ለገጣፎ ለገዳዲ የስድስት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቋል

የአሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊሱ ለገጣፎ ለገዳዲ ከሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ ተጫዋች በማስፈረም ዝውውሩን አገባዷል።

በዝውውር መስኮቱ ላይ የበለጠ ተሳትፎን ካደረጉ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው እና በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ ተቀምጦ የሚገኘው ለገጣፎ ለገዳዲ ስድስት አዳዲስ ተጫዋችን በማስፈረም ከተስፋዬ ነጋሽ እና ኤልያስ አታሮ በመቀጠል የአዳዲስ ተጫዋቾችን ቁጥር ስምንት አድርሷል።

ጋናዊው ግብ ጠባቂ ኮፊ ሜንሳህ የመጀመሪያው የውጪ ዜጋ ሆኖ የለገጣፎ ተጫዋች ሆኗል። የግብ ዘቡ በሀገሩ ክለቦች ኢብሱዋ ዱዋራፍስ ፣ አሻንቲ ጎልድ እና መዲያማ ቡድኖች ውስጥ ቆይቶ ወደ ለገጣፎ አምርቷል።

\"\"

ናይጄሪያዊው አጥቂ ኢማኑኤል አላራይብ ሁለተኛው የለገጣፎ የውጪ ዜጋ ተጫዋች ሆኗል። ለሀገሩ ክለብ ኦሎምፒክ ሀይብሪድ ፣ ለሞልዶቫዎቹ ኮድሩ እና ባሊቲ እንዲሁም በእስራኤሉ ራማት ሀሻሮን የተጫወተው ተጫዋቹ ቀጣይ መዳረሻው ኢትዮጵያ መሆኑ ዕርግጥ ሆኗል።

ዘነበ ከድር ሳይታሰብ ወደ ለገጣፎ አምርቷል። የቀድሞው የነገሌ ቦረና ፣ ደቡብ ፓሊስ እና ሀዋሳ ከተማ የመስመር ተከላካይ በክረምቱ በሁለት ዓመት ውል ኢትዮጵያ ቡናን ቢቀላቀልም በስምምነት በመለያየት ለገጣፎን ተቀላቅሏል።

ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ሌላኛው ፈራሚ ነው። የቀድሞው የመቻል ፣ መቐለ 70 እንደርታ እና ወልቂጤ ከተማ ተጫዋች ያለፉትን ወራት ያለ ክለብ ካሳለፈ በኋላ በመጨረሻም ወደ ለገጣፎ አምርቷል።

ያሬድ ሀሰን የለገጣፎ ሰባተኛው አዲሱ ተጫዋች ነው። የቀድሞው የወልድያ ፣ መቐለ 70 እንደርታ ፣ ድሬዳዋ ከተማ ፣ ሰበታ እና አዲስ አበባ የግራ መስመር ተከላካይ ባለፈው ዓመት አጋማሽ ለስድስት ወራት በቅዱስ ጊዮርጊስ ዘንድሮ ደግሞ ያለፉትን ወራት በከፍተኛ ሊጉ ክለብ ደሴ ቆይታ ነበረው።

\"\"

በጅማ አባጀፋር ያለፉትን ዓመታት ያሳለፈው የመስመር እና የመሀል አማካዩ ሱራፌል አወልም የዝውውር መስኮቱ ለሊት ከመዘጋቱ በፊት የክለቡ ስምንተኛ ፈራሚ ሆኗል።

ቡድኑ ከአማካዩ ዮናስ በርታ እንዲሁም ከሌሎች ሦስት ተጫዋቾችም ጋር በስምምነት መለያየቱንም አውቀናል።