መረጃዎች | 94ኛ የጨዋታ ቀን

ነገ በ23ኛው ሳምንት የሚስተናገዱትን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።

ኢትዮጵያ መድን ከ ሲዳማ ቡና

ባሳለፍነው ሳምንት ከድል ጋር የተገናኙት ኢትዮጵያ መድን እና ሲዳማ ቡና ተከታታይ ጨዋታዎችን የማሽነፍ ህልምን ይዘው ይገናኛሉ።

\"\"

ለገጣፎ ለገዳዲ ላይ የጎል ናዳ ካዘነበ በኋላ ነገሮች ለኢትዮጵያ መድን ጥሩ አልነበሩም። ሦስት ጨዋታዎችን ማሸነፍ አለመቻላቸው ከዋንጫ ፉክክሩ ቢያንሸራትታቸውም ኢትዮ ኤሌክትሪክን በማሸነፍ ቢያንስ ከኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ደረጃው ላለመራቅ ጥረታቸውን ቀጥለዋል። ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባህር ዳር ከተማ ዛሬ ማሸነፉ ደግሞ የነጥብ ልዩነቱን ወደ ስድስት ከፍ ስላረገው የነገው ጨዋታ ለመድን ወሳኝ ሆኗል። ሲዳማ ቡናም ወደ መቀመጫ ከተማው በተመለሰበት ቀዳሚ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማን 1-0 መርታት ችሏል። ከድሉ ባሻገር ቡድኑ በእንቅስቃሴም ረገድ ተስፋ ማሳየቱ በጥሩ ጎን ቢታይም አሁንም በወራጅ ቀጠና ውስጥ መገኘቱ ግን ለነገው ጨዋታ ከፍ ያለ ትኩረት እንዲሰጠው ያደርገዋል። በዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ተከታታይ ድል ማሳካት ከቻለ ግን ይህንን ሳምንት ከአደጋ ዞኑ በጥቂቱ ከፍ ማለት ይችላል።

ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም በሊጉ 7 ጊዜ ተገናኝተው ሲዳማ ቡና 2 ጊዜ ሲያሸንፍ 4 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተለያይተው ኢትዮጵያ መድን የዘንድሮውን ጨዋታ አሸንፏል። በጨዋታዎቹ ሲዳማ 6 ሲያስቆጥር መድን በበኩሉ 8 አስቆጥሯል።

ሀዋሳ ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

ከዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በተለየ የምሽቱ ፍልሚያ በ22ኛው ሳምንት ሽንፈት የገጠማቸው ቡድኖች የሚገናኙበት ይሆናል።

ሀዋሳ ከተማ ውድድሩ ወደ መቀመጫ ከተማው ቢመጣም በመጀመሪያ ጨዋታው በሲዳማ ቡና ተረቷል። ይህ በመሆኑም ቡድኑ ለሦስተኛ ተከታታይ ጊዜ የ1-0 ሽንፈትን በውጤት ዝርዝሩ ውስጥ እንዲመዘግብ አስገድዶታል። ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ ባልተገመተ መልኩ በለገጣፎ ለገዳዲ ነጥብ ከጣለበት ጨዋታ በኋላ በፋሲል ከነማ ሽንፈት አጋጥሞታል። ከወቅታዊ ውጤት መመሳሰል ባለፈ በኩል 31 ነጥብ ላይ የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች ወደ አራተኛነት ከፍ ለማለት ይፋለማሉ።

\"\"

በጨዋታው ሀዋሳ ከተማ ብርሀኑ አሻሞ እና ወንድምአገኝ ኃይሉን በጉዳት ምክንያት ሲያጣ ሀዲያ ሆሳዕናም ባዬ ገዛኸኝን በቅጣት ቃለአብ ውብሸት እና ቤዛ መድህንን በጉዳት ሳቢያ አያሰልፍም።

ቡድኖቹ እስካሁን ሰባት ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ ከተማ ሁለቱ ሲረታ ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ አንዱን አሸንፏል። ቀሪዎቹን አራት ጨዋታ ደግሞ በአቻ ውጤት ፈፅመዋል። በጨዋታዎቹም ሀዋሳ 12 ሀዲያ 10 ጎሎች አስቆጥረዋል።