የአንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ላይ የሚሳተፉ ክለቦች ሲለዩ የውድድሩ ስፍራም ታውቋል

በተለያዩ ከተሞች ከህዳር 20 ጀምሮ ሲደረግ የነበረው የአንደኛ ሊግ የምድብ ጨዋታዎች አስራ ሁለት ክለቦችን ወደ ማጠቃለያ ውድድር አሳልፎ ተጠናቋል።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን አዘጋጅነት በየዓመቱ የሚዘጋጀው የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ውድድር የ2015 መርሀግብር በአራት ምድቦች ተከፍሎ በድምሩ በ53 ክለቦች መካከል ሲደረግ ቆይቶ በያዝነው ሳምንት መጨረሻ አስራ ሁለት ቡድኖችን ወደ ማጠቃለያ ውድድር አሳልፎ የምድብ ጨዋታዎቹ ተገባደዋል። ውድድሩ ህዳር 20 ሲጀመር ሀዋሳ ከተማ ፣ ወላይታ ሶዶ ፣ ደብረማርቆስ ከተማ እና ቢሾፍቱ ከተማ ውድድሮቹን ያስተናገዱ ሲሆን ሁለተኛውን ዙር ደግሞ ቢሾፍቱ ፣ ቡራዩ ፣ ሰበታ እና ደብረማርቆስ ከተሞች የሁለተኛውን ዙር ውድድር ያካሄዱ ሲሆን በተደረጉ ጨዋታዎችም ወደ ማጠቃለያ ውድድር ያለፉ 12 ክለቦችን ለይቶ ተገባዷል።
\"\"
የምድብ ጨዋታዎች በሚደረጉበት ወቅት ከምድብ ሀ ሙከጡሪ ከምድብ መ ደግሞ ቡሌ ሆራ እና ገደብ አሳሳ በበጀት ዕጥረት የተነሳ ውድድሩን ማቋረጣቸው የሚታወስ ሲሆን ሦስቱን ክለቦች ጨምሮ በድምሩ አስራ ሁለት ክለቦች ወደ ክልል ውድድሮች መውረድም ችለዋል።

ግንቦት 1 በአዳማ ከተማ ወደ 2016 የከፍተኛ ሊግ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ ክለቦች የሚለዩበት ውድድር የሚጀመር ሲሆን ከየምድባቸው ከአንድ እስከ ሦስት የወጡ ክለቦች በዚህ በማጠቃለያው ውድድር የሚሳተፉ ይሆናል።
\"\"
በምድብ ሀ – ዱከም ከተማ ፣ ዶሬ ላንጋኖ እና አሶሳ ከተማ
ምድብ ለ – አማራ ውሀ ስራ ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና ሞጆ ከተማ
ምድብ ሐ- ሱልልታ ከተማ ፣ ጎፋ ባራንቼ እና አዲስ ቅዳም
ምድብ መ – ኦሮሚያ ፓሊስ ኮሌጅ ፣ ንፋስ ስልክ እና ሞጣ ከተማ በማጠቃለያው ውድድር የሚሳተፉ ይሆናል።