ቅድመ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮጵያ ቡና

የሊጉን መመለስ የሚያበስረው 45ኛው የመዲናይቱን ትልቅ ደርቢ የተመለከተ ቅድመ ዳሰሳ በሚከተለው መልኩ አሰናድተናል።

የሀገራችን ከፍተኛው የሊግ እርከን ውድድር የሆነው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በብሔራዊ ቡድናችን የቻን ዝግጅት እና ውድድር ምክንያት ታኅሣሥ 16 ከ13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በኋላ የተደረጉትን ተስተካካይ ጨዋታዎች አከናውኖ መቋረጡ ይታወቃል። ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ ነገ ሲመለስ ብዙዎች በጉጉት በሚጠብቁት እና በ12ኛ ሳምንት መደረግ በነበረበት የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ነው። በተለምዶ \”የሸገር ደርቢ\” በሚል ስያሜ የሚጠራው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በመዲናው መደረግ ባይችልም በሊጉ የአንድ ከተማ የውድድር ቅርፅ በሌሎች የክልል ስታዲየሞች ሲደረግ ቆይቷል። እርግጥ ነገም ጨዋታው አዲስ አበባ ላይ ባይከወንም ለከተማው ቅርብ በሆነው አዳማ መደረጉ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ በርካታ የክለቦቹ ደጋፊዎች መልካም የሚባል ነው። በነገው ዕለትም ከሜዳ ላይ ፉክክሩ በዘለለ በደጋፊዎች መካከል የሚፈጠረው ድባብ ቀልብን እንደሚስብ ይጠበቃል።

\"\"

ሊጉ ለአንድ ወር ተቋርጦ እንደመምጣቱ ክለቦቹ የሚገኙበትን ወቅታዊ አቋም እያነሱ ሜዳ ላይ ሊኖር ስለሚችለው ፉክክር፣ ጠንካራ እና ደካማ ጎን ማውራት የሚከብድ ነው። እርግጥ በባህር ዳር እና ድሬዳዋ የሊጉ ቆይታ በሁለት የተለያየ በሚመስል መንገድ ሲጓዙ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና በመካከላቸው የስምንት ነጥቦች እና ስድስት ደረጃዎች ልዩነት ቢኖሩም የነገውን ጨዋታ ግለት አያቀዘቅዘውም። እንደገለፅነው ወቅታዊ ብቃታቸውን እንደማመሳከሪያ አንስቶ በጨዋታው ሊፈጠሩ የሚችሉ ነገሮችን መናገር ቢያዳግትም ካላቸው ተቀናቃኝነት አንፃር በሜዳ ላይ የሚኖረው ፉክክር ከፍ እንደሚል ይገመታል።

በመርሐ-ግብር ደረጃ ባለሜዳ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ የነገው ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው 25 ነጥቦችን በመያዝ በደረጃ ሰንጠረዡ በኢትዮጵያ መድን በአንድ ነጥብ ብቻ ተበልጦ ሁለተኛ ሲሆን የነገውን ፍልሚያ ከረታ ረዘም ላሉ የጨዋታ ሳምንታት የነበረበትን መሪነት መልሶ ይረከባል። እስከሁን አንድ ጨዋታ ብቻ የተረታው (በፋሲል ከነማ) ቡድኑ በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ በሊጉ ጠንካራ ነው። ምንም እንኳን ቡድኑ ሊጉን በተከታታይ አራት ጨዋታዎች ድል ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ከዛ በኋላ በተከተሉይ አራት ጨዋታዎች በድምሩ ማግኘት ከሚገባው አስራ ሁለት ነጥብ ሦስቱን ብቻ አሳክቶ መጠነኛ መንገራገጭ ውስጥ ገብቶ ነበር። ከመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ግን በተቃራኒው ሁለት ነጥብ ብቻ በመጣል ዳግም ወደ ነበረበት ጠንካራ አቋሙ ተመልሷል።

በደረጃ ሰንጠረዡ 17 ነጥቦችን በመሰብሰብ አካፋይ ቦታ ላይ የተቀመጠው ኢትዮጵያ ቡና የውድድር ዓመቱ ከመጀመሩ በፊት ጥሩ ዐየር የሚነፍስበት ክለብ ነበር። ከአሠልጣኝ ቅጥር ጀምሮ በርካታ ተጫዋቾችን በማስፈረም ቡድኑን እንደ አዲስ ለማዋቀር ጥሮ የነበረ ቢሆንም ጉዞው ካሰበው እጅግ ባፈነገጠ መንገድ አምርቷል። በዚህም አሠልጣኝ ተመስገን ዳናን በ11ኛ ሳምንት በሀዲያ ሆሳዕና ሲረታ አባሮ በጊዜያዊነት ምክትል አሠልጣኙን ዮሴፍ ተስፋዬ በመንበሩ ሾሟል ፤ ጊዜያዊው አሠልጣኙም ሁለት ጨዋታዎችን አከናውነው በአንዱ ተረተው አንዱን አሸንፈዋል። በአጠቃላይ ክለቡ ካሸነፈው ጨዋታ ቁጥር እኩል አምስት ጨዋታዎችን ተረቶ ከመሪው ኢትዮጵያ መድን በዘጠኝ ነጥቦች ርቆ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። እርግጥ በነገው ጨዋታ ሦስት ነጥቦችን የሚያሳካ ከሆነ ሦስት ደረጃዎችን በማሻሻል አምስተኛ ቦታን ወላይታ ድቻ እሁድ እስኪጫወት ይይዛል።

ፈረሰኞቹ የሊጉን የመጨረሻ ጨዋታ ታኅሣሥ 12 ከለገጣፎ ለገዳዲ ጋር አከናውነው አራት ለባዶ ካሸነፉ በኋላ ለቡድኑ አባላት የሁለት ሳምንት የእረፍት ጊዜ ሰጥተው ነበር። ከጥር 1 ጀምሮ ግን በቢሾፍቱ በመከተም ዝግጅታቸውን ማድረግ ጀምረዋል። በዚህ የዝግጅት ወቅት በሊጉ ለመጨረሻ ጊዜ ከገጠሙት ለገጣፎ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ተጫውተው የነበረ ቢሆንም ሽንፈት አስተናግደዋል። ቡናማዎቹ ደግሞ የመጨረሻ ጨዋታቸውን ታኅሣሥ 15 ከአዳማ ከተማ ጋር አድርገው ሦስት ለምንም ከረቱ በኋላ ለአንድ ሳምንት ለተጫዋቾቻቸው ዕረፍት ሰጥተው ወዲያው የውድድር አጋማሽ የቅድመ ዝግጅታቸውን መከወን ይዘዋል። በዚህ ጊዜም ቡድኑ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከለገጣፎ ለገዳዲ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አድርጎ የነበረ ሲሆን በተመሳሳይ እንደ ነገ ተጋጣሚው ማሸነፍ አልቻለም።

\"\"

በብሔራዊ ቡድን ግዳጅ በርካታ ተጫዋቾችን (ስምንት) አጥቶ የነበረው ጊዮርጊስ ያስመረጣቸው አብዛኞቹ ተጫዋቾችም ግልጋሎት ሲሰጡ የነበረ ስለሆነ በነገው ጨዋታ ላይ ከድካም ጋር ተያይዞ ክፍተት እንዳይፈጠርበት ያሰጋል። በተቃታኒው ሁለት ተጫዋቾችን ብቻ ለብሔራዊ ቡድን ያስመረጠው ቡና ተጫዋቾቹ ከጉዞ ጋር በተያያዘ ካወጡት ጉልበት ውጪ በጨዋታ ስላልተሳተፉ ያን ያህል የሚጎዳ አይመስልም። በሌላ መንገድ ካሰብነው ደግሞ በቀዳሚ አሰላለፍ ውስጥ የሚገቡት የጊዮርጊስ ተጫዋቾች ከልምምድ ባለፈ የነጥብ ጨዋታዎችን ስላደረጉ ከቡና ተጫዋቾች የበለጠ የጨዋታ ሪትም ውስጥ ስላሉ ጥቅም ሊያገኙ ይችላሉ። የሆነው ሆኖ በአጠቃላይ በሁለቱም ቡድን በኩል የሚገኙት አስር ተጫዋቾች በሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ ቡድኖቻቸውን ተቀላቅለው የዛሬውን ጨምሮ አምስት የቡድኖቻቸው የልምምድ መርሐ-ግብር ላይ ተሳትፈዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከላይ እንደገለፅነው የአጥቂ አማካያቸው ዳዊት ተፈራ ከጉዳቱ አገግሞ ልምምድ ቢጀምርላቸውም ለጨዋታ ዝግጁ ስላልሆነ አይጠቀሙትም። ከዳዊት ውጪ ግን ሁሉም የቡድኑ አባላት ለነገው ጨዋታ ዝግጁ እንደሆነ ተጠቁሟል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል የአምበሉ አማኑኤል ዮሐንስ ወደ ሜደ መመለስ መልካም ዜና ነው። ተጫዋቹ በነገው ጨዋታም ከረጅም ጊዜ በኋላ ቡድኑን ያገለግላል ተብሎ ይጠበቃል። ከአማኑኤልም በላይ ከሜዳ ከራቀ የሰነባበተው የመስመር ተከላካዩ አስራት ቱንጆ ግን ከጉዳቱ ማገገም ቀላል አልሆነለትም። ተጫዋቹም ሰርጀሪ እንደሚያስፈልገውና ከቡድኑ ለረጅም ጊዜያት እንደሚርቅ ተሰምቷል። ከእርሱ ውጪ ግን ሌላ የነገው ጨዋታ የሚያመልጠው ተጫዋች የለም።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ 44 ጊዜ ተገናኝተዋል። በእነዚህ ግንኙነቶች ጊዮርጊስ 21 ጊዜ ድል ሲቀናው ቡና ደግሞ 7 ጊዜ አሸንፏል ፤ 16 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል።

– በ44ቱ የሁለቱ ቡድኖች ግንኙነት በድምሩ 88 ጎሎች መረብ ላይ አርፈዋል። 60ውን ግብ በማስቆጠር ፈረሰኞቹ ቀዳሚ ሲሆኑ ቡናማዎቹ ደግሞ 28 ኳሶችን ከመረብ አዋህደዋል።

የነገው ጨዋታ በኢንተርናሽናል አልቢትሮች ይመራል። በዚህም ዋና ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው ከረዳቶቹ ትግል ግዛው እና ፋሲካ የኋላሸት እንዲሁን አራተኛ ዳኛው ለሚ ንጉሴ ጋር በመሆን በጋራ ይመሩታል።