ከፍተኛ ሊግ | የ12ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 12ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ ዘጠኝ ጨዋታዎች ሲፈፀም አዲስ አበባ ከተማ ምድብ \’ለ\’ን መምራት ጀምሯል።

በቶማስ ቦጋለ ፣ ጫላ አቤ እና ተመስገን ብዙዓለም

የ04፡00 ጨዋታዎች

ባህርዳር ላይ በምድብ \’ሀ\’ ቡታጅራ ከተማ እና ሰበታ ከተማ ሲገናኙ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩም ይሁን የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ቡታጅራዎች እጅግ የተሻሉ ነበሩ። ረፍት የለሽ እንቅስቃሴ በማድረግም በርካታ ሙከራ ሲያደርጉ በተለይም 34ኛው ደቂቃ ላይ ሙፋድ እንድሪስ ከቅጣት ምት ጥሩ ሙከራ  አድርጎ ግብጠባቂው የመለሰበት ኳስ በአጋማሹ የተሻለው ሙከራ ነበር። ካለፉት ሁለት ጨዋታዎች እጅግ ተዳክመው የቀረቡት ሰበታዎች 40ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለውን ሙከራቸውን ሲያደርጉ ምትኩ ጌታቸው ከሳጥን አጠገብ ያደረገው ሙከራ የግቡን የላዩ አግዳሚ ታክኮ ወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስም ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥል ቡታጅራዎች 62ኛው ደቂቃ ላይ በክንዴ አብቹ ድንቅ የቅጣት ምት ግብ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። 73ኛው ደቂቃ ላይም ምንተስኖት ዮሴፍ በግሩም ሁኔታ ግብጠባቂውን አታሎ በማለፍ ያደረገውን ሙከራ የግቡ የቀኝ ቋሚ ሲመልስበት ኳሱን ያገኘው ክንዴ አብቹ ወደግብ ሲሞክር ራሱ ምንተስኖት ዮሴፍ ኳሱን አቅጣጫ አስቀይሮ መረቡ ላይ አሳርፎታል። ሰበታ ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ 80ኛው ደቂቃ ላይ ዮናስ አቡሌ በግራ መስመር የተገኘውን የማዕዘን ምት ሲያሻማ ያገኘው አስቻለው ታደሠ በግንባሩ ገጭቶ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም የግቡን የቀኝ ቋሚ ታክኮ ወጥቶበታል። 95ኛው ደቂቃ ላይ የሰበታው ይስሃቅ መኩሪያ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወገድ ጨዋታውም በቡታጅራ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ቡታጅራ ከተማ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያውን ሦስት ነጥብ አሳክቷል።

ምድብ \’ለ\’ ጅማ ላይ የአዲስ አበባ እና ነቀምቴ ከተማ ጨዋታን አስተናግዷል። ሁለቱም ቡድኖች ለመሪነት ደረጃ የሚጫወት ቡድን የሚመስል የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ያላሳዩ በተጃጅም ኳሶች ላይ የተመሰረተ ተመጣጣኝ ፉክልር አድርገዋል። የመጀመሪያ ኢላማው የጠበቀ ሙከራ በአዲስ አበባው ዘርዓይ ገ/ስላሴ ሲደረግ በተቀሩት ደቂቃዎች ነቀምቴ ከተማዎች በመስመር ጥቃት የተሻሉ ሆነው ቢታዩም የጎል ዕድል መፍጠር አልቻሉም።

በሁለተኛ አጋማሽ ነቀምቴ ከተማዎች ሙሉ በሙሉ ብልጫ ሲወስዱ አብዛኛው ደቂቃዎች በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ሲጫወቱ ቆይተዋል። በዚህ ብልጫ በቦና ቦካ እና በምኞት ማርቆስ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ችለዋል።

\"\"

አዲስ አበባዎች ከዕረፍት መልስ አንድ ነጥብ ፍለጋ የገቡ በሚመስል የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ከአራት ጊዜ በላይ በመልሶ ማጥቃት ወደ ተቃራኒ ቡድን የሜዳ ላይ መገኘት ሳይችሉ ቀርተዋል። በተገኙበትም እንቅስቃሴም በቀላሉ ኳስ ሲነጠቁ ተስተዋሏል። በዚህ መልኩ ጨዋታው ያለግብ ሲጠናቀቅ አዲስ አበባ ከተማ ወደ መሪነት መጥቷል።

ሮቤ ከተማ እና ደሴ ከተማ በምድብ \’ሐ\’ ሆሳዕና ላይ ተገናኝተዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ በተስሏች ሳይመን የሚመራው የደሴ ከተማ የመሀል ክፍል በኳስ ቁጥጥር ብቻ ሳይሆን ወደ ግብ በመድረስም የተሻሉ ነበሩ። በዚህም ምክንያት በ28ኛው ደቂቃ በማናዬ ፋንቱ አማካኝነት ግብ በማስቆጠር መሪ ሆነዋል። ከግቧ መቆጠር በኋላም በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ስንመለከት አድርገው አጋማሹ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሮቤ ከተማዎች ተጭነው እና ኳስን ተቆጣጥረው በመጫወት 70ኛው ደቂቃ ድረስ ይህን ጫናቸውን ቀጥለዋል። ከ70 ደቂቃ በኋላ ደሴ ከተማዎች የተጫዋች ቅያሪዎችን ሲያደርጉ ይበልጥ በመከፋፈት ለሮቤ ከተማዎች የተሻለ አጋጣሚ የፈጠሩ ሲሆን በ81ኛ ደቂቃ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው የፊት መስመር ተጨዋች የሆነው አብዱልአዚዝ ኦማር ግብ በማስቆጠር ሮቤ ከተማን አቻ አድርጎ ጨዋታው በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል።

የ08፡00 ጨዋታዎች

ባህርዳር ላይ በምድብ \’ሀ\’ ዱራሜ ከተማን ከ ጅማ አባ ቡና ሲያገናኝ ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ጅማ አባ ቡናዎች በመጠኑ የተሻሉ ሲሆን የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን ሁለቱም ቡድኖች ሲቸገሩ ታይቷል። 11ኛው ደቂቃ ላይ የጅማው ብዙዓየሁ እንደሻው ወደ ግብ ሞክሮት የግቡን የቀኝ ቋሚ ታክኮ የወጣው ኳስ የመጀመሪያው ፈታኝ ሙከራ ነበር። በዱራሜዎች በኩል የተሻለው ሙከራ 32ኛው ደቂቃ ላይ ሲደረግ ዳግም ደሳለኝ ከቀኝ የተሻገረለትን ኳስ ቢሞክርም ግብ ጠባቂው ሌሊሣ ታዬ መልሶበታል። በአምስት ደቂቃዎች ልዩነትም ዱራሜዎች ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው በተከላካዩ ሮሆቦት ሳላሎ መክኖባቸዋል።

ከዕረፍት መልስ ዱራሜዎች እጅግ ተሻሽለው በመቅረብ እና ፍጹም የበላይነቱን በመውሰድ በርካታ ሙከራዎችን ማድረግ ሲችሉ በተለይም ኪሩቤል ካሳ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶት ግብጠባቂው የመለሰውን ኳስ ያገኘው አብርሃም አልዲ ያደረገውን ሙከራ ተከላካዩ ሳሙኤል ተሻለ በጥሩ የቦታ አያያዝ አስወጥቶበታል። ያለ ማቋረጥ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን የቀጠሉት ዱራሜዎች 73ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው በወንዱ ፍሬው አማካኝነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ግብ ካስቆጠሩ በኋላም ወደፊት ተጠግተው መጫወት የመረጡት ዱራሜዎች ማራኪ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ 82ኛው ደቂቃ ላይ መሪሁን መንቴ ከቀኝ መስመር ድንቅ ሙከራ አድርጎ የግቡ የላዩ አግዳሚ ሲመልስበት በአንድ ደቂቃ ልዩነትም በመልሶ ማጥቃት የወሰዱትን ኳስ መሪሁን መንቴ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ ሲያሻግር ኳሱን ያገኘው እስራኤል ከበደ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ጨዋታውም በዱራሜ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከምባታ ሺንሽቾ እና አምቦ ከተማን ያገናኘው የምድብ \’ለ\’ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ በግማሽ ሜዳ የበዛ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። አምቦ ከተማዎች በሁሉም በኩል ብልጫ በመውሰድ የበላይ ሲሆኑ በነብዩ ንጉሱ ኃይሌ ክፍሌ ፣ ብሩክ ቸርነት እና በዳሳ ታሪኩ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርገዋል። በከንባታ ሺንሽቾ በኩል ደካማ እንቅስቃሴ የተመለከትን ሲሆን በመልሶ ማጥቃቱም ምንም ዓይነት የጎል ሙከራ መፍጠር ሳይችል ጨዋታው ተጋምሷል።

በሁለተኛ አጋማሽ ቀዳሚ 20 ደቂቃዎች አምቦዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም በማጥቃቱ ተቀዛቅዘው ቆይተው 55ኛው ደቂቃ ላይ በፍራኦል ሪቂታ አማካኝነት ጎል ማግባት ችለዋል። በተቀሩ ደቂቃዎች ግን ወደ መከላከሉ አመዝነዋል። ከምባታ ሺንሺቾዎች ጎል ከተቆጠርባቸው በኋላ ሙሉ ለሙሉ ብልጫ ሲወስዱ ለማጥቃት የመረጡትበት የጫዋታ ሀሳብ በረጅም ኳስ ሲሆን በአምቦ የመከላከል አቅም የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ሊገታ ችሏል። ጨዋታውም በአምቦ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሆሳዕና ላይ ኦሜድላ እና ሶዶ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እንቅስቃሴ የተመለከትን እና በሁለቱም በኩል አንዳቸው በኳስ ቁጥጥር ሲጫወቱ ሌላኛቸው ደግሞ በመልሶ ማጥቃት በመጫወት አና ከቆይታ በኋላ ደግሞ አጨዋወት በመቀያየር ተፋልመዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እንቅስቃሴ የታየበትና በአጨዋወታቸው የአልሸነፍ ባይነት ስሜት የታየበት ሆኖ ግብ እንዳይቆጠርባቸው ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተናል። በተመሳሳይ ሁኔታም ግብ ለማስቆጠር ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ምንም ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው መጠናቀቅ ችሏል።

የ10፡00 ጨዋታዎች

ወልዲያ እና ባቱ ከተማን ባገናኘው የምድብ \’ሀ\’ ጨዋታ መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ አሳዎቹ 11ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። አምበሉ ክንዳለም ፍቃዱ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ተመስገን ቃበቶ በግንባሩ በመግጨት ሲያስቆጥረው 21ኛው ደቂቃ ላይም ኢዩኤል ሳሙኤል ከሳጥን ውጪ ግሩም ሙከራ አድርጎ የግቡን የግራ ቋሚ ታክኮ ወጥቶበታል። እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት ወልዲያዎች 31ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ምቹ አጋጣሚ አግኝተው ነበር። በጥሩ ቅብብል በወሰዱት ኳስ  ከግብ ጠባቂ ጋር የተገናኘው ቢንያም ላንቃሞ ያደረገው ሙከራ የቀኙን ቋሚ ታክኮ ወጥቶበት ትልቅ የግብ ዕድል አባክኗል።

ከዕረፍት መልስ የጁ ፍሬዎች እጅግ ተሻሽለው ሲቀርቡ 58ኛው ደቂቃ ላይ አቻ ሆነዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ቢንያም ላንቃሞ በግንባሩ በመግጨት ያቀበለውን ኳስ ያገኘው አምበሉ አማኑኤል ባርባ ማስቆጠር ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላም እጅግ በጋለ ስሜት ጨዋታውን የተቆጣጠሩት ወልዲያዎች በተደጋጋሚ የተጋጣሚ የግብ ክልል ሲደርሱ 84ኛው ደቂቃ ላይም ማሸነፊያ ግብ አግኝተዋል። ከግራ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት በጋሻው ክንዴ ሲያሻማ ያገኘው ብሩክ ጌታቸው በግንባሩ በመግጨት ማስቆጠር ችሏል። ከመጀመሪያው አጋማሽ ተቀዛቅዘው የቀረቡት ባቱዎች 90ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ፍሬው ዓለማየሁ ከሳጥን አጠገብ ያደረገውን ሙከራ ግብጠባቂው ቴዎድሮስ ጌትነት በግሩም ቅልጥፋና አስወጥቶበታል። ጨዋታውም በወልዲያ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ወልዲያ ከተማ ነጠቡን 25 በማድረስ ከመሪው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሁለት ነጥቦች ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ምድብ \’ለ\’ በይርጋ ጨፌ እና ቦዲቲ ከተማ ጨዋታ 12ኛ ሳምንቱን አጠናቋል። በመጀመሪያው አጋማሽ ቦዲቲዎች የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ በጎል ሙከራዎች የተሻሉ ሲሆኑ የአገኙትን አጋጣሚዎች መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። ይርጋ ጨፌዎች ፈጥነው ወደ ጨዋታ መመለስ ቢፈልጉም በቦዲቲዎች ሲበለጡ የሚያገኙትን ኳስ በመልሶ ማጥቃት ተጫውተዋል። በ45ኛ ደቂቃ ኦኒ ኡጁሉ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በግሩም አጨራረስ በግንባር በመግጨት ጎል ማስቆጠር ሲችል ይርጋ ጨፌዎች የመጀመሪያ አጋማሽ በመሪነት አገባደዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ቦዲቲዎች ተሻሽለው የቀረቡ ሲሆን ኳስ በተጋጣሚ ሜዳ በመጫወት እና በማስጨነቅ የበላይነት ይዘዋል። በሙከራ ደረጃ ብዙ ሙከራዎች ሲያደርጉ በይርጋ ጨፈዎች ተከላካዮች ኳሶች ሲጨናገፍባቸው እና በግብ ጠበቂ ሲመክንባቸው ነበር። እንደሚታወቀው በውድድሩ ውስጥ ታዳጊዎችን በመያዝ የሚታወቁት ቦዲቲዎች ጥሩ እንቅስቃሴ በማሳያታቸው ከተመልካች አድናቆትን ተችረዋል።

\"\"

ይርጋ ጨፌዎች በመከላከሉ መሪነታቸውን አስጠብቀው ለመውጣት ሲንቀሳቀሱ በመልሶ ማጥቃት በተደጋጋሚ አስራ ስድስት ከሃምሳ ውስጥ ሲገኙ የአገኟቸውን አጋጣሚዎች ወደ ጎል የመቀየር ደካማ አጨራረስ ሲያደርጉ ተስተውሏል። ጨዋታውንም አፈግፍገው በመከላከል መሪነታቸው አስጠብቀው ቋጭተዋል።

በሳምንቱ የምድብ \’ሐ\’ የመጨረሻ ጨዋታ ቡራዩ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር ተገናኝተዋል። ፈጣን እንቅስቃሴ ባሳየን ጨቃታ በ28ኛው ደቂቃ ላይ ቡራዩ ከተማዎች ያገኙትን ጥሩ የግብ ዕድል ወደ ጅማ አባ ጅፋር የግብ ክልል ይዘው እየሄዱ ሳለ የጅማ አባ ጅፋሩ ብርሀኑ ደስታ ከፍተኛ ጥፋት በመፈፀሙ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሊወገድ ችሏል። ይህንንም ተከትሎ ጅማ አባ ጅፋሮች ለአንድ ሰዓት ያህል በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት ተገደዋል። ይህንንም ክፍተት ለመሙላት ከፊት መስመር ተጫዋቾች በመቀነስ ጉድለታቸውን ለመሸፈን ችለዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ቡራዩ ከተማዎች ያገኙትን የተጫዋች ብልጫ ለመጠቀም ጫን ብሎ ለመጫወት ሞክረዋል። ጅማ አባ ጅፋሮች በጥንቃቄ በመጫወትና ያገኙትን ዕድል በመልሶ ማጥቃት ለመጠቀም ሲሞክሩ ቆይተዋል። ይህንንም ተከትሎ በ56ኛው ደቂቃ ዋቁማ ደንሳ ግብ አስቆጥሮ ጅማ አባ ጅፋርን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ቡራዩ ከተማዎች ተጭነው መጫወት የቻሉ ቢሆንም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው በጅማ አባ ጅፋር አሸናፊነት ተጠናቋል።