መረጃዎች | 64ኛ የጨዋታ ቀን

በ16ኛው ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ቀን ነገ የሚስተናገዱትን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።

ለገጣፎ ለገዳዲ ከ ሀዋሳ ከተማ

በመጀመሪያው ዙር ያልተጠበቀ ውጤት ካስተናገዱ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የነበረው የለገጣፎ ለገዳዲ እና የሀዋሳ ከተማ ግንኙነት ነገ በሁለተኛው ዙር የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ይሆናል።

16ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ለገጣፎ ለገዳዲ በመቻሉ ጨዋታ በፎርፌ ካጣቸው ሦስት ነጥቦች በኋላ አዳዲስ ተጫዋቾቹን እንደሚያሰልፍ በሚጠበቅበት ጨዋታ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ይገመታል። ሶከር ኢትዮጵያ ማምሻውን ከክለቡ ባገኘችው መረጃ መሰረት ቡድኑ የነገውን ጨዋታ ማድረጉ ሙሉ ለሙሉ የተረጋገጠ ጉዳይ አይመስልም። ይልቁኑም የክለቡ የቦርድ አመራሮች ነገ ረፋድ በሚያደርጉት ስብስባ ለገጣፎ የተሰጠበትን የፎርፌ ውጤት ተከትሎ ቀጣዩን የሀዋሳ ጨዋታ ስለማከናወኑ እንደሚረጋገጥ ይጠበቃል። ሁለት የውጪ ዜጎች እና ስድስት የሀገር ውስጥ ተጫዋቾችን ዝውውር የፈፀመው ክለቡ በአሰልጣኝ ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስ እየተመራ በሁለተኛው ዙር ከመጀመሪያው የተለየ የቡድን አደረጃጀት ይዞ እንደሚመለስ ይታሰባል።

\"\"

በሰንጠረዡ አጋማሽ ላይ ረግቶ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ በሚፈልገው ወቅታዊ አቋም ላይ የሚገኝ አይመስልም። ከሦስት ተከታታይ የ1-1 ውጤቶች በኋላ ወደዚህ ጨዋታ የሚመጣው ቡድኑ ግብ የማስቆጠር አቅሙ አሁንም ጥያቄ ውስጥ ይገኛል። ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች አራት ጊዜ ብቻ ኳስ እና መረብን ያገናኙት ኃይቆቹ እነዚህን ጎሎች በሙሉ ያገኙት ከአጥቂዎቻቸው ቢሆንም እንደቡድን ያላቸው የግብ ፊት አፈፃፀም አሳሳቢ የሚባል ነው። ቡድኑ ነገ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ከሚገኝ ቡድን ጋር እንደመጫወቱ ይህንን ደካማ ሪከርድ በፊት አጥቂዎቹም ሆነ በቀሪ ተሰላፊዎች ግቦች አሸንፎ ከግብ ጋር ያለውን ግንኙነት ማደስ ዋነኛው ዓላማው ይሆናል ማለት ይቻላል። ሀዋሳ በግል ጉዳይ ከሚያጣው ዳንኤል ደርቤ በቀር ቀሪው ስብስቡ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆኑ ታውቋል።

አንድ የእርስ በርስ ግንኙነት ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ በመጀመሪያው ሳምንት የተገናኙበት ጨዋታ በለገጣፎ ለገዳዲ 2-1 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ነበር።

ጨዋታውን ዳንኤል ግርማይ በመሀል ዳኝነት ሲመራው ሻረው ጌታቸው እና ሸዋንግዛው ይልማ በረዳትነት ሔኖክ አክሊሉ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ወላይታ ድቻ

በአንድ ነጥብ ልዩነት በሰንጠረዡ አጋማሽ ላይ የሚገኙት ቡና እና ድቻ የሁለተኛ ዙር ጉዟቸውን ቀደሚ ጨዋታ ምሽት ላይ ያከናውናሉ።

ከመጨረሻው የአዳማ ከተማ ድል በኋላ ሦስት ዘጠና ደቂቃዎችን ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው መውጣት ያልቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ ላይኛው ፉክክር መቅረብ ቀላል አልሆነላቸውም። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በተመሳሳይ የመጀመሪያ ተጫዋቾች ምርጫ ወደ ሜዳ የገባው የአሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ ቡድን አሁንም በስብስቡ ውስጥ ያሉ ተጫዋቾችን የቀደመ ብቃት መልሶ ለማግኘት የተቸገረ ይመስላል። ቡድኑ ወደ ግብ የሚደርስባቸውን የንክኪዎች ቁጥር ከወትሮው ቀነስ አድርጎ በቶሎ ተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ የሚደርስበት አኳኋን ተገማችነቱን በመቀነስ ጥንካሬን ሲያላብሰው ይታያል። ሆኖም የፊት መስመር ተሰላፊዎቹ ስልነት ወጥነትን አለመላበሱ ዕድሎችን እንዲያመክን እያደረገው ይገኛል ። በእርግጥ በነገው ጨዋታ ከኳስ ጋር ብዙ ጊዜ ሊኖረው እንደሚችል እና የግብ ዕድሎቹ ከብዙ ንክኪዎችም ጭምር እንደሚመጡ ቢገመትም በአንፃሩ በፋሲል ከነማው ጨዋታ የታየበት ደካማ የቆመ ኳስ መከላከል ሂደቱ ከነገ ተጋጣሚው አንፃር ሊሻሻል የሚገባው ሌላው ድክመት ሆኖ ይነሳል።

\"\"

ወላይታ ድቻ በእስካሁኑ ጉዞው የመከላከል ጥንካሬው ከደካማ አጀማመሩ ቀና እንዲል የረዳው ይመስላል።13 ግቦች ብቻ በተቆጠሩበት የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ውስጥ ደግሞ እየጎላ የመጣው ቢኒያም ገነቱን ማንሳት ተገቢ ነው። የሶከር ኢትዮጵያ የ15ኛ ሳምንት ምርጥ የግብ ዘብ የነበረው ቢኒያም ጠንካራ ሙከራዎችን በማምከኑ የቀጠለ ሲሆን በነገውም ጨዋታ ለአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም ቡድን ወሳኝ እንደሚሆን ይጠበቃል። በአንፃሩ የሊጉ ሁለተኛ ደካማ የማጥቃት ቁጥር ያለው ወላይታ ድቻ የፊት መስመሩን ብቃት ማሻሻል ዋነኛ የቤት ሥራው ይመስላል። ቡድኑ በመጨረሻው ጨዋታ በአመዛኙ የተንፀባረቀበት ቀጥተኛነት ነገም እንደሚደገም ሲጠበቅ የማጥቃት ሽግግር ጥራቱን ማሻሻል እና የስንታየሁ መንግሥቱን ተፅዕኖ መልሶ ማግኘት ያስፈልገዋል።

ምሽት ላይ በሚደረግው በዚህ ጨዋታ ወላይታ ድቻ ተከላካዮቹ አንተነህ ጉግሳ እና ደጉ ደበበ እንዲሁም አማካዩ በኃይሉ ተሻገር በጉዳት ምክንያት ከስብስቡ ውጪ ሆነውበታል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል ግን ከአስራት ቱንጆ ውጪ ቀሪው ስብስብ ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑ ታውቋል።

በ17 ጊዜ የክለቦቹ የቀደመ ግንኙነት 8 የአቻ ውጤቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይዘዋል። ወላይታ ድቻ አምስቱን ሲረታ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ አራቱን አሸንፏል። በእነዚህ 15 ጨዋታዎች አጠቃላይ 26 ጎሎች ሲቆጠሩ ቡድኖቹ እኩል 13 13 ግብ በስማቸው አስመዝግበዋል።

ኤፍሬም ደበሌ በዋና ዳኝነት በሚመራው ጨዋታ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ እና አማን ሞላ ረዳቶች ፣ ተፈሪ አለባቸው ደግሞ የአራተኛ ዳኝነት ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።