የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አዲስ አበባ ከተማ አጥቂ አስፈርሟል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ ተወዳዳሪው አዲስ አበባ ከተማ ባለልምዷን አጥቂ በዛሬው ዕለት የግሉ አድርጓል።

\"\"

የመጀመሪያውን ዙር የ2015 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ውድድርን በደረጃ ሰንጠረዡ 6ኛ ላይ በ18 ነጥቦች ተቀምጦ ዙሩን ያገባደደው የመዲናይቱ ክለብ አዲስ አበባ ከተማ የካቲት 26 በባህር ዳር ከተማ ለሚጀመረው የሁለተኛው ዙር የሊጉ ጨዋታዎች ራሱን አጠናክሮ ለመቅረብ ጥር 17 የተከፈተውን የሴቶች ፕሪምየር ሊግ የዝውውር መስኮት በመጠቀም አንጋፋዋን የፊት መስመር አጥቂ ረሒማ ዘርጋውን በዛሬው ዕለት ማስፈረሙን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ በላከው መረጃ አመለክቷል።

እግር ኳስን በ90ዎቹ አጋማሽ በተክለኃይማኖት ፔፕሲ ከጀመረች በኋላ በሴንትራል ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ከ2003 ጀምሮ እስከ 2013 ድረስ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለ11 ዓመታት የተጫወተች ሲሆን ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ደግሞ ከክለቡ ጋር ተለያይታ በመቻል ቆይታ በማድረግ አሳልፋለች።

\"\"

የመጀመሪያውን ዙር የሊግ ጨዋታዎች ያለ ክለብ አሳልፋ የሰነበተችው ተጫዋቿ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ለመቀላቀል ብትቃረብም በስተመጨረሻ ግን ከፍተኛ የአጥቂ ክፍተት የሚታይበትን የአሰልጣኝ አብዱራህማን ዑስማንን ክለብ አዲስ አበባ ከተማ በዛሬው ዕለት ተቀላቅላለች።