\”የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኳስ መጫወት የሚፈልግ እንደሆነ አይተናል። ቡድኑን እናከብራለን ፤ ከጨዋታዎቹም ነጥቦችን ለማግኘት እንሞክራለን\” አሠልጣኝ ካባ ዲያዋራ

የጊኒ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ካባ ዲያዋራ ከወሳኙ ጨዋታ በፊት የሰጡትን አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበናል።

\"\"

ስላደረጉት ዝግጅት…

ለጨዋታዎቹ ዝግጅት የተሰባሰብነው እሁድ እና ሰኞ ነው። የዝግጅት ጊዜው በጣም አጭር ነው። ለሁለቱም ጨዋታዎች ያለውን ቀን እኛም ሆነ ኢትዮጵያ መላመድ አለብን። እኛ ሁሉም ተጫዋቾች ተሰባስበው ልምምድ ማድረግ የጀመርነው ማክሰኞው ነው። አብዛኞቹ ተጫዋቾች ቅዳሜ እና እሁድ በክለብ ደረጃ ጨዋታ ሲያደርጉ ስለነበር ሰኞ ነው በተሟላ ሁኔታ የተቀላቀሉን። ከዓርቡ ጨዋታ በፊት ሦስት ቀናት ከዛ በኋላ ደግሞ ለሰኞው ጨዋታ ሁለት ቀናት ብቻ ነው የሚኖሩን።

ስለተጋጣሚያቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን…

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን እናከብራለን። ከቀናት በፊት ከሩዋንዳ ጋር ያደረጉትንና አንድ ለምንም የረቱትን የአቋም መፈተሻ ጨዋታም አይተናል። ከዚህ ጨዋታ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ጨዋታዎችም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኳስ መጫወት የሚፈልግ እንደሆነ አይተናል። በአጠቃላይ ቡድኑን እናከብራለን ፤ ከጨዋታዎቹም ነጥቦችን ለማግኘት እንሞክራለን።

\"\"

ከሜዳቸው ውጪ ስለመጫወታቸው…

ከሜዳችን ውጪ መጫወታችም ምንም ጥያቄ የለውም ፈታኝ ነው። በሜዳችን ብንጫወት ኖሮ እነዛን ለብሔራዊ ቡድናቸው ሙሉ 90 ደቂቃ የሚደግፉ ደጋፊዎችን እናገኝ ነበር። ይህ አልሆነም። በዚሁ አጋጣሚ ግን ኢትዮጵያን ማመስገን እንፈልጋለን። ምክንያቱም እኛ እዚህ መጫወት ስንመርጥ እነርሱም እዚሁ መጥተዋል። በዚህ ምክንያት ለሁለተኛው ጨዋታ ወደ ሌሎች ሀገሮች መጓዝ አላስፈለገንም። የሆነው ሆኖ ያለውን ነገር መቀበል ነው ያለብን። ከሜዳችን ውጪ ብንጫወትም ጨዋታውን ለማሸነፍ እንጥራለን።