኛው ደቂቃ ያገኙትን የግብ እድል ሀይልሽ ፀጋዬ በማስቆጠር የካ ክ/ከተማን አቻ ማድረግ ችሏል። ጨዋታው ከግቦቹ መቆጠር በኋላ ውጥረት የታየበትና ከዳኞች ጋር አለመግባባት እንደነበር ተስተውሏል። የመጀመሪያ አጋማሽም በአቻ ውጤት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ ቀዝቀዝ ያለበት እና ብዙም የግብ ሙከራ ያልታየበት አጋማሽ ሲሆን አልፎ አልፎ በብስራት በቀለ የሚመራው የየካ ክ/ከተማ የፊት መስመር የሚያደርጉትን የግብ ዕድል በግብ ጠባቂው አባቱ ጃርሶ ሲከሽፍ የነበረ ሲሆን በነጌሌ አርሲ በኩል በአብዱላኪም ሱልጣን የሚመራው የፊት መስመር የግብ ሙከራ ሲያደርግ የነበረ ታይትቷል። ሆኖም ወደ ግብ መቀየር ተስኗቸው በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቅ ችሏል።

የ08፡00 ጨዋታዎች

በምድብ \’ሀ\’ ባህርዳር ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ጨዋታ ሲደረግ ብርቱ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የመሃል ሜዳው ላይ ብልጫ ለመውሰድ ጥሩ ፍልሚያ ታይቶበታል። ይሁን እንጅ ሁለቱም የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል። በአንጻራዊነት የተሻሉ የነበሩት ንግድ ባንኮች 38ኛው ደቂቃ ላይ በአቤል ማሙሽ ግብ መሪ መሆን ሲችሉ ግብ የሆነው ኳስ ከግራ መስመር ሲሻማ በውጪ ዞሮ ነው ኳሱ አግቢው እግር የደረሰው በሚል በአዲስ ከተማዎች በኩል ከፍተኛ ቅሬታ ቀርቦ ጨዋታውም ለአራት ደቂቃዎች ያህል ለመቋረጥ ተገዶ ነበር።

\"\"

በሁለተኛው አጋማሽ ፍጹም የበላይነቱን መውሰድ የቻሉት ንግድ ባንኮች 55ኛው ደቂቃ ላይ በማራኪ ቅብብል የወሰዱትን ኳስ በመጨረሻም በረከት ግዛቸው በግሩም አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል። መረጋጋት የተሳናቸው አዲስ ከተማዎች ከኳስ ውጪ የንግድ ባንክን እንቅስቃሴ ለመመከት ሲቸገሩ ተስተውሏል። በተረጋጋ የጨዋታ መንፈስ መጓዝ የቀጠሉት ንግድ ባንኮች 76ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ማሙሽ ከረጅም ርቀት አክርሮ መትቶት የግቡን የግራ ቋሚ ታክኮ በወጣው ኳስም በቀሪዎቹ ደቂቃዎች የተሻለውን ሙከራ አድርገዋል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነገ ከሚደረገው የቤንች ማጂ ቡና እና የወልዲያ ከተማ ጨዋታ ላይ ከሚፈጠረው የነጥብ ልዩነት በፊት የምድቡ መሪ ሆኗል።

\"\"

ጅማ ላይ በጅንካ እና ጉለሌ ጨዋታ ጅንካዎች ጨዋታው በተጀመረ በ4ኛ ደቂቃ በኢትዮ ሎሳንጉሌ ጎል በማግባት መሪ መሆን ችለዋል። በጨዋታው ኃይል የተቀላቀለው እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ተከላከይ መስመር ተጫዋቾች ከተቃራኒ አጥቂዎች ኳስ በመንጠቅ በረጅም ኳስ በግራና በቀኝ ኳሶችን ሲያሻግሩ የነበረ ቢሆንም የጎል ሙከራም ብዙም ማድረግ አልቻሉም። የጉለሌ እንቅስቃሴ ኳስ በመጫወት ጎል ለማስቆጠር  ቢሞክሩም የጅንካ ተጫዋቾች አቅም በተሞላው ኳስን በመንጠቅ እንቅስቃሴ የተሻሉ ስለሆኑ ጉለሌዎች የጎል ሙከራዎች  ማድረግ አልቻሉም።

በሁለተኛ አጋማሽ ጅንካዎች ወደ መከላከሉ አመዝነው በመጫወት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ በተጋጣሚያቸው ፍፁም የኳስ ቁጥጥር ተወስዶባቸዋል። ጨዋታውን በመከላከል ውጤት አስጠብቀው ለመጨረስ ቢፈልጉም አልተሳካላቸውም። የጉለሌ በሁለተኛ አጋማሽ የጫዋታ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ከተጋጣሚያቸው ጅንካ  የኳስ ብልጫ ሲወስዱ በሁሉም የሜዳ አቅጣጫ የማጥቃት እንቅስቃሴ በተጋጣሚ የጎል ክልል ሙከራዎች አድርገዋል። በመጨረሻም 87ኛው ደቂቃ ላይ አቻ ምታደርጋቸውን ጎል በጁንዲክስ አወቀ አማካይነት አስቆጥረዋል። በተቀሩት ደቂቃዎች ማሸነፊያ ጎል ለማስቆጠር ቢጥሩም አልተሳካላቸውም ፤ ጨዋታውም  አንድ ለአንድ በሆነ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

\"\"

በምድብ ሐ ገላን ከተማ እና ሀምበሪቾ ዱራሜን ያገናኘው ጨዋታ ተጠባቂ ነበር። የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ የገላን ከተማ የበላይነት የታየበትና በኳስ ቁጥጥሩም ተሽለው ተነኝተዋል። ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በመድረስም ገላን ከተማዎች የተሻሉ ሲሆኑ ሀምበሪቾ ዱራሜዎች በአብዛኛው በረጅም ኳስ ወደ ግብ ለመድረስ ሲሞክሩ ተስተውሏል። በ24ኛው ደቂቃ ገላን ከተማዎች ያገኙትን የቅጣት ምት በማሻማት የኋላሸት ፍቃዱ በግንባሩ በማስቆጠር ገላን ከተማን መሪ ማድረግ የቻለ ሲሆን የመጀመሪያ አጋማሽም በገላን ከተማ መሪነት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሀምበሪቾ ዱራሜ የተሻለ ሲሆን ግብ ለማስቆጠርም በተቻላቸው መጠን ጫና ፈጥረው የተጫውተዋል። በአንፃሩ ገላን ከተማዎች ያገኙትን የግብ ብልጫ ለማስጠበቅ ወደ ኋላ በማፈግፈግ የተጫወቱ ሲሆን በ79ኛው ደቂቃ ሀምበሪቾ ዱራሜዎች ያገኙትን የቅጣት ምት ደስታ ግቻሞ በግንባሩ በማስቆጠር አቻ አድርጓቸዋል። ከግቧ መቆጠር በኋላም ሀምበሪቾ ዱራሜ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ምንም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቅ ችሏል። ውጤቱንም ተከትሎ ሀምበሪቾ ዱራሜ አሁንም ምድቡን እየመራ ይገኛል።

የ10፡00 ጨዋታዎች

ፍጹም ተቃራኒ አጋማሾች በታዩበት የሰበታ ከተማ እና የአቃቂ ቃሊቲ የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ቀዝቃዛ ፉክክር የታየበት ሲሆን በአጋማሹ የተሻለው ሙከራም 6ኛው ደቂቃ ላይ በአቃቂዎች ተደርጓል። ሊዮናርዶ ሰለሞን ያቀበለውን ኳስ ያገኘው እሸቱ ጌታሁን ወደ ግብ ሲሞክር የኳሱ ኃይል የለሽነት ተጨምሮበት ግብጠባቂው በቀላሉ መልሶበታል። ከዚህ ሙከራ በኋላም በሁለቱም በኩል የጠሩ የግብ ዕድሎችን ሳያስመለክተን ወደ ዕረፍት አምርተዋል።

\"\"

ሁለተኛው አጋማሽ ለተመልካች እጅግ አዝናኝ የነበር ሲሆን አምስት ግቦችም ተቆጥረውበታል። በመጀመሪያም 49ኛው ደቂቃ ላይ በኃይሉ ወገኔ ከእሸቱ ጌታሁን የተሻገረለትን ኳስ አስቆጥሮት አቃቂን መሪ ሲያደርግ 58ኛው ደቂቃ ላይም ሰለሞን ያለው ከበኃይሉ ወገኔ የተቀበለውን ኳስ ወደግብ ሞክሮት ግብጠባቂው የመለሰበትን ኳስ ያገኘው ተቀይሮ ወደ ሜዳ ከገባ ሦስት ደቂቃዎች ያልሞሉት አብዩ ቡልቲ አስቆጥሮት የአቃቂን መሪነት አጠናክሯል። ከዚህ ግብ በኋላ በእንቅስቃሴው ብልጫ መውሰድ የቻሉት ሰበታዎች 65ኛው ደቂቃ ላይ በኤፍሬም ቀሬ አማካኝነት ግብ ማስቆጠር ሲችሉ በ አራት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ ብሩክ ግርማ ከሳጥን ውጪ ድንቅ ግብ ማስቆጠር ችሎ ጨዋታውን አቻ አድርጎታል። ከኋላ በመነሳት አቻ የሆኑት ሰበታዎችም በተሻለ የጨዋታ መንፈስ ጨዋታውን እያስኬዱ የማሸነፊያ ግብ ለማስቆጠር በሚጥሩበት ሁኔታ የራሳቸው ሳጥን ውስጥ በፈጠሩት መዘናጋት በሊዮናርዶ ሰለሞን ግብ ተቆጥሮባቸዋል። ጨዋታውም በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

\"\"

ጅማ ላይ በዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ነቀምቴ እና እንጅባራ ተገናኝተዋል። ነቀምቶች ጫና በመፍጠር ከሚነጠቁ ኳሶች በረጅሙ ወደፊት በመጣል የጎል ዕድል ለመፍጠር በማሰብ ቢንቀሳቀሱም የጎል ዕድል መፍጠር አልቻሉም። የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ለመያዝ ይጥሩ የነበሩት እንጅብራዎችም ቅብብሎቻቸው ይቆራረጡ ነበር። ቡድኑ 15ኛ ደቂቃ ላይ በትኩሱ ጌታቸው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሲያደርጉ ከዚህ በተጫማሪ የጎል ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

በሁለተኛ አጋማሽ በጫወታ  የተለየ  እንቅስቃሴ ባይኖርም ነቀምቶች በመጀመሪያው አጋማሽ ያሳዩትን እንቅስቃሴ ሲደግሙት በማጥቃቱ በኩል ኳሶችን በረጃጅም በመጣል ለማጥቃት ሞክረዋል። 59ኛው ደቂቃ ላይ የገኙትን ኳስ በቦና ቦካ አማካይነት አስቆጥረው መምራት ችለዋል። በ77ኛ ደቂቃ በገመቺስ አማኑኤል ሁለተኛ ጎል ለማስቆጠር ቢሞክርም በእንጅባራው ግብ ጠባቂ ብቃት ጎል ሳይቆጠር ቀርቷል።

እንጅባራዎች ተጭነው ለመጫወት ሲሞክሩ  ኳስ በመቀባበል ወደ ነቀምት የግብ ክልል  ወደ ፊት ቢሄዱም የነቀምንት የተከላካይ መስመር ተጫዋቾች የመከላከል ታክቲክ  አልፈው ጎል ማስቆጠር አልቻሉም። በ63ኛው ደቂቃ በባሕሩ ጥላሁን ድንቅ የጎል ሙከራ ቢያደርግም በነቀምንት ግብ ጠባቂ መክናለች። በተቀሩት ደቂቃዎች እንጅባራዎች ጎል ለማግባት በተደጋጋሚ ወደ ነቀምንት የጨዋታ ክልል  በማስከፈት ለማግባት ቢሞክሩም በነቀምንት  ተከላካዮች ጥንቃቄ የተሞላው መከላከል ጎል ማስቆጠር ሳይችለ ቀረተዋል ። ጨዋታውም በነቀምንት 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሆሳዕና ላይ ኮልፌ ክ/ከተማ እና ሮቤ ከተማ የምድብ ሐ የዕለቱ የመጨረሻ ጫዋታ ከውነዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ የኮልፌ ክ/ከተማ የበላይነት የታየበት ጨዋታ ሲሆን በኳስ ቁጥጥሩም የበላየነቱንም ኮልፌ ክ/ከተማዎች ወስደዋል። ሮቤ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት አልፎ አልፎ ወደ ግብ የሚደርሱ ሲሆን የመጀመሪያው አጋማሽም ምንም ግብ ሳይቆጠር ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

\"\"

ሁለተኛው አጋማሽ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታየበት ጨዋታ ሲሆን ኮልፌ ክ/ከተማ ኳሱን ተቆጣጥሮ ሲጫወት ሮቤ ከተማ የሚያገኙትን ዕድል በመልሶ ማጥቃት ወደ ግብ ደርሰዋል። በ64ኛው ደቂቃ ሮቤ ከተማዎች በአብዱላዚዝ ኦማር አማካኝነት አስቆጥረው ጨዋታውን መምራት የቻሉ ሲሆን ከግቧ መቆጠር በኋላ ኮልፌ ክ/ከተማዎች በጣም ተጭነው ግብ ለማስቆጠር ጥረዋል። ሮቤ ከተማዎች ወደ ግባቸው ተጠግተው በማፈግፈግ የገኙትን የግብ የበላይነት ለማሰጠበቅ ሲጫወቱ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመረው የባከነ ደቂቃ ኮልፌ ክ/ከተማዎች የመጨረሻ ዕድላቸውን ለመጠቀም የግብ ክልላቸውን ለቀው ለማጥቃት በወጡ ሰዓት ሮቤ ከተማዎች ያገኙትን የመልሶ ማጥቃት በያሬድ መኮንን አማካኝነት በማስቆጠር አሸናፊነታቸውን ማረጋገጥ ችለዋል። በጨዋታው ሮቤ ከተማ ድል በማድረግ ጣፋጭ ሦስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል።