የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሪነቱን አጠናክሯል

ዛሬ በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 14ኛ ሳምንት አዲስ አበባ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጋጣሚዎቻቸውን ሲያሸንፉ ቦሌ እና ኤሌክትሪክ ነጥብ ተጋርተዋል።

አዳማ ከተማ 0-1 አዲስ አበባ ከተማ

ጥሩ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ አዳማዎች ብልጫውን ሲወስዱ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን አዲስ አበባዎች የተሻሉ ነበሩ። የአዲስ አበባዋ ቤተልሔም መንተሎ 15ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር የተሻማው የማዕዘን ምት ሲመለስ አግኝታው ከሳጥን ውጪ ያደረገችው ሙከራም የመጀመሪያው የተሻለ የግብ ሙከራ ነበር። ከኳስ ውጪ ደካማ የነበሩት እና በሚያገኙት ኳስ ግን ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉት አዲስ አበባዎች 38ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ረሂማ ዘርጋው ከረጅም ርቀት እየገፋች የወሰደችውን ኳስ በተረጋጋ አጨራረስ በግራ እግሯ መረቡ ላይ አሳርፋዋለች።

ከዕረፍት መልስ በማራኪ የኳስ ቅብብል ከተመልካቾች አድናቆት የተቸራቸው አዳማዎች በተሻለ ሁኔታ በተለይም በግራው የማጥቂያ መስመራቸው ከሳባ ኃ/ሚካኤል በሚነሱ ኳሶች የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሲጀምሩ 82ኛው ደቂቃ ላይ ራሷ ሳባ በግራ መስመር ከሳጥን አጠገብ ያደረገችው ግሩም ሙከራ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ተመልሶባታል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነትም ተቀይራ የገባችው ቤተል ጢባ በግንባሯ ገጭታ ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ ስርጉት ተስፋዬ መልሳባታለች። ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት በቀጥተኛ ኳስ መጫወትን የመረጡት አዲስ አበባዎች ጨዋታውን በማረጋጋት ውጤታቸውን አስጠብቀው 1-0 መርታት ችለዋል።

ቦሌ ክ/ከተማ 1-1 ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ለተመልካች እጅግ ሳቢ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ ቦሌዎች በኳስ ቁጥጥሩም ይሁን የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ብልጫውን ወስደዋል።

\"\"

6ኛው ደቂቃ ላይም ንግሥት በቀለ ከቀኝ መስመር ያሻገረችውና ስንታየሁ ኢርኮ ኃይል አሳነሳ በሞከረችው ኳስ የመጀመሪያውን የግብ ዕድል ሲፈጥሩ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ትርሲት ወንደሰን ከረጅም ርቀት ከተገኘ ቅጣት ምት ያደረገችው ሙከራ የግብጠባቂዋ የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ተጨምሮበት መረቡ ላይ ያርፋል ተብሎ ሲጠበቅ የግቡን የግራ ቋሚ ገጭቶ ተመልሷል።

ከራሳቸው የግብ ክልል ለመውጣት እጅግ የተቸገሩት ኤሌክትሪኮች 23ኛው ደቂቃ ላይ ከራሳቸው የግብ ክልል ውስጥ በሠሩት ስህተትም በስንታየሁ ኢርኮ ግብ ተቆጥሮባቸዋል። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላም በተወሰነ መነቃቃት ወደፊት ለመጠጋት ሲሞክሩ 42ኛው ደቂቃ በሕይወት ዳንጊሶ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ የግቡን የላይ አግዳሚ ተጠግቶ የወጣ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በሚያገኙት ኳስ ሁሉ በስኬታማ ቅብብሎች የታጀበ የማጥቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ከተመልካች ከፍተኛ አድርቆት የተቸራቸው ቦሌዎች 45ኛው ደቂቃ ላይም በንግሥት በቀለ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር።

ከዕረፍት መልስ እጅግ ተሻሽለው በመቅረብ ጨዋታውን የተቆጣጠሩት ኤሌክትሪኮች 66ኛው ደቂቃ ላይ አቻ መሆን ችለዋል። ቤተልሔም አስረሳኸኝ በግራ መስመር ከረጅም ርቀት በውድድሩ ከታዩ ድንቅ ግቦች አንዱ የሆነ ግብ አስቆጥራለች። በሁለተኛው አጋማሽ አቅማቸውን በመጨረስ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ለመጫወት የተገደዱት ቦሌዎች የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ 80ኛው ደቂቃ ላይ የኤሌክትሪኳ ሕይወት ደንጊሶ ከረጅም ርቀት የሞከረችው እና ግብ ጠባቂዋ የያዘችው ኳስ የጨዋታው የመጨረሻ ትዕይንት ሆኖ ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል።

ሀዋሳ ከተማ 1-2 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ በተደረገው ተጠባቂ ጨዋታ መጠነኛ ፉክክር በማሳየት ሲጀምር በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በርካታ የግብ ዕድል መፍጠር የቻሉት ንግድ ባንኮች 8ኛው ደቂቃ ላይ በእመቤት አዲሱ አማካኝነት የመጀመሪያውን የተሻለ ሙከራ ከሳጥን ውጪ አድርገዋል።

\"\"

በቁጥር በዝተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ ሲችሉም 14ኛው ደቂቃ ላይ ሰናይት ቦጋለ ከሳጥን አጠገብ ባስቆጠረችው ግሩም ግብ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ከራሳቸው የግብ ክልል ወጥተው የግብ ዕድል ለመፍጠር የተቸገሩት ሀዋሳዎች በአቋቋም ስህተት 23ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። አረጋሽ ካልሳ በድንቅ ዕይታ አመቻችታ ባቀበለቻት ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር የተገናኘችው አርያት ኦዶንግ ሳትጠቀምበት ቀርታ ትልቅ የግብ ዕድል አባክናለች።

ቀስ በቀስ የጨዋታውን ሚዛን ወደ ራሳቸው እየደፉ የመጡት ሀዋሳዎች በጠንካራ የማጥቃት እንቅስቃሴ 38ኛው ደቂቃ ላይ አቻ ሆነዋል። ረድኤት አስረሳኸኝ ከግራ መስመር ያሻገረችውን ኳስ ያገኘችው እሙሽ ዳንኤል በግሩም ፍጥነት በግንባሯ ገጭታ መረቡ ላይ አሳርፋዋለች።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል ንግድ ባንኮች 57ኛው ደቂቃ ላይ በዕረፍት ተቀይራ የገባችው መዲና ዐወል ባስቆጠረችው ግብ በድጋሚ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ሀዋሳዎች ዙፋን ደፈርሻ ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ከፈጠረችው የግብ ዕድል ውጪ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ሲቸገሩ 83ኛው ደቂቃ ላይ ግን ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ረድኤት አስረሳኸኝ ከቅጣት ምት ያደረገችው ግሩም ሙከራ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ተመልሶባታል።

ሎዛ አበራ 77ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ካደረገችውና ግብ ጠባቂዋ ፍሬወይኒ ገብሩ ከያዘችባት ኳስ ውጪ ንፁህ የግብ ዕድል በመፍጠሩ በኩል እየተዳከሙ የሄዱት ንግድ ባንኮች ጨዋታውን በማቀዛቀዝ እና ሰዓት በመግደል የግብ ብልጫቸውን አስጠብቀው ወጥተዋል። ውጤቱን ተከትሎም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነጥቡን 32 በማድረስ ከተከታዩ ኤሌክትሪክ በሦስት ነጥብ ከፍ ብሎ በመሪነቱ ቀጥሏል።