ጎፈሬ ከዩጋንዳ የቅርጫት ኳስ አሶሴሽን ጋር የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት ፈፀመ

👉 \”ብሔራዊ ቡድኖች ላይ ለመስራት የምናስበውን ነገር እንደማስጀመሪያ መንገድ ይጠቅመናል\” አቶ ሳሙኤል መኮንን

👉 \”ጎፈሬ ጥሩ ብራንድ ነው ፤ ጥሩም ምርት አለው። ለዚህም ነው ከጎፈሬ ጋር ለመስራት ውሳኔ ለመስጠት ያልተቸገርነው\” ሚስተር ናስር ሴሩንጆጂ

👉 \”ይህ ስምምነት እንደ ብራንድ ከእግርኳስ ውጪ ሌሎች ስፖርቶች ላይም ተደራሽ ለመሆን እየሰራን መሆኑን ያስመሰከርንበት ነው\” አቶ ሀሰን መሐመድ

ኢትዮጵያዊው የስፖርት ትጥቅ ብራንድ ጎፈሬ ከሀገር ውስጥ ክለቦች ጋር ከመስራት አልፎ ከተለያዩ የአህጉራችን ክለቦች ጋር በትጥቅ አቅርቦት ጉዳዮች ስራዎችን እየሰራ የሚገኝ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከውጪ ሀገር ብሔራዊ ፌዴሬሽን ጋር አብሮ ለመስራት ስምምነት ፈፅሟል። በዚህም ተቋሙ ከዩጋንዳ የቅርጫት ኳስ አሶሴሽን ጋር የፈጠረውን ስምምነት የብዙሃን መገናኛ አባላት በተገኙበት ቦሌ አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ በፊርማ አፅንቷል። በዚህ ሥነ-ስርዓት ላይ የጎፈሬ መስራቾች እንዲሁም ባለቤቶች አቶ ሳሙኤል መኮንን እና አቶ ሀሰን መሐመድ ከዩጋንዳ የቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሚስተር ናስር ሴሩንጆጂ ተገኝተዋል። ሁለቱ አካላት የፊርማ ሥነ-ስርዓቱን ከማድረጋቸው በፊት ስለስምምነቱ ገለፃ አድርገዋል።

\"\"

በቅድሚያም አቶ ሳሙኤል \”የዛሬው የፊርማ ሥነ-ስርዓት በአይነቱ ለየት ያለ ነው። ምክንያቱም ለመጀመሪያ ጊዜ ከብሔራዊ ፌዴሬሽን ጋር ያደረግነው ስምምነት ስለሆነ። ይህ ብቻ ሳይሆን የስፖርት ዘርፉም የቅርጫት ኳስ መሆኑ ለየት ያደርገዋል። ይህንን ስምምነት በመፈፀማችን ታላቅ ደስታ ይሰማናል። በስምምነቱ ውስጥ ሁለታችንንም የሚመለከቱ ግዴታ እና መብቶች አሉ። ይህንን በዝርዝር ከፌዴሬሽኑ ጋር ተነጋግረን ተስማምተናል። ጎፈፌ በፌዴሬሽኑ ስር ለሚገኙ ብሔራዊ ቡድኖች ትጥቆችን ከማቅረቡ በተጨማሪ ከ50 በላይ የሆኑ ቡድኖች የሚሳተፉበት ውድድር ላይም ትጥቆችን ያቀርባል። እንደምታውቁት ዩጋንዳ ውስጥ ከእግርኳስ ቀጥሎ ሁለተኛው ስፖርት ቅርጫት ኳስ ነው። ስለዚህ ብዙ ተመልካች ያለው ስፖርት ስለሆነ ይህ ለእኛ ትልቅ ጥቅም ይሰጣል ፤ ብራንዳችንንም ምስራቅ አፍሪካ ላይም በደንብ ለማስተዋወቅ ይረዳናል። ብሔራዊ ቡድኖች ላይ ለመስራት የምናስበውንም ነገር እንደማስጀመሪያ መንገድ ይጠቅመናል። በአጠቃላይ ይፋዊ የትጥቅ ስፖንሰር በመሆናችን ደስተኞች ነን።\” ብለዋል።

የአቶ ሳሙኤል ባልደረባ አቶ ሀሰን በበኩላቸው ይህ ስምምነት ለጎፈሬ አዲስ ምዕራፍ እንደሆነ በመጥቀስ ንግግራቸውን ጀምረዋል። \”ይህ ስምምነት እንደ ብራንድ ከእግርኳስ ውጪ ሌሎች ስፖርቶች ላይም ተደራሽ ለመሆን እየሰራን መሆኑን ያስመሰከርንበት ነው። ከዚህ በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ በጥራትም ሆነ በዋጋ በደንብ ተወዳዳሪ መሆን እንደምንችል ያስመሰከርንበት ነው። ዩጋንዳ ላይ ያለንን የብራንድ ተፅዕኖም በከፍተኛ ሁኔታ ያንፀባረቅንበት ነው። ይህ ለጎፈሬ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገርም የሚያኮራ ቀን ነው።\” ካሉ በኋላ ጎፈሬ ከምስራቅ አፍሪካ ባሻገር መሐከለኛው አፍሪካ እንዲሁም ከአህጉሩ ውጪ ስራዎችን እየሰራ እንደሆነ አመላክተዋል።

በማስከተል መድረኩን የተረከቡት የዩጋንዳ የቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሚስተር ናስር ሴሩንጆጂ የተሰማቸውን ደስታ በስፍራው ለተገኙ የሚዲያ አካላት ገልፀው \”በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ስር የሚገኙ በርካታ ብሔራዊ ቡድኖች አሉ። በሁለቱም ፆታዎች የሚገኙ ከ16፣ 18 እና 23 ዓመት በታች ቡድኖችን ጨምሮ ዋናው ብሔራዊ ቡድናችን ከዚህ በኋላ ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት የጎፈሬን ምርት የሚጠቀሙ ይሆናል። ጎፈሬ አፍሪካዊ ብራንድ ነው። እኛም አፍሪካዊ እንደመሆናችን ከአፍሪካዊ ብራንድ ጋር ስማችን እንዲገናኝ እንፈልጋለን። ይሄ ለአህጉራችን ትልቅ ነገር ነው። መለያውንም ለብሰን ስናስተዋውቅ የራሳችን እንደሆነ በመረዳት ነው። ጎፈሬ ጥሩ ብራንድ ነው ፤ ጥሩም ምርት አለው። ለዚህም ነው ከጎፈሬ ጋር ለመስራት ውሳኔ ለመስጠት ያልተቸገርነው። ከዚህም መነሻነት ስምምነቱ ረጅም ጊዜ ይጓዛል ብለን እናስባለን።\” በማለት ሀሳባቸውን አጋርተዋል።

\"\"

ለሦስት ዓመት እንደሚቆይ በተገለፀው ስምምነት ጎፈሬ በሁለቱም ፆታዎች ለሚገኙ የእድሜ እርከን እና ዋናው ብሔራዊ ቡድኖች የጉዞ፣ የልምምድ፣ የመጫወቻ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ትጥቆችን ከማቅረቡ በተጨማሪ በብሔራዊ አሶሴሽኑ ስር የሚደረጉ የውስጥ የሊግ ውድድሮች ላይ ለሚሳተፉ ክለቦችም እና ዳኞች ትጥቆችን ይሰጣል። በተጨማሪም አሶሴሽኑ በዓመት እስከ 10 ሺ የሚጠጋ የደጋፊዎች ማሊያ ከጎፈሬ እንደሚወስድም ተመላክቷል። በአጠቃላይ ስምምነቱም ከ70 – 100 ሺ ዶላር እንደሚያወጣ ተጠቁሟል። በመጨረሻም የፊርማ ሥነ-ስርዓቱ ተከናውኖ የትጥቅ ትውውቅ ተደርጎ መርሐ-ግበሩ ተቋጭቷል።