ከፍተኛ ሊግ | ሻሸመኔ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማደግ በሩ ላይ ቆሟል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ የ22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በተደረጉ አራት መርሀግብሮች ሲጀመር ሻሸመኔ ከተማ ወደ ሊጉ የማደግ ዕድሉን ከጫፍ ሲያደርስ በሌሎች ጨዋታዎች ቦዲቲ እና ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃንም ድል ቀንቷቸዋል።

\"\"

የምድብ ለ የ22ኛው ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀመሩ ቀዳሚ የነበረው የአዲስ አበባ ከተማ እና ይርጋጨፌ ቡና ጨዋታ ነበር። ጠንካራ የሜዳ ላይ ፉክክርን ያየንባቸው ሁለቱ ክለቦች በሁለቱም አጋማሾች ተቃራኒ የጨዋታ መልክን ይዘው የተመለክትንበት ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ለመንቀሳቀስ የሞከሩት አዲስ አበባ ከተማዎች 42ኛው ደቂቃ ላይ የሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሙሉቀን ታሪኩ ከመረብ ባገናኘው ግብ መሪ ሆነዋል። በሁለተኛው አርባ አምስት ስህተታቸውን አርመው ወደ ሜዳ የገቡትን እና በወጥ የማጥቃት ሽግግር የተጫወቱት ይርጋጨፌዎች 50ኛው ደቂቃ ዮሐንስ ኪሮስ ከርቀት ወደ ጎል ሲመታ የግብ ጠባቂው ሳምሶን አሰፋ ስህተት ታክሎበት ወደ ጎልነት ኳሷ ተለውጣ ጨዋታው በቀሩት ደቂቃዎች ተጨማሪ ግቦችን ሳያስመለክተን 1ለ1 በሆነ ውጤት ተደምድሟል።

\"\"

በሁለተኛው ዙር መሻሻሎችን እያሳየ የመጣው ቦዲቲ ከተማ እንጂባራ ከተማን ገጥሞ ድል አድርጓል። ከጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃ አንስቶ ኳስን አቅልለው በመጫወት ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በቀላሉ ይደርሱ የነበሩት ቦዲቲዎች በጥሩ የጨዋታ ፍሰት ቢኒያም ታከለ የሰጠውን ኳስ ማሞ አየለ በቀላሉ ጎል አድርጓታል። ከዕረፍት በኋላ የእንጅባራው አሰልጣኝ አዲሱ ዶይሶ ወደ ጨዋታ ለመመለስ የተጫዋች ለውጥን በማድረግ ቡድናቸውን አሻሽለው መቅረብ ቢችሉም ሁለት ተጫዋቾች በቀይ ለማጣት ተገደዋል።

\"\"

52ኛው ደቂቃ ላይ ትኩሱ ጌታቸውን በሁለተኛ ቢጫ ካርድ በቀይ ቢያጡም በጎዶሎ ተጫዋቾች በተደጋጋሚ ሙከራን በማድረግ ወደ አቻነት ለመምጣት እንጂባራዎች ቢሞክሩም የግብ ጠባቂው ግሩም በለጠን ድንቅ ብቃት መስበር ግን ሳይችሉ ቀርተዋል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተሰጠው የጭማሪ ደቂቃ ላይ እንጅባራ ከተማ ባህሩ ፈጠነ የእንጅባራ ተከላካይን በክርን በመማታቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከተወገደ በኋላ ጨዋታውም በ1ለ0 የቦዲቲ አሸናፊነት ተቋጭቷል።

ከቀትር መልስ በዝናባማ የዐየር ባህሪ የተገናኙት ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን እና ከምባታ ሺንሺቾ ጨዋታ 2ለ1 በሆነ የደብረብርሃን ድል ተጠናቋል። መሐል ሜዳ ላይ በሚደረጉ ቅብብሎች በቀላሉ ወደ ሦስተኛ የተጋጣሚ የግብ ክልል የሚደርሱት ደብረብርሃኖች 25ኛ ደቂቃ ገደማ የሺንሺቾው ግብ ጠባቂ ተሾመ ታደሰ እና ተከላካዮች የሰሩትን አለመናበብ ተከትሎ የተሻ ግዛው ወደ ጎልነት ቀይሯታል።

\"\"

በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ጨዋታ ሪትም ለመግባት ሺንሺቾዎች ወደ እንቅስቃሴ መለስ ቢሉም ተቀይሮ የገባው መስፍን ኪዳኔ ከየተሻ ግዛው የደረሰውን ኳስ በጥሩ አጨራረስ ለደብረብርሃን ሁለተኛ ጎል አድርጓል። ሁለት ጎል ካስተናገዱ በኋላ ወደ አቻነት ሽግግር ለማድረግ የታገሉት በሊጉ ወራጅ ላይ የሚገኙት ከምባታ ሺንሺቾዎች የማስተዛዘኛ ግብን በአምበሉ ናሆም አዕምሮ ካስቆጠሩ በኋላ ጨዋታው በሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን 2ለ1 የበላይነት ድምዳሜ ላይ ደርሷል።

ሻሸመኔ ከተማ ያለ ተፎካካሪ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማደግ እያደረገ ያለውን ጉዞ በይበልጥ ያሰመረበትን ውጤት በአምቦ ላይ ተጎናፅፏል። በበርካታ ደጋፊዎቹ ተጅቦ ጨዋታውን ያደረገው የአሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙው ሻሸመኔ ከተማ በፈጣን የመስመር አጨዋወት አቀራረቡን ቢያደርግም አምቦ ከተማዎች የዋዛዎች አልነበሩም። ሜዳ ላይ ፋታ የለሽ እንቅስቃሴዎች በርክተው ባየንበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ 23ኛው ደቂቃ ላይ በአምቦ የግራ የሜዳው ክፍል የተገኘን የቅጣት ምት አማካዩ ሳምሶን ተሾመ ቀርቅሯት ሻሸመኔን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

\"\"

ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ቀጥሎ አምቦ ከተማዎች አቻ ለመሆን ቶሎ ቶሎ ወደ ሻሸመኔ የግብ ክልል ደርሰው ብናይም ደካማው የአጨራረስ ችግራቸው በተቃራኒው በፈጣን ሽግግር በተጫወቱት ሻሸመኔዎች ሁለተኛ ጎል አስተናግደዋል። 63ኛው ደቂቃ ኤቢሳ ከድር ግሩም ኳስን ከመረብ ያገናኘው ተጫዋች ነው። ሁለት ጎሎችን ካስተናገዱ በኋላ በተነሳሽነት ሲጫወቱ የተመለከትናቸው አምቦዎች በአጥቂው ነቢል አብዱልሰላም ከሽንፈት ያልዳኑበትን ጎል ካገኙ በኋላ ጨዋታው 2ለ1 ተቋጭቷል። ውጤቱን ተከትሎ ሻሸመኔ ከተማ ከቀጣዩ የ23ኛ ሳምንት የነቀምት ጨዋታው አንድ ነጥብን ማግኘች ከቻለ ወደ 2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ማደጉን ያረጋግጣል።

\"\"