ሪፖርት | አዳማ ከተማ ዘጠነኛ ድሉን በሲዳማ ቡና ላይ አሳክቷል

አዳማ ከተማ በሲዳማ ቡና ላይ የበላይነት በወሰደበት ጨዋታ 3-1 በመርታት ተከታታይ ድልን አስመዝግቧል።

ሁለቱም ቡድኖች ካለፈው ጨዋታቸው በተመሳሳይ የሦስት ተጫዋቾችን ለውጥ ማድረግ አስፈልጓቸዋል። አዳማ ከተማዎች ድል ካደረጉበት ጨዋታ አንፃር ኤልያስ ለገሰን በአማኑኤል ጎበና ፣ ቢኒያም አይንን በአድናን ረሻድ እና አሜ መሐመድን በቦና ዓሊ ቦታ ሲጠቀሙ ከሽንፈት የመጡት ሲዳማ ቡናዎች ፊሊፕ ኦቮኖ ፣ ቴዎድሮስ ታፈሰ እና ጉዳት የገጠመው ሰልሀዲን ሰይድን በመክብብ ደገፉ ፣ ሰለሞን ሀብቴ እና ይገዙ ቦጋለ ለውጠው ቀርበዋል።

\"\"

ከጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች አንስቶ በተዝናኖት ከኋላ የሜዳ ክፍላቸው መስርተው የመጫወት ምልክት የሰጡት አዳማዎች በተጋጣሚያቸው ላይ ብልጫን የወሰዱበት እንደነበር በጊዜ የተቆጠረችው ግብ ማሳያ ነች ፣ 7ኛው ደቂቃ ላይ ከእጅ ውርወራ መሐሪ መና በተሳሳተ አቅጣጫ የጣላት ኳስን አድናን ረሻድ አግኝቶ ለዮሴፍ ታረቀኝ ሰጥቶት የግል ጥረቱን ሳጥን ውስጥ የተጠቀመው ወጣቱ አጥቂ ከተከላካዮች ታግሎ የሰጠውን አድናን ከራሱ የተነሳችዋን ኳስ ከመረብ ቀላቅሏት አዳማን መሪ አድርጓል።

\"\"

በቁጥር በዝተው መሐል ሜዳ ላይ በሚያደርጉት ቅብብሎች ወደ ሁለቱም መስመሮች በመለጠጥ አዳማዎች በወጥነት የሲዳማን የግብ ክልል በተደጋጋሚ ማንኳኳት የቻሉ ሲሆን ጎልን ለማስቆጠር ግን የመረጋጋት ችግሮች በድግግሞሽ ተስተውሎባቸዋል።

በአጋማሹ ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመግባት ከጅምሩ አንስቶ የተቸገሩ የሚመስሉት ሲዳማ ቡናዎች ኳስን በሚያገኙበት ወቅት ወደ ግራ የሜዳው ክፍል ዘንበል ብለው የጋናዊውን አጥቂ ፊሊፕ አጃህን እንቅስቃሴ እና ከተሻጋሪ ኳስ ደግሞ መሐሪ መናንን የትኩረት መንገዳቸው አድርገዋል።

\"\"

ሆኖም 16ኛው ደቂቃ ይገዙ ቦጋለ ሰይድ ሀብታሙን ያልፈተነች እንዲሁም 35ኛው ደቂቃ የአዳማው ተከላካይ ሚሊዮን ሠለሞን ኳስን በተሳስተ መንገድ አስጀምሮ ይገዙ ደርሶት ለፍሬው ለመስጠት ሲጥር ሚሊዮን ተንሸራቶ የራሱን ስህተት ካረመበት ሙከራ ውጪ አጋጣሚዎችን በመፍጠሩ ረገድ ኮስታሮች አልነበሩም።

በአንፃሩ ጨዋታው በራሳቸው ቁጥጥር አድርገው ወደ ሦስተኛው የተጋጣሚ የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ በጥሩ የጨዋታ ፍሰት ይደርሱ የነበሩት አዳማ ከተማዎች በድንቅ የአንድ ሁለት የኳስ ንክኪ ሁለተኛ ጎላቸውን ወደ ቋታቸው ከተዋል። 

\"\"

መደበኛው የመጀመሪያ አጋማሽ ተጠናቆ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ ላይ ማለትም 45+2 ላይ አማኑኤል ጎበና ራሱ ያስጀመራትን ኳስን ከመስዑድ እና አሜ ጋር ተቀባብሎ አሜ ወደ ቀኝ የላከለትን ኳስ አንድ ጊዜ ገፋ ካደረገ በኋላ መክብብ ደገፉ መረብ ላይ አሳርፏት በ2ለ0 የአዳማ መሪነት አጋማሹ ተጋምሷል።

በቀዳሚው የጨዋታ አጋማሽ ላይ የነበረባቸውን የስልነት ችግር ለመቅረፍ ሲዳማ ቡናዎች ሁለተኛውን አጋማሽ ቡልቻ ሹራን በፀጋዬ አበራ ተክተው ወደ ሜዳ ቢገቡም ራሳቸውን ከጎል ለማገናኘት ደቂቃዎችን መጠበቅ ግድ ብሏቸዋል። በምቾት ኳስን ሜዳ ላይ በመቀባበል ተጨማሪ ጎል ለማግኘት ያልቦዘኑት አዳማ ከተማዎች እንደነበራቸው የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ሦስተኛ ጎልን አግኝተዋል። 64ኛው ደቂቃ ሙሉቀን አዲሱ በቀኝ የሲዳማ የሜዳ ክፍል ሳጥኑ ጠርዝ በአሜ ላይ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተገኘችን የቅጣት ምት ዮሴፍ ታረቀኝ መክብብ ደገፉ ባጠበበት አንግል ስር ግሩም ግብ አስቆጥሯል።

\"\"

ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ አጃህን በአቤኔዘር በመለወጥ መንቃት የጀመሩት ሲዳማ ቡናዎች አቤል እንዳለ ከአቤኔዘር አስፋው ጋር ተቀባብሎ 74ኛው ደቂቃ ላይ ቡድኑን ወደ ጨዋታ የምትመልስ ጎልን ማስቆጠር ችለዋል ቡድኑም የመጨረሻዎቹን 15 ደቂቃዎች በተደጋጋሚ ዕድሎችን መፍጠር ቢችሉም የአዳማን የኋላ ግድግዳ መሻገር ግን አልቻሉም። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲቃረብ አዳማዎች በቢኒያም እና ጀሚል ሲዳማዎች በመሐሪ መና አማካኝነት ጥሩ ጥሩ ሙከራዎችን ካደረጉ በኋላ ጨዋታው በአዳማ የ3ለ1 ድል አድራጊነት ፍፃሜው ሆኗል።

\"\"

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ አዳማ ከተማዎች ጨዋታውን ተቆጣጥሮ በመጫወቱ ድል እንደቀናው ገልፀው በቡድናቸው ላይ የነበረው አቀራረብ ግን የወረደ እንደሆነ ነገር ግን በሁለተኛ አጋማሽ ጥሩ መሆናቸውን ከጠቆሙ በኋላ በአጠቃላይ በበቡድኑ ተጫዋች ላይ መጥፎ እና ጥሩ ነገር አለ ካሉም በኋላ በውጤቱ መከፋታቸውን አልሸሸጉም። በአንፃሩ የአዳማ ከተማ አቻቸው ይታገሱ እንዳለ ጨዋታው ጥሩ መልክ እንደ ነበረው ገልፀው ቀድመው ጎል ማግባታቸው በሁለተኛው አጋማሽ ጥንቃቄን እንዲመርጡ እንዳስገደዳቸው በንግግራቸው ጠቁመዋል።