ከፍተኛ ሊግ | ቦዲቲ ፣ ጂንካ እና እንጅባራ ሦስት ነጥብ አሳክተዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ የ2ዐኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ መደረግ ሲጀምሩ ቦዲቲ ከተማ ፣ ጂንካ ከተማ እና እንጅባራ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን ሲረቱ የሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን እና አዲስ አበባ ከተማ ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል።

\"\"

የሳምንቱ የመክፈቻ ጨዋታ ቦዲቲ ከተማ እና ቂርቆስ ክፍለ ከተማን አገናኝቶ በቦዲቲ የ2ለ1 ድል አድራጊነት ተቋጭቷል። በኳስ ቁጥጥሩ የቂርቆስን የበላይነት ብናይም በመልሶ ማጥቃት ወደ ሦስተኛ የሜዳ ክፍል በቀላሉ የሚደርሱት ቦዲቱዎች በማሞ አየለ ጎል በ6ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን ችለዋል። ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል በብዙ መልኩ አሁንም ከኳስ ጋር በምቾት በመጫወት ቂርቆስ ተሽሎ ቀጥሏል። ይሁን እንጂ 50ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ማንዴላ መለሠ ያሻማትን ኳስ ተጠቅሞ ክብሩ በለጠ ሁለተኛ ጎል ለቦዲቲ አስቆጥሯል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ የመጨረሻዎቹን ሰላሳ ያህል ደቂቃዎች እየቀሩ ወደ ጨዋታ ቅኝት በጥልቀት የገቡት ቂርቆሶች 70ኛ ደቂቃ ሲደርስ የቦዲቲው ተከላካይ ግሩም ግዛው በተመስገን ዘውዱ ላይ ሳጥን ውስጥ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ከድር ሳህል ወደ ጎልነት ለውጧት ጨዋታው በቦዲቲ የ2ለ1 ድል ፍፃሜን አግኝቷል።

\"\"

በቀጣይነት ጂንካ ከተማን ከነቀምት ከተማ ያገናኘው መርሀግብር ቀጥሎ ተከናውኗል። ረጃጅም ኳሶች የበረከቱበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ በተደረጉ ፈጣን የመልሶ ማጥቃት የጨዋታ ሒደቶች ነበር ጎሎችን ያስመለከተን በተሻለ የማጥቃት ወጥነት የተጫወቱት የአሰልጣኝ መድምሙ ጂንካ ተጫዋቾች 73ኛው ደቂቃ ላይ ቁመታሙ አጥቂ ማኑሄ ጌታቸው ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ አማካዩ ሀቁምንይሁን ገዛኸኝ ከመረብ ባገናኛት ኳስ መሪ መሆን ሲችሉ ከአስራ አምስት ደቂቃዎች መልስ ማኑሄ ጌታቸው ሁለተኛ ጎል አክሎ ጨዋታው በጂንካ የ2ለ0 ድል ተጠናቋል።

የእንጂባራ ከተማ እና ሺንሺቾ መርሀግብር ሜዳ ላይ ጥሩ የመሸናነፍ ስሜትን በሁለቱም ቡድኖች በኩል በጉልህ ያየንበትን የጨዋታ መንገድ ተመልክተንበታል። መሐል ሜዳ ላይ በተሻለ የቅብብል ወጥነት ይጫወቱ የነበሩት እንጅባራዎች በተደጋጋሚ ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ቶሎ ቶሎ ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ይደርሱ ነበር። ጨዋታው በሁለተኛ አጋማሽ ተመልሶ ሲቀጥል በአሰልጣኝ አዲሱ ዶይሶ የሚመሩት እንጂባራዎች ባደረጉት ብርቱ የጥቃት ወጥነት የተነሳ ኳስ እና መረብን አዋህደዋል።

\"\"

63ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ደምቆ የዋለው አማካዩ ምትኩ ማመጫ በጥሩ እይታ በተከላካዮች መሐል የላከለትን ኳስ ተጠቅሞ ባህሩ ነጋሽ የግብ ጠባቂን መውጣት ተመልክቶ እጅግ ማራኪ ጎል አስቆጥሯል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተሰጠው የጭማሪ ደቂቃ ላይ የሺንሺቾው ተከላካይ ሚሊዮን ካሳ ግጭት በማስተናገዱ ምላሱ ታጥፎ ለረጅም ደቂቃዎች ራሱን ስቶ የነበረ ቢሆንም በተደረገለት ህክምና መንቃት በመቻሉ ጨዋታው የቀሩት ደቂቃዎች ተደርገውበት በእንጅባራ 1ለ0 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

የዕለቱ የማሳረጊያ ጨዋታ ጎል ሳያስመለክተን ተጠናቋል። የሰሜን ሸዋ ደብረብርሃንን እና ከአዲስ አበባ ከተማ ጨዋታ በጀመረ በአራተኛው ደቂቃ ላይ በጣለው ንፋስ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ ተቋርጦ ሰላሳ ደቂቃዎችን ቆይታ ከተደረገበት በኋላ በድጋሚ ቀጥሏል። ጨዋታው ወደ ግብ የመድረስ ፉክክሮችን እያሳየን ቢዘልቅም ወደ ጎልነት የተለወጡ ኳሶችን ለማየት ግን አልታደልንበትም ይልቁኑስ መደበኛው የጨዋታ ደቂቃ ተጠናቆ በተሰጠው የጭማሪ ደቂቃ ላይ የደብረብርሃኑ የመስመር አጥቂ ያሬድ ብርሀኑ ሙሉቀን ታሪኩን መተሀል በሚል በዕለቱ ዳኛ ሔኖክ አበበ በቀይ ከተወገደ በኋላ ጨዋታው 0ለ0 ተደምድሟል።

\"\"