አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከጨዋታው በኋላ ምን አሉ?

👉\”ከዓርቡ ጨዋታ ዛሬ አቀራረባችን የተሻለ ነበር ማለት እችላለው\”

👉\”ከእኔ በብዙ እጥፍ አቅም ያለው ሰው በዚህ ቦታ ላይ ቢቀመጥ ያሉት እነዚሁ ተጫዋቾች ናቸው\”

👉\”…እኛ ካልቻልን ደግሞ የሚችል አካል በቅርብ ጊዜ ወደዛ እንዲመለስ ያደርገዋል ብዬ አስባለው\”


👉\”ለአፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ ያለን ዕድል በጣም ጠባብ ነው\”

ስለጨዋታው….

የመጀመሪያውን ጨዋታ ከመሸነፋችን ጋር ተያይዞ ትንሽ ከዐምሮ ጋር በተገናኘ የሥነ-ልቦና ትግል ተጫዋቾቹ ጋር ነበረን። ከዓርቡ ጨዋታ ዛሬ አቀራረባችን የተሻለ ነበር ማለት እችላለው። ጎሎች ያስተናገድንበት መንገድ ምናልባት ቶሎ ከሪትም እንድንወጣ አደረገን እንጂ በአብዛኛው የጨዋታ ክፍል የተሻለ ለመንቀሳቀስ ሞክረናል።

ቡድኑ ከዓርቡ ጨዋታ ተሻለ ስለተባለበት መንገድ…

በዓርቡ ጨዋታ ባልተለመደ መልኩ ቡድናችን ከምንፈልገው መንገድ ውጪ ነበር። ይሄ ደግሞ ጊኒዎች እንደልባቸው እና እንደፈለጉ በተደጋጋሚ እንዲያጠቁና ብዙ የጎል ዕድል እንዲፈጥሩ አድርጓል ፤ ጨራሽ አልነበሩም እንጂ ካስቆጠሩት የበለጠ ማስቆጠሩት የሚችሉበት ፐርፎርማንስ ነው ያደረጉት። እኛ በተቃራኒው ጥሩ አልነበርንም ነበር። ዛሬ እኛ ከባለፈው ጨዋታ አንፃር በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ወደ ጎል በመድረስ ረገድ የተሻልን ነበርን። በእነሱ በኩል በተለይ በሽግግር የሚመጡ ኳሶችን በመጨረሱ በኩል ክሊኒካል ነበሩ። ይሄ ነገር ውጤቱን ይዘን እንዳንወጣ እንቅፍት ሆነን እንጂ ቡድኑ ላይ ባልኩት መስፈርቶች ጥሩ ነገር ነበር ማለት እችላለው።

\"\"

ወደሞሮኮ ሲመጡ አቅደውት ስለነበረው ውጤት…

አፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመካፈል የምንፈልግ ከሆነ ውጤት መያዝ አለብን። ማክሲመም ነጥቡ ደግሞ ሁለቱን ጨዋታዎች ማሸነፍ ነበር ፤ ይህ አልሆነም። ለዚህ ግን እንደ መሠረታዊ ነገር አድርጌ የምቆጥረው የመጀመሪያውን ጨዋታ በምንፈልገው መንገድ አለመቆጣጠራችን ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥሮብናል። ለአፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ ያለን ዕድል በጣም ጠባብ ነው። በእኛ ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ላይም የተመሰረተ እንዲሆን አድርጎታል። ከውድድር አንፀቀር አስቸጋሪ ነገር ውስጥ ነው ያለነው። እርግጥ 100% የማለፍ ዕድላችን አክትሟል ማለት አይቻልም። በሂሳባዊ ስሌት ሙሉ ለሙሉ ውጪ አይደለንም ፤ ግን ዕድሉ የጠበበ ነው።

ስለአጥቂ…

እንደ ሀገር የ9 ቁጥር ተጫዋች የለንም። የትኛው ሰፊ አማራጭ አለን ብለን መጠየቅ አለብን። የምናየው ከሀገር ውስጥ አንፃር ነው። የ9 ቁጥር ጉዳይ ግብ ካለማስቆጠራችን እና ከመሸነፋችን ጋር የሚያያዝ አይደለም። በዓርቡ ጨዋታ ሙሉ ለሙሉ ጨዋታን ከመቆጣጠር ጋር ከዕቅዳችን ውጪ ነበርን። ከጎል ጋር ተያይዞ ግን በርካታ ተጫዋቾች ጎል ጋር እየደረሱ እና የግብ ዕድሎችን እየፈጠሩ ነው። 9 ቁጥር ኖሮም ያለ 9 ቁጥር መጫወትን ልንመርጥም እንችላለን። ለጊዜው ግን 9 ቁጥር ሆኖ በዛ ቦታ ልብ የሚያስደፍር ተጫዋች የለንም። አንዳንዴ ማነፃፀር ይገባናል። ለራሳችን የምንሰጠውም ግምት የተሳሳተ ይመስለኛል። ሜዳ ላይ የእነሱን ተጫዋቾች ተመልከቱ! ይሄንን ለሰበብ ለማቅረብ አይደለም። ከጥራት አንፃር እንደ ሀገር መስራት አለብን። ባለን ነገር የምንችለውን ለመታገል ሞክረናል።

ከግብፁ ጨዋታ በኋላ በጊኒ በተከታታይ ስለመሸነፋቸው…

የግብፁ ጨዋታ እና የጊኒው ጨዋታ የተለየ ነው። በግብፁ ጨዋታ በብዙ ነገር የተሻለ ነበርን። በተለይ ከፊትም ያገኘነውን ዕድል በሚገባ ተጠቅመናል። ከኳስ ቁጥጥር ጀምሮ በብዙ ነገሮች ጥሩ ነበርን። አሁን ያለው ቡድን ውስጥ አራት እና አምስት ተጫዋቾች የሉም። በተጫዋች ብቃትም በጉዳት ምክንያት አብረውን የሉም። የግብፁ ብቻ ሳይሆን የዓርቡ እና የዛሬው ጨዋታም ይለያያል። ዛሬ ከዓርቡ ጨዋታ በተሻለ ተጫውተናል ፤ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ግን ተሸንፈናል።

\"\"

ስለቡድኑ ወጥነት…

ብሔራዊ ቡድን በተለይ እንደእኛ አይነት ብሔራዊ ቡድን በወጥነት ለረጅም ጊዜ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ማግኘት ከባድ ነው። ከግብፁ ጨዋታ በኋላ እንኳን የተወሰነ የተጫዋች ልዩነት አለ። በወጥነት የሚጫወቱ ተጫዋቾችንም ማግኘት አንዱ ክፍተት ነው። እንደ ሌሎች ቡድኖች በወጥነት አምስት እና ስድስት ዓመት የሚጫወቱ ተጫዋቾችን እያገኘን ነው ወይ የሚለው ላይ እውነታው የሚያሳየው ያንን አይመስለኝም።

ዞሮ ዞሮ የፈለከው አይነት አቅም ቢኖርህ ፤ ከእኔ በብዙ እጥፍ አቅም ያለው ሰው በዚህ ቦታ ላይ ቢቀመጥ ያሉት እነዚሁ ተጫዋቾች ናቸው። ጥራት ያላቸው ተጫዋቾችን የማፍራት ስራ ላይ እንደ ሀገር መትጋት ያለብን ይመስለኛል ፤ ባለው ነገር ግን የምንችለውን ነገር ለማሳየት ሞክረናል።

ወደአፍሪካ ዋንጫ ስለማለፍ…

ፍላጎታችን ቀጣይ አፍሪካ ዋንጫ ላይ መገኘት ነው። በፍላጎት ደረጃ ይሄ ነው። በነጥብ ደረጃ ግን ይሄንን የሚያመላክት ነገር አይደለም እያየን ያለነው። ያ እንዳይርቅ መስራት ነው ያለብን። ምክንያቱም ኢትዮጵያ በየሁለት ዓመቱ አፍሪካ ዋንጫ ላይ ስትገኝ የነበረች ሀገር እንዳልሆነች ሁላችንም እናውቃለን። ስለዚህ ያ የራቀውን ነገር ለማሳጠር መሞከር ነው። እኛ ካልቻልን ደግሞ የሚችል አካል በቅርብ ጊዜ ወደዛ እንዲመለስ ያደርገዋል ብዬ አስባለው።