ሪፖርት | በሁለት አጋማሾች የተቆጠሩ አራት ግቦች ሀዋሳ እና መድንን ነጥብ አጋርተዋል

ሲሞን ፒተር እና ሰዒድ ሀሰን በሁለቱም አጋማሾች ለክለቦቻቸው ያስቆጠሯቸው ግቦች ሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድንን 2ለ2 አቻ አለያይተዋል።

ባለሜዳው ሀዋሳ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ ከተጋራበት ስብስቡ በቅጣት ባጣው በረከት ሳሙኤል ምትክ ሰዒድ ሀሰንን የተካበት ብቸኛ ቅያሪው ሲሆን ከድሬዳዋው ድል አንፃር ኢትዮጵያ መድኖች በሁለቱ ላይ ቅያሪ አስፈልጓቸዋል። በዚህም ወገኔ ገዛኸኝ እና ሐቢብ ከማልን በዮናስ ገረመው እና ኪቲካ ጀማ ለውጠዋዋል።


መድኖች የዕለቱ ዳኛ ሀይለሱስ ባዘዘው ባስጀመሩበት ቅፅበት ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል እንዳመሩ ነበር መሪ መሆን የቻሉት። በዚህም 2ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ ሙሉጌታ ላይ በሳጥን ውስጥ ተከላካዩ ፀጋአብ ዮሐንስ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠችውን የፍፁም ቅጣት ምት ሲሞን ፒተር ወደ ግብነት ለውጧት ቡድኑ ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ጎልን ገና በጊዜ ካስተናገዱ በኋላ በፍጥነት ሀዋሳዎች አከታትለው ጥቃትን ሰንዝረዋል። 4ኛው ደቂቃ ላይ በሽግግር የጨዋታ ሒደት ከግራ መስመር በኩል የደረሰውን ኳስ ኤፍሬም አሻሞ አቡበከር መረብ ላይ አሳረፈው ተብሎ ሲጠበቅ ስቷታል። ከዚህች ሙከራ አንድ ደቂቃ በኋላ ግን ሀዋሳ አቻ የሆነበትን ግብ በተከላካዩ ሊያገኝ ችሏል። ከመድን የግራ የሜዳው ክፍል ከመስመር ካደላ ቦታ ላይ መድሀኔ ብርሀኔ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተንተርሶ የተገኘችን ቅጣት ምት እዮብ አለማየሁ በረጅሙ ወደ ጎል ሲያሻማ ሰዒድ ሀሰን በግንባር ገጭቶ አቻ የሆኑበትን ጎል አስገኝቷል።


ገና በመጀመሪያዎቹ የጨዋታ ደቂቃዎች ጎሎች ከተቆጠሩ በኋላ መድኖች ወደ ጨዋታ ራሳቸውን በይበልጥ ለማስገባት በፈጣን የመስመር አጨዋወት የሀዋሳን የተከላካይ ክፍል ሲረብሹ ተስተውሏል። ለዚህም ማሳያው 10ኛው ደቂቃ ላይ ሲሞን የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ያቀበለውን ኳስ ብሩክ ነፃ ቦታ ሆኖ ወደ ጎል መቶ መሐመድ ሙንታሪ ያወጣበት እና በድጋሚ ደግሞ ሲሞን ግልፅ ዕድልን አግኝቶ በሙንታሪ የመከነበት አጋጣሚዎች የሚጠቀሱት ናቸው። ሀዋሳዎች በማጥቃቱ ረገድ ሻል ቢሉም የኋላ መስመራቸው ክፍት ከመሆኑ አኳያ ተጋጣሚያቸው በቀላሉ ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል እንዲገባ ሲያደርጉ ተመልክተናል። ተባረክ ሂፋሞ ከሳጥን ውጪ ከሞከራት ሙከራ ውጪ በተቃራኒው መድኖች ተካልኝ በተለይ 32ኛው ደቂቃ ሲሞን ሰጥቶ ኪቲካ በቀላሉ ያመከናቸው የሚጠቀሱት ሙከራዎች የነበሩ ሲሆን አጋማሹ በ1ለ1 ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

\"\"

ከዕረፍት ጨዋታው ተመልሶ ሲቀጥል ሀዋሳዎች ከመስመር በሚነሱ ኳሶች የጨዋታ መንገዳቸው አድርገው ለመንቀሳቀስ በሞከሩበት ፍጥነት ጥሩ የግብ አጋጣሚን ፈጥረው ታይተዋል። 51ኛው ደቂቃ ላይ እዮብ አለማየሁ በረጅሙ ወደ ጎል ያሻገራት ኳስን ተባረክ ሄፋሞ በግንባር ገጭቶ አቡበከር ኑራ በጥሩ ቅልጥፍና ያወጣበት ሙከራ የምትጠቀስ ነች። ኳስን በሚያገኙበት ወቅት በፈጣን አጨዋወት ወደ መስመር አጋድለው የሚንቀሳቀሱት መድኖች በድጋሚ ወደ መሪነት መጥተዋል። 57ኛው ደቂቃ ላይ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ኪቲካ ጀማ ኳስን ወደ ሳጥን ይዞ በሚገባበት ወቅት መድሀኔ ብርሀኔ ሳጥን ውስጥ ጥፋት በመስራቱ ለሁለተኛ ጊዜ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ዩጋንዳዊው አጥቂ ሲሞን በቀላሉ ከመረብ አገናኝቷታል።


ሀዋሳዎች ወደ ተመሪነት ከመጡ በኋላ ጎል መፈለጋቸውን የሚያረጋግጡ ሁለት ቅያሪዎችን በአጥቂ ክፍላቸው ላይ አድርገዋል። አማካዮቹ አብዱልባሲጥ እና አዲሱን በሙጂብ እና ዓሊ ከተኩ ከደቂቃዎች መልስ የአቻነት ግባቸውን ወደ ካዝናቸው ከተዋል። 73ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ወደ ግብ ክልል ከእዮብ አለማየሁ የተላከችን ኳስ ሰዒድ ሀሰን ልክ እንደ ቀዳሚው አጋማሽ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ጨዋታውን 2ለ2 አድርጎታል። በቀሩት የጨዋታ ደቂቃዎች ሜዳ ላይ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውጪ ተጨማሪ ግብን ሳንመለከት ጨዋታው 2ለ2 ተቋጭቷል።

\"\"