የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | የ19ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ዛሬ ሲጀመር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዕለቱ ብቸኛ ባለድል ሆኗል።

ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ 0-0 ኢትዮ ኤሌክትሪክ

በሳምንቱ የመጀመሪያ መርሐግብር ንፋስ ስልክን ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሲያገናኝ ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ያልተደረገበት ነበር። 41ኛው ደቂቃ ላይ የኤሌክትሪኳ ዙሌይካ ጁሃር ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆና ወደ ውስጥ ያሻገረችው እና ምንትዋብ ዮሐንስ ወደ ግብ ሞክራው ግብ ጠባቂዋ ላይላ ሸሪፍ በግሩም ፍጥነት በእግሯ ያገደችባት ኳስ በጨዋታው የተሻለው ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ዳኝነት ላይ በሚነሱ ቅሬታዎች እና በተጫዋቾች መካከል በተደጋጋሚ በሚከሰቱ ጉሽሚያዎች ተጋግሎ ሲቀጥል በኳስ ቁጥጥሩ ፍጹም የበላይነቱን የወሰዱት እና አጋማሹን በሙሉ በተጋጣሚ የግብ ክልል ውስጥ ማሳለፍ የቻሉት ኤሌክትሪኮች 89ኛው ደቂቃ ላይ ሽታየ ሲሳይ ወደ ሳጥን ያሻገረችው እና ከጥቂት ንክኪዎች በኋላ ትንቢት ሳሙኤል ወደ ግብ መትታው በአግዳሚው በኩል ለጥቂት ከወጣባት ኳስ ውጪ የተሻለ የግብ ዕድል ለመፍጠር ተቸግረው ጨዋታውም ያለግብ ተጠናቋል።

\"\"

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጫዋቾች ከዳኞች ጋር እንዲሁም የሁለቱም ቡድን አባላት እርስ በርስ ከፍተኛ ፀብ ውስጥ ሲገቡ ይባስ ብሎም በሁለቱም ቡድን አሰልጣኞች መሠረት ማኔ እና ድሪባ ጃንቦ መካከል የተከሰተው ፀብ ሊደገም የማይገባው ተግባር ሆኖ ተመልክተነዋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 5-0 አዲስ አበባ ከተማ

ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ  በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ብልጫ የወሰዱት ንግድ ባንኮች የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን ፍጹም የበላይነቱን ወስደዋል። ገና በ 3ተኛው ደቂቃ ሎዛ አበራ ባስቆጠረችው ግብ ጨዋታውን መምራት የጀመሩት ባንኮቹ በቀጣዮቹ 30 ደቂቃዎች ውስጥ ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ባያደርጉም 35ኛው ደቂቃ ላይ በመዲና ዐወል 44ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በሎዛ አበራ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም በግብ ጠባቂዋ መክናባችዋለች። በአጋማሹ አንድም የግብ ሙከራ ማድረግ ያልቻሉት አዲስ አበባ ከተማዎች ይባስ ብሎም ወደ ዕረፍት ሊያመሩ የዋና ዳኛዋ ማርታ መለሰ ፊሽካ ሲጠበቅ በኝቦኝ የን ተጨማሪ ግብ ተቆጥሮባቸዋል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥል እና ንግድ ባንኮች ፍጹም የበላይነቱን ሲወስዱ 60ኛው ደቂቃ ላይ አረጋሽ ካልሳ ከረጅም ርቀት ያደረገችው ሙከራ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ሲመለስባት በመጨረሻ 20 ደቂቃዎች ውስጥ ግን ሦስት ግቦች አስቆጥረዋል። በቅድሚያም 71ኛው ደቂቃ ላይ እመቤት አዲሱ ከሳጥን ውጪ ግሩም ግብ ስታስቆጥር ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ራሷ እመቤት ከግራ መስመር ከማዕዘን በተነሳ ኳስ ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ችላለች። 79ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ተቀይራ ከገባች 10 ደቂቃዎችን ብቻ ሜዳ ላይ የቆየችው መሳይ ተመስገን እጅግ ድንቅ ግብ ከሳጥን ውጭ ስታስቆጥር የተጋጣሚን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመመከት እጅግ የተቸገሩት አዲስአበባዎች በአረጋሽ ካልሳ እና በሎዛ አበራ ተጨማሪ ሙከራ አስተናግደው ነበር። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 5-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

መቻል 0-0 ሀዋሳ ከተማ

ቀዝቀዝ ብሎ በጀመረው የዕለቱ የመጨረሻ መርሐግብር በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል በመስመር ብልጫውን ለመውሰድ ከሚደረጉ ፉክክሮች ውጪ ንጽህ የግብ ዕድል ያልተፈጠረበት ነበር። ወደ ዕረፍት ሊያመሩ በተጨመሩ የባከኑ ደቂቃዎች ውስጥ የሀዋሳዋ ፀሐይነሽ ጁላ በቀኝ መስመር ከረጅም ርቀት ከተገኘ የቅጣት ምት ያደረገችው እና የግቡን አግዳሚ ገጭቶ የተመለሰባት ኳስ በአጋማሹ ብቸኛው ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር።

ከዕረፍት መልስም ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ በኩል የተሻሉ የነበሩት መቻሎች የሀዋሳን የተከላካይ መስመር ጥሰው ለመግባት ሲፈተኑ በአጋማሹም በሀዋሳዎች በኩል ፀሐይነሽ ጁላ ከግራ መስመር ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ያደረገችው ሙከራ በመቻሎች በኩል 86ኛው ደቂቃ ላይ ምርቃት ፈለቀ ከቀኝ መስመር ያሻገረችው እና ኳሱን ያገኘችው ሴናፍ ዋቁማ ኃይል በሌለው ሙከራ ሳትጠቀምበት የቀረችው የግብ ዕድል ተጠቃሽ ነበሩ። ሆኖም ጨዋታው ያለግብ ተጠናቋል።

\"\"