አቶ ባህሩ የኢትዮጵያ እና ሞሮኮን እግርኳሳዊ ግንኙነት በተመለከተ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል

👉\”እነሱን ላመሰግንበት የምችልበት ምንም ቃል የለኝም። ለሁሉም ግን ላደረጉልን ነገር ሁሉ ከልብ እናመሰግናለን\”

👉\”እኛ ጥሩ ተማሪ ነን ፤ ከእነሱ ብዙ የምንወስዳቸው ነገሮች አሉ\”

👉\”…ምናለ አዲስ አበባ እና ሌሎች የሀገራችን ከተሞች እንደዚህ ሆነው ባያቸው ብለህ ታስባለህ\”

👉\”ሁሌ ተደጋፊ እና ሁሌ እርዳታ አግኚ የሚል ስሜትም እንዳይፈጠር ደግሞ እኛም በአጭር ጊዜ ውስጥ ራሳችንን አውጥተን እግርኳሳችንን ማሳደግ የቤት ስራችን ነው\”

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከሞሮኮ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል?ስምምነቱ ምን ዓይነት ነገሮች ላይ መሠረት አድርጓል?

\”የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከሞሮኮ እግርኳስ ማኅበር ጋር ግንኙነቱን በደንብ አጠናክሮ የጀመረው ክቡር ፕሬዝዳንታችን ለሁለተኛ ጊዜ ተመርጠው ወደ ፌዴሬሽናችን ከመጡ በኋላ ምታስታወሱ ከሆነ በተመረጡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሞሮኮ በመምጣት ነው የተለያዩ ስምምነቶችን ከሞሮኮ እግርኳስ ማኅበር ጋር ያደረጉት። ይህ ስምምነት በውስጡ ብዙ ነገሮችን ይይዛል ፤ አንደኛ ከአሰልጣኞች ስልጠና ጋር በተያያዘ በተለይም አሁን ሞሮኮ ካለችበት የእግርኳስ ደረጃ አንጻር እና አሁን ካላቸው የተሻለ ተሞክሮ መማር የምንችልባቸው ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የተለያዩ አሰልጣኞችን በማምጣት ስልጠና እንዲያገኙ ከማድረግ ጋር በተያያዘ በአሰልጣኝነት ትምህርቱ ላይ እንደዚሁ ስምምነት አለን። ከዛ በተጨማሪም ከሞሮኮ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር የወዳጅነት ጨዋታዎችን በተለያዩ የዕድሜ ደረጃ ከሚገኙ ቡድኖች ጋር የማድረግ ዕድል ይኖረናል። አሁን ላይ እንደምትመለከተው ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የምንፈልጋቸውን ነገሮች ከነሱ ጋር በመነጋገር ሊያግዙን ሁሌም ዝግጁ ናቸው። ባለፈውም ብሔራዊ ቡድናችን ለቻን ዝግጅት ያደረገው በወቅቱ ከነበረን ውይይት በኋላ ነው። በተለይም ደግሞ ከስምምነቱ ውጪ ባሉ ሂደቶችም ክቡር ፕሬዝዳንታችን በሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች መሠረት የሞሮኮ እግርኳስ ፌዴሬሽን ተቀባይነት እያገኘ ነው። በሁሉ ነገር እያገዙን ነው የሚገኙት። ሌላኛው ከመሠረተ ልማት ጋር በተያያዘ ከእነሱ ጋር ያለውን ልምድ ከመጋራት ጋር ተያይዞ ምንድነው ከነሱ ጋ ያለው? እኛ ጋር ደግሞ የሚጎሉት ነገሮች ምንድን ናቸው የሚሉትን ባለሙያ ልኮ የተሻለውን ነገር በመመልከት ኢትዮጵያም ያንን ፈለግ ተከትላ ከመሥራት አንጻር እንዲሁም ከቴክኖሎጂ ሽግግር ጋር ተያይዞ አፍሪካ ውስጥ እንደሚገኙ ሀገራት ሞሮኮ አሁን ያለችበት ደረጃ የተሻለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን እየተጠቀሙ ይገናኛሉ ፤ ከቴክኖሎጂም አንጻር ወደ እግርኳሱ ማምጣት የምንችላቸው ተሞክሮዎች ካሉ ከእነሱ ማግኘት የምንችልበት አጠቃላይ ሁኔታዎችን ያካትታል ማለት ነው። ስለዚህ ስምምነቱ አንድ ነገር ላይ ብቻ ሳይሆን በርከት ያሉ ነገሮችን አብሮ ከመሥራት አብሮ በጋራ ወደፊት እግርኳሱን ከማሳደግ ጋር የተያያዘ ነው።\”

አብሮ የመሥራት ፍላጎቱ የተነሳው ከማን ነበር?

\”ፍላጎቱ በሁለቱም በኩል ነው የነበረው። በተለይም ክቡር ፕሬዝዳንታችን እንደዚህ አዳዲስ ነገሮችን በፌዴሬሽኑ ውስጥ የመሞከር ፍላጎት ነበራቸው ፤ ያንንም ግንኙነት ፈጥረዋል። ስለዚህ ሞሮኮም ደግሞ ያላትን ነገር በተለይም ለአፍሪካ ሀገራት ለማጋራት የነበራት ዝግጁነት የሚደነቅ ነው። ከዛ አንጻር እንደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አቋም የመያዙ ነገር ክቡር ፕሬዝዳንታችንም ጋር ስለነበር ያ ደግሞ ስኬታማ ሲሆን እንደምትመለከተው ጊዜም ሳይወሰድ ወደ ሞሮኮ በመሄድ ሥራዎች መሥራት የተጀመረው እና ዓለም ዋንጫ ላይ አራተኛ ከመውጣታቸው እና ከብዙ ነገር በፊት ነው እኛ መጥተን የጀመርነው።\”

\"\"

መሠረተ ልማቶችን በተመለከተ ያሉት ሀሳብ እና አሰልጣኞች የማገዙ ስራ በቅርቡ ይጀመራል?

\”ከመሠረተ ልማት ጋር በተያያዘ እንግዲህ ከእነሱ ጋር ምክር የመለዋወጥ ሥራዎችን ነው እየሠራን ያለነው። ከዛ ውጪ አንድ ያልጠቀስኩት የእግርኳስ ዳኝነት ልማት ጋር በተያያዘ አብረን በጋራ ለመሥራት ፍላጎቱ አለን። ከዚህ ከአሰልጣኞች ጋር በተያያዘ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ የሆኑ ዕድሎች ይኖራሉ ብለን እናስባለን።\”

በዚህ ስምምነት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሚያገኘው ጥቅም ብዙ ነው። የሞሮኮ እግርኳስ ፌዴሬሽንስ ከስምምነቱ ምንድነው የሚያገኘው?

\”እውነት ለመናገር አሁን ባለንበት ሁኔታ የተለየ ለእነሱ ማድረግ የምንችልበት ሁኔታ ላይ ነን ብለን ለመናገር አንችልም ፤ ምክንያቱም ክፍተቶች እንዳሉ ይታወቃል። ግን የአንድ ሀገር እግርኳስ ወይም ደግሞ የሞሮኮ እግርኳስ ብቻ ማደጉ የአህጉሩን እግርኳስ ማሳደግ ነው ማለት አይደለም። ተወዳዳሪ የሆኑ ብሔራዊ ቡድኖች ያስፈልጋሉ ፤ ከዛ አስተሳሰብም አንጻር ነው እኛም ባደግን ቁጥር ሌሎች ሀገሮችም ማደግ አለባቸው የሚል ሀሳብ ይዘው እየተነሱ ያሉትና ኢትዮጵያም በዚህ ሁኔታ ምን ልታደርግላቸው ትችላለች ካልን እኛ ጥሩ ተማሪ ነን ፤ ከእነሱ ብዙ የምንወስዳቸው ነገሮች አሉ። በእርግጥ እግርኳሳችን ያለበት ደረጃ ከእነሱ ልንወስዳቸው ወይም ልንማራቸው የምንችላቸው ነገሮች ይበዛሉ። በተቻለ መጠን ጥሩ ተማሪ ሆነን እኛም ተወዳዳሪ የምንሆንበትን ሁኔታ መፍጠር ነው። ከዛ ውጪ ደግሞ በሀገራችንም ደግሞ የተሻለ ደረጃ ላይ የደረሱ እንደነ ባምላክ ተሰማ ያሉ ኤሊት ዳኞች ይኖሩናልና እነሱንም ከመጠቀም አንጻር ደግሞ ከእነሱ ልምድ ከማግኘት እና ሞሮኮ አሁን ካለችበት ደረጃ አንጻር ከእኛ ይፈልጋሉ እያልን ሳይሆን እንደዚህ ወጣ ያሉ ባለሙያዎቻችን ደግሞ ከቴክኖሎጂ ጋር አብሮ ከመሥራት ጋር በተያያዘ የጋራ ጥቅም እንዲኖረው የሚያስችል ሥራ ይሠራል በእኛ በኩል።\”

እኛ ጥሩ ተማሪ ነን ካሉ ባለፉት ቀናት በሞሮኮ ቆይታችሁ ምን ትምህርት ወሰዳችሁ?

\”ከሜዳ አንፃር በተወሰነ ኬሎሜትር ርቀት እንኳን ማዘውተሪያ ስፍራዎች አሉ። ወጣቱ እና ታዳጊው ስፖርት ሊሰራባቸው የሚችልባቸው ደረጃቸውን የጠበቁ ሜዳዎች አሉ። የእግርኳስ ሜዳ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ስፖርቶችም ምን ያህል እየሰሩ እንደሆነ አይተናል። ዋናው ነገር ጤናማ እና በስፖርት የዳበረ ህብረተሰብ ሲኖርህ ምርታማነትም ከፍ እያለ ይመጣል። ከዚህ አንፃር ጤናን ከመጠበቅ አንፃር መንግስታቸቸው የሰራውን የስፖርት መሰረተ ልማቶች የማየቱ ዕድል ነበረን። ከዚህ በኋላ ነው ወደ ኤሊት እግርኳስ ወደሚለው ነገር የምትመጣው። ከዚህ አንፃር በየቦታው ያለው ነገር በጣም የሚያስገርም ነው። ምናለ አዲስ አበባ እና ሌሎች የሀገራችን ከተሞች እንደዚህ ሆነው ባያቸው ብለህ ታስባለህ። ቢያንስ በየቀበሌው እና ወረዳው እንደዚህ አይነት ነገር ቢኖር ምን ያህል ህብረተሰቡ ለውጥ ማምጣት የሚል ነው ብዬ አስባለው። ቀን ብቻ ሳይሆን ማታም ነው የሚሰራው። ይሄ ሰፈር ውስጥ ነው የሚሰራው። ከፍ ወዳለው ስፖርተኛ ስንመጣ ደግሞ ያሉ ስታዲየሞችን እያየን ነው። በምን አይነት ጥራት ስታዲየሞቹ የተሰሩ እንደሆነ እያየን ነው። እውነት ለመናገር እዚህ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ክቡር አምባሳደር አቶ ኢሳይያስ ብዙ ነገሮችን አንስተናል። ወደፊት የመንግስት አመራር ወደ ሞሮኮ ሊመጣ ይችላልና በደንብ አፅዕኖት ሰጥተው እንደዚህ አይነት ነገሮችን እንዲጎበኙና እንደ ሀገራችን አሁን ካሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ጋር ተግባራዊ የሚሆኑበት መንገድ እንዲፈጠር አንስተናል። አሁን ዶ/ር ዐብይ በየአካባቢው የጀመሩት ነገር አለ። ይሄ ነገር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከሞሮኮ መንግስት ወይም ከተለያዩ አካላት ጋር መነጋገር ሊሆን ይችላል። ይሄ ትልቅ ልምድ ነው። ከዚህ ውጪ ደግሞ እግርኳሳቸው ምን ደረጃ እንዳለ እያየን ነው። አሁን ሞሮኮ የአፍሪካ መሐከል ሆናለች። በርካታ ቡድኖች ስታዲየማቸው ተቀቶ እዚህ እየተጫወቱ ነው። ይሄ በራሱ ትልቅ ነገር ነው። ከስፖርት ቱሪዝምም አንፃር ብዙ ነገር እንዳለ ማሰብ ይቻላል። ይሄንንም ደግሞ ምስራቅ አፍሪካ የምትገኘው ሩዋንዳ ምን እየሰራች እንደሆነ ማየት ይቻላል። በአጠቃላይ ብዙ የምንማራቸው ነገሮች አሉ።\”

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሞሮኮ ላይ ሁለት ጨዋታዎችን ሲያደርግ በሞሮኮ እግርኳስ ፌዴሬሽን የተደረገለትን አቀባበል እና እንክብካቤ በተመለከተ ምን ይላሉ?

\”የሞሮኮ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከመምጣታችን በፊት ጀምሮ ሲገልፁልን እንደነበረው ነው አሁንም እዚህ መሬት ላይ እየሆነ ያለወረ ነገር። ከአቀባበሉ ጀምሮ እያንዳንዱን ነገር ከማመቻቸት እንዲሁም ውድድሩን ለማመቻቸት ሰውም መድበውልን ከጠበቅነው በላይ ነው እያገዙን የሚገኙት። እውነት ለመናገር የተሰጠው ትኩረት ልክ የራሳቸው ብሔራዊ ቡድንን የሚያስተናግዱ እስኪመስል ድረስ ነው። በዚህ አጋጣሚ የሞሮኮ እግርኳስ ፌዴሬሽን እያደረገልን ላለው ነገር ላቅ ያለ ምስጋናችንን ልናቀርብ እንፈልጋለን። ይሄ ትልቅ ድጋፍ ነው። ለዚህም እናመሰግናለን። በዚሁ አጋጣሚ ደግሞ ይሄንን ዕድል ለፈጠሩልን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ክቡር ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ከልብ የመነጨ ምስጋናችንን ማቅረብ እንፈልጋለን። ብዙ ጊዜ ራስ ጋር ያለ ሰው አይመሰገንምና ይሄንን ነገር እሳቸው ባይፈጥሩት ኖሮ ምንም ማድረግ አንችልም ነበር። ከፍተኛ ወጪ የምናወጣበት ሁኔታ ይፈጠር ነበር። አሁን ላይ ያለው ነገር ልክ እንደ ቤታችን ተሰምቶን እንድንንቀሳቀስ የፈለግነውን ነገር እያቀረቡልን ነው ያለው። እነሱን ላመሰግንበት የምችልበት ምንም ቃል የለኝም። ለሁሉም ግን ላደረጉልን ነገር ሁሉ ከልብ እናመሰግናለን ፤ ለወደፊቱም ደግሞ አብረን ለምንሰራው ነገር እንደኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከልብ እናመሰግናለን። ትልቅ ሸክም ነው ያነሱልን። ያለምምም መንገጫገጭ ነው ቆይታ ያደረግነው። ለዚህም በድጋሜ እናመሰግናለን።\”

በቀጣይስ መሰል የውጪ ግንኙነቶችን ለመፍጠር ፌዴሬሽኑ ምን ያህል እየሰራ ነው?

\”አሁን ሞሮኮን ጠበቅ አድርገን ይዘናል። ከሌሎችም ሀገራት ጋር የምንገናኝበትን መንገድ ጠንክረን ነው የምንሰራው። ከዚህ ቀደም ከእስራኤል እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር የጀመርነው ነገር አለ። አሁንም የተለያዩ ፍላጎቶች አሉ። እነዛን ፍላጎቶች ለሀገራችን ምን ያህል ይጠቅማል የሚለውን አስቦ አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል። ይህም ብቻ ሳይሆን ሁሌ ተደጋፊ እና ሁሌ እርዳታ አግኚ የሚል ስሜትም እንዳይፈጠር ደግሞ እኛም በአጭር ጊዜ ውስጥ ራሳችንን አውጥተን እግርኳሳችንን ማሳደግ የቤት ስራችን ነው። ለምሳሌ የስፖርት መሰረተ ልማቶችን በተመለከተ በሀገራችን ያለውን ክፍተት ያገኘነውን ልምድ ለሚመለከተው አካል ማቅረብ እና ስራው እንዲሰራ ማድረግ መቻል አለበት። ሁል ጊዜ ተለጥፎ የሆነ ነገር ማግኘት ብቻ ሳይሆን ከወሰድናቸው እና ከተጠቀምናቸው ነገሮች ሀገራችን ላይ ለትውልድ ሊያልፉ የሚችሉ ስራዎችን ማየት ያስፈልጋል። ሁላችንም እዚህ ቦታ ለዘላለም አንቀመጥም ፤ ለትውልድ የሚተርፍ አሻራ አስቀምጠን መሄድ አለብን ብዬ አስባለው።\”