ሪፖርት | አዞዎቹ እና ኃይቆቹ ነጥብ ተጋርተዋል

የ15ኛ ሣምንት የመጀመሪያ መርሐ-ግብር የሆነው እና ቀዝቃዛ ፉክክር የታየበት የአርባምንጭ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ 1ለ1 ተጠናቋል።

10፡00 ላይ በ15ኛ ሣምንት የመጀመሪያ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ ሲገናኙ አዞዎቹ ድሬዳዋ ከተማን 3-1 ሲያሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ በአምስት ቢጫ ካርዶች አንድ ጨዋታ የተቀጣውን ሱራፌል ዳንኤልን በወርቅይታደስ አበበ ሲተኩ ኃይቆቹ በበኩላቸው ከባህርዳር ከተማ ጋር 1-1 ከተለያዩበት አሰላለፍ የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ፀጋአብ ዮሐንስ ፣ ዳንኤል ደርቤ ፣ በረከት ሳሙኤል ፣ አዲሱ አቱላ እና አሊ ሱሌይማን ወጥተው በምትካቸው ሠዒድ ሀሰን ፣ አቤኔዜር ኦቴ ፣ ዳዊት ታደሰ ፣ በቃሉ ገነነ እና ኢዮብ ዓለማየሁ ገብተዋል።

\"\"

ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በማሳያት ጅማሮውን ያደረገው ጨዋታ 8ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ተቆጥሮበታል። ወርቅይታደስ አበበ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ተመስገን ደረሰ በሁለት ተከላካዮች  መሀል ሾልኮ ገብቶ በግንባሩ ገጭቶ መረቡ ላይ በማሳረፍ አርባምንጭን መሪ ማድረግ ችሏል።

መሀል ሜዳው ላይ መጠነኛ ብልጫ የተወሰደባቸው ሀዋሳዎች አቻ ለመሆን ብዙም አልቆዩም ነበር። 20ኛው ደቂቃ ላይ አዞዎቹ ላስቆጠሩት ግብ ቁልፍ መነሻ የነበረው ወርቅይታደስ አበበ ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ሙጅብ ቃሲም ማስቆጠር ችሏል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ አህመድ ሁሴን እና ተመስገን ደረሰን መሠረት ያደረጉ ተሻጋሪ ኳሶች በመጠቀም የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩት አርባምንጮች 39ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ሙና በቀለ ከቀኝ መስመር ለአህመድ ሁሴን ያሻገረው ኳስ አቅጣጫ ቀይሮ መረቡ ላይ ያርፋል ተብሎ ሲጠበቅ የግቡን  አግዳሚ ገጭቶ ተመልሶበታል።

በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ የተወሰደባቸው ኃይቆቹ በረጃጅም ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም ያን ያህል ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳያደርጉ ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።

ጨዋታው ከዕረፍት መልስ በሚቆራረጡ ቅብብሎች ተቀዛቅዞ ሲቀጥል አርባምንጭ ከተማዎች በአንጻራዊነት የተሻሉ ነበሩ። ሆኖም ጨዋታው በሁለቱም በኩል ደካማ እንቅስቃሴ አሳይቶ 1-1 ተጠናቋል።

\"\"