የኢትዮጵያ የሴቶች እግርኳስ አሰልጣኞች ማኅበር የምሥረታ ጉባዔ ተደርጓል

የኢትዮጵያ የሴቶች እግርኳስ አሰልጣኞች ማኅበር የምክክር መድረክ ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ አዝዋ ሆቴል ተካሂዷል።

በጋራ በመሰባሰብ ሙያዎች እና ዕውቀቶችን በመካፈል እና በመለዋወጥ  የተሻለ የሴቶችን ሊግ የመፍጠር እና የተለያዩ የማኅበራዊ ችግሮችን የመፍታት ዓላማን ያነገበው ማኅበር ዛሬ ሚያዚያ 14/2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ከሚሳተፉ አሥራ ሦስት ቡድኖች የዘጠኙ  ቡድኖች አባላት በተገኙበት ምሥረታውን አድርጓል። \”የማኀበሩ እስከዛሬ ሳይመሠረት መቆየት ብዙ ነገር አጉድሎብን ነበር።\” የሚሉት አሰልጣኞቹ እንደ ምክንያትም \”እርስ በእርሳችን ጥሩ ግንኙነት እንዳይኖረን እና ዕውቀታችንን እንዳንከፋፈል ዕክል ፈጥሮብን ነበር። በተለይም በችግርም በደስታም ጊዜ መገናኘት እና የግለሰብን ችግሮች በጋራ አድርጎ መፍታት ፣ አቅም የቸገረውን አንዱ እንዲሞላለት በማድረጉ በኩል ብዙ መሥራት ስለሚጠበቅብን እና የተሻሉ ነገሮችን ማድረግ ስንችል እንዳንችል በመደረጋችን እና በቀጣይም በምንችለው አቅም አሰልጣኞችም በሙያቸው እና ባላቸው አቅም የተሻለ ነገር መሥራት እንዲችሉ ለማድረግ አስበናል\” ብለዋል ።

\"\"

ሌሎች ከዚህ በፊት ተመሥርተው ብዙ ርቀት ያልሄዱ ማኅበራትን በመጥቀስ \”በተቻለን አቅም ካለፉት ተሞክሮዎች መማር አለብን ብለን እናስባለን። ሌሎቹ የፈረሱበትን ምክንያት ካወቅን ይህ ማኅበር እንዳይፈርስ  ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን። እንደሚታየው አሰልጣኞቹ ከተለያየ አካባቢ የሚኖሩ ናቸው። አቀማመጣችን እና የተለያየ አካባቢ መኖራችን አንዱ ፈታኝ ምክንያት ሊሆን የሚችል ነገር ነው ብለን ነው የምናስበው። ግን እነዚህን ሁሉ ተቋቁመን ለሚቀጥለው ትውልድ የምናስረክበው ማኅበር እንዲሆን ብዙዎቻችን በስሜት ሳይሆን በፍላጎት ታስቦበት እና ታቅዶበት በእውነት የመሠረትነው ማኅበር ስለሆነ በቀጣይ የተሻለ ይሆናል የሚል እምነት አለን። አሁን ሊጉን የሚመራው በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሥር የተቋቋመው የሴቶች ልማት ዴስክ ነው። ስለዚህ ይህንን የሴቶች ልማት ዴስክ ከጎኑ በመሆን ከፍተኛ የሆኑ ግብዓቶችን በመስጠት ውድድሮቹ የበለጠ ደማቅ እና ውብ የሆነ ጠንካራ ተፎካካሪነት ሊኖራቸው የሚችሉ ሀሳቦችን እና ግብዓቶችን በማቅረብ ከነሱ ጋር ቅርርብ በመፍጠር የተሻለ ውድድር እንዲኖር ለማድረግ እንዲሁም ተጨማሪ ሌሎችን ሀሳቦችን በማቅረብ ከሴቶች ልማት ዴስክ ኃላፊዎች ጋር ወይም ኮሚቴዎች ጋር በመነጋገር እና በጋራ በመሥራት የተሻለ ነገር ለማድረግ እንደ ዕቅድ አስበናል። እኛ እያቋቋምን ያለነው የኢትዮጵያ የሴቶች እግርኳስ አሰልጣኞች ማኅበር በመሆኑ ከሌሎች ጋር የሚጣረስ ማኀበር አይደለም።\” ሲሉም ሀሳባቸውን ያጠናክራሉ።

\"\"

በመጨረሻም በጉባዔው መሠረት ማኅበሩን ሰባት ኮሚቴዎች እንዲመሩት ሲወሰን ከከፍተኛ ሊጉ የሚመጡ ሁለት አባላት ቦታ በመተው አምስት የሚሆኑት አባላት ተመርጠው የሥራ ክፍፍል አድርገዋል።

1ኛ. ብርሃኑ ግዛው (ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ቡድን ዋና አሰልጣኝ ) – የማኅበሩ ሰብሳቢ
2. መሠረት ማኔ (የኢትዮ ኤሌክትሪክ ሴቶች ቡድን ዋና አሰልጣኝ) – የማኅበሩ ምክትል ሰብሳቢ
3. ዳዊት ሀብቴ (የትዕንግርት ስፖርት ዋና ፀሐፊ) – ሕዝብ ግንኙነት
4. መልካሙ ታፈረ (የሀዋሳ ከተማ ሴቶች ቡድን ዋና አሰልጣኝ) – ፀሐፊ
5. ዮሴፍ ገብረወልድ (የአርባምንጭ ከተማ ሴቶች ቡድን ዋና አሰልጣኝ) – ሂሳብ ሹም ሆነው ተመርጠዋል።


በመጨረሻም የፎቶ መነሳት መርሐግብር ተካሂዶ ጉባዔው ተጠናቋል።