ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ተጠባቂውን የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታን ይመራሉ

የፊታችን ቅዳሜ ካይሮ ላይ የሚደረገው የአል ሀሊ እና ማሜሎ ዲ ሰንዳውንስ ተጠባቂ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ በኢትዮጵያውያን አራት ዳኞች ይመራል።

\"\"

የ2022/23 የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ሦስተኛ ጨዋታዎች ከነገ ጀምሮ ቀጥለው ይደረጋሉ። በሳምንቱ ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል ቅዳሜ ምሽት 1፡00 ሰዓት ላይ በካይሮው አል ሰላም ስታዲየም በምድብ ሦስት ተደልድለው የሚገኙት አል ሀሊ እና ማሜሎ ዲ ሰንዳውንስ የሚያደርጉትን ተጠባቂ ጨዋታ ባሳለፍነው ሳምንት አንጎላ ላይ ፔትሮ ዲ ሉዋንዳ ከ ጄኤስ ካቢሊዬ ያደረጉትን ጨዋታ መርተው የነበሩት ኢትዮጵያዊያን አራት አለም አቀፍ ዳኞች በዚህም ሳምንት ይህን ጨዋታ በተመሳሳይ እንዲመሩ ስለ መመረጣቸው ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት በአምላክ ተሰማ የመምራት ሀላፊነቱን ሲወስድ ትግል ግዛው እና ተመስገን ሳሙኤል ረዳቶች እንዲሁም ቴዎድሮስ ምትኩ በበኩሉ አራተኛ ዳኛ በመሆን በጣምራ ጨዋታውን ይመሩታል።

\"\"

ሁለቱ ቡድኖች ባለፉት አምስት ግንኙነታቸው ሰንዳውንስ ሁለት ጊዜ አልሀሊ ደግሞ አንድ ጊዜ ድል ሲቀናቸው በአንዱ አቻ ተለያይተዋል። የአቡበከር ናስሩ ክለብ ሰንዳውንስ ምድብ ሦስትን በ6 ነጥቦች ሲመራ የሱዳኑ አል ሂላል በ3 እንዲሁም የግብፁ አል ሀሊ እና የካሜሮኑ ኮተን ስፖርት በበኩላቸው ያለ ምንም ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ ከአንድ እስከ አራተኛ ተቀምጠዋል።