ቻን | የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከቻን ውጪ ሆኗል

ዋልያዎቹ በመጨረሻው የምድብ ጨዋታ በሊቢያ አቻቸው የሦስት ለአንድ ሽንፈት ገጥሟቸው ከውድድሩ ውጪ ሆነዋል።

\"\"

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአልጀርያ ሽንፈት ካስተናገደበት ስብስብ ፉዐድ ፈረጃን በቢንያም በላይ ተክቶ ሲገባ ሊቢያ ደግሞ በሞዛምቢክ ሽንፈት ካስተናገደው ስብስብ አምስት ለውጦች በማድረግ ጨዋታውን ጀምረዋል።

በሁለቱም ቡድኖች በኩል ማራኪ እንቅስቃሴ ባልታየበት አጋማሽ ሙከራ በማድረግ ረገድ ቀዳሚ የነበሩት ዋልያዎቹ ሲሆኑ ሙከራዋም አማኑኤል ገብረሚካኤል ከከነዓን ማርክነህ የተላከለትን ኳስ ሳጥን ውስጥ ለነበረው ቸርነት ጉግሳ አቀብሎ የመስመር አጥቂው ያመከናት ኳስ ናት። ሊቢያዎች ምንም እንኳ አመርቂ የሚባል የማጥቃት አጨዋወት ባይከተሉም የኢትዮጵያን አማካዮች የመቀበባበያ መስመር በመሸፈን በኩል ግን ተሳክቶላቸዋል። በተለይም ቡድኑ ከኳስ ውጪ የነበረው እንቅስቃሴ ጥሩ የሚባል ነበር።

ቡድኑ ካደረጋቸው ሙከራዎች ውስጥም አጥቂው ሳልቱ ከቱሃሚ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ተጠቅሞ የሞከረው ኳስ ፣ አል አባሲ ከቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ እና ሳልቱ በግራ እግሩ አክርሮ መቶ ፋሲል ገብረሚካኤል በቀላሉ የያዘው ኳስ ይጠቀሳሉ።

በአጋማሹ መረጋጋት አቅቷቸው የረባ እንቅስቃሴ ማድረግ ያልቻሉት ዋልያዎቹ በሠላሳ ስምንተኛው ደቂቃ ላይ ሊቢያዎች በሳጥናቸው በከነዓን ማርክነህ ላይ በሰሩት ጥፋት የተገኘው ፍፁም ቅጣት ጋቶች ፓኖም ወደ ግብነት ቀይሮ ኢትዮጵያን መሪ ማድረግ ችሏል። ሆኖም የኢትዮጵያ መሪነት የቆየው ለደቂቃዎች ነበር። በአርባ አራተኛው ደቂቃ ላይ ዓሊ አቡ አርቁብ ከሳጥን ውጪ የመታትን ኳስ የፋሲል ገብረሚካኤል ስህተት ታክሎባት መረብ ላይ አርፋለች።

እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ የረባ እንቅስቃሴ ፣ የተጠና አጨዋወት እና ጥሩ የጨዋታ መንፈስ ባልታየበት ሁለተኛው አጋማሽ በቁጥር ጥቂት ሙከራዎች ብያስመለክተንም በኢትዮጵያ በኩል የተፈጠሩ የግብ ዕድሎች ግን ከተጋጣሚ አንፃር ሲታይ ለግብ የቀረቡ ነበሩ። ሆኖም ግብ በማስቆጠር ረገድ የቀናቸው ሊብያዎች ነበሩ። በሀምሳኛው ደቂቃ ላይ አልኪህጃ ከመስመር ያሻማትን ኳስ ግብ ጠባቂው ጨርፏት ከተከላካዮች ደካማ የቦታ አያያዝ ችግር ተዳምሮ አብዱላቲ አባሲ በቀላሉ ወደ ግብነት ቀይሯታል።

ከግቡ በኋላ የተሻሉ ለግብ የቀረቡ ዕድሎች የፈጠሩት ዋልያዎቹ በርከት ያሉ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም ዱሪሳ ሹቢሳ በተከላካዮች ስህተት አግኝቶ መቷት ለጥቂት የወጣችው ኳስ ፤ ረመዳን የሱፍ ከጋቶች ፓኖም የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ለግብ የቀረበች ሙከራ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ባሳጥን ውስጥ መቷት ግብ ጠባቂው ያዳናት ኳስ እጅግ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

በሰባ ስምንተኛው ደቂቃም ሊቢያዎች በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ መሐሙድ አብዱሰላም እና አቡ አርቁብ ተቀባብለው ለአጥቂው ያመቻቹለት ኳስ ረጅሙ አጥቂ ወደ ግብነት ቀይሮ የሊቢያን መሪነት ወደ ሦስት አስፍቶታል። ጨዋታው በዚህ ውጤት መጠናቀቁ ተከትሎ አዘጋጅዋ አልጀርያ እና ሞዛምቢክ ወደ ቀጣይ ዙር ስያልፉ ሊቢያ እና ኢትዮጵያ ከውድድሩ ውጪ ሆነዋል።

\"\"