ኢትዮጵያዊው ዳኛ የቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታን ይመራል

በዋይዳድ እና አልሀሊ መካከል የሚደረገውን ሁለተኛ ዙር የካፍ የ2023 የቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ በኢትዮጵያዊው ዳኛ ይመራል።

የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የ2023 የውድድር ዘመን ሲደረግ ሰንብቶ ወደ ፍፃሜው ተቃርቧል። በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በሚገኙ ክለቦች መካከል በምድብ ማጣሪያ እና በተለያዩ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ሲደረግ ቆይቶ በመጨረሻም ሁለቱን የመድረኩ ዝነኛ ክለቦች ለፍፃሜ አብቅቷል። በሁለት የደርሶ መልስ ውጤት ውድድሩን በበላይነት ለማጠናቀቅ የግብፁ ሀያል ክለብ አልሀሊ ከአምናው ሻምፒዮን የሞሮኮው ዋይዳድ አትሌቲክ ጋር የሚፋለሙ ይሆናል።
\"\"
ግንቦት 27 በግብፅ ካይሮ ስታዲየም ላይ የመጀመሪያው ዙር የፍፃሜ ጨዋታ በሊቪያዊው ዳኛ ኢብራሂም ሙታዛ ከተመራ በኋላ ሁለተኛ እና የመጨረሻው የፍፃሜ ጨዋታ በሞሮኮ ካዛብላንካ ሁለቱ ክለቦች ሰኔ 4 ዕለተ ዕሁድ በመሐመድ ቪ ኮምፕሌክስ ስታዲየም ሲጫወቱ ኢትዮጵያዊ አለም አቀፍ ዳኛ በአምላክ ተሰማ እንዲመራው በካፍ ስለ መመረጡ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። ከበአምላክ ጋር በረዳት ዳኝነት ካሜሮናዊው ጉይ ኤልቨስ ኖፓይ እና ኬኒያዊው ጊልቨርት ኪፕኮች ጋቦናዊው ፔር አትቾ በአራተኛ ዳኝነት በጣምራ ሲመሩት ከኬኒያ ፣ ዛምቢያ እና ሞሪታኒያ የቫር ዳኞች ተሰይመዋል።
\"\"
ከፈረንጆቹ አቆጣጠር 2012/13 ጀምሮ በካፍ ስር የተደረጉ 38 ጨዋታዎችን እስከ አሁን በዋና ዳኝነት የመራው በአምላክ ከፍተኛ ትኩረት የሚስበውን የፍፃሜ ጨዋታ ሲመራ 39ኛው ጨዋታው ሆኖ ይመዘገባል።