መረጃዎች | 97ኛ የጨዋታ ቀን

ነገ እንደሚደረጉ የሚጠበቁ የሊጉን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ ቅድመ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰባስበናል።

መቻል ከ ሀዋሳ ከተማ

አንድ ነጥብ እና ሁለት ደረጃዎች ብቻ የሚለያቸው መቻል እና ሀዋሳ ከተማ ከተመሳሳይ የሁለት አቻ ውጤት በኋላ በሚያደርጉት የእርስ በርስ ፍልሚያ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ከፍ ያለ ትግል እንደሚደረግበት ይጠበቃል።

ከሁለት ተከታታይ ድሎች በኋላ በሁለት ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻለው መቻል በሊጉ በወጥነት መጫወት አቅቶታል። በስብስብ ረገድ ጥራት ያላቸው ተጫዋቾችን በቡድኑ ቢይዝም በሁሉም የሜዳ ክፍሎች በየሳምንቱ የወጥነት ጥያቄዎች ሲነሱበት ይሰማል። ከምንም በላይ የአጥቂ መስመሩ ክፍተት የአደባባይ ሚስጥር ቢሆንም ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በወራጁ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለት ግቦችን አስተናግዶ ነጥብ መጋራቱ ከኋላም ጥያቄዎችን አስነስቶበታል። የነገ ተጋጣሚው ሀዋሳ ደግሞ በመከላከሉ ረገድ በቀላሉ ክፍተቶች የሚሰጥ ባለመሆኑ እንዲሁም በመልሶ ማጥቃት አደገኛ ስለሆነ የበለጠ እንዳይቸገር በከፍተኛ ትኩረት ጨዋታውን መቅረብ ይገባዋል።
\"\"
ያለፉትን ስድስት ጨዋታዎች ሙሉ ሦስት ነጥብ ማግኘት ያልቻለው ሀዋሳ ከተማ በመቀመጫ ከተማውም ውጤት እየቀናው አይገኝም። እርግጥ በስድስቱ ጨዋታዎች የገጠማቸው ቡድኖች አብዛኞቹ በሊጉ ጠንካራ የሆኑ ቢሆንም በጨዋታዎቹ በተለይ በሁለቱ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች የነበረው ስልነት እጅግ ቀንሶ ተስተውሏል። ለማሳያም በተጠቀሱት ጨዋታዎች 6 ግቦችን በድምሩ ሲያስተናግድ በተቃራኒው 3 ግቦችን ብቻ ተጋጣሚ ላይ አስቆጥሯል። የሆነው ሆኖ በቀጥተኛ እንዲሁም በፈጣን ሽግግር አጨዋወት የተካነው ቡድኑ ነገም መቻልን ለማሸነፍ የሚመርጠው ስልት ይሁ እንደሚሆን ይገመታል።

መቻል በነገው ጨዋታ የሁለት ተጫዋቾችን ግልጋሎት አያገኝም። የውድድር ዓመቱን ሙሉ ውጪ ከሆነው ፍፁም ዓለሙ በተጨማሪም ኢብራሂም ሁሴን በልምምድ ጉዳት አስተናግዶ ወደ አዲስ አበባ ለተሻለ ህክምና በመላኩ ከጨዋታው ውጪ ሆኗል። ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ ነገም የአማካዩ ብርሃኑ አሻሞን ግልጋሎት በጉዳት ምክንያት አያገኝም።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 31 ጊዜ ሲገናኙ ሀዋሳ ከተማዎች 14 እንዲሁም መቻሎች 8 ጊዜ ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን
የተቀሩት 9 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።

አርባምንጭ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

በወራጅ ቀጠናው የሚገኙት አርባምንጭ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሊጉ ያላቸው ዕቅድ ለየቅል ነው። አርባምንጭ በሊጉ ለከርሞ ለመጫወት የሚያስችለውን ነጥብ ለመሰብሰብ ወደ ሜዳ ሲገባ ኤሌክትሪክ በበኩሉ መውረዱን ባሳለፍነው ሳምንት በማወቁ ለክብር እና ለክብር ብቻ ጨዋታዎችን ያደርጋል።
\"\"
በሊጉ በርካታ የአቻ ውጤቶችን (14) ያስመዘገበው አርባምንጭ ከተማ ከቀናት በፊት ዋና አሠልጣኙን ከመንበሩ አንስቷል። የአሠልጣኝ ለውጡ የተደረገበት ጊዜ ብዙዎችን እያከራከረ ቢገኝም ከዚህ ቀደም በሁለት አጋጣሚዎች የቡድኑ ጊዜያዊ አሠልጣኝ ሆነው ያገለገሉትን በረከት ደሙ በቦታው ተሹመዋል። አዲሱ አሠልጣኝ ቡድኑ በየዲፓርትመንቱ ያለበትን ችግር በዚህች አጭር ጊዜ አሻሽለው ያቀርቡታል ተብሎ ባይጠበቅም በዋናነት በማጥቃቱ እንዲሁም መከላከሉ ላይ ያለውን ውስንነት ትኩረት ሰጥተው ያስተካክላል ተብሎ ይጠበቃል። የነገ ተጋጣሚው ደግሞ የወረደው ኤሌክትሪክ በመሆኑ በአንፃራዊነት ቀለል ያለ ፈተና ሊገጥመው እንደሚችል ይታሰባል።

በ25 ሳምንታት የሊጉ ጨዋታዎች ከአንድ በላይ ድል ማሳካት ያልቻለው ብቸኛው ክለብ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱን ካረጋገጠ በኋላ ነገ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደርጋል። ቡድኑ በውድድር ዓመቱ እጅግ የወረደ ብቃት ሲያሳይ ቆይቶ የነበረ ቢሆንም በመጨረሻው የመቻል ጨዋታ አንፃራዊ የሜዳ ላይ መሻሻል አስመልክቶ ነበር። ይህ ቢሆንም ግን የውድድር ዓመቱን ሙሉ ዋጋ ሲያስከፍለው የነበረው የኋላ መስመር ሽንቁር መውረዱን እንዲያፋጥን አድርጎበታል። ቡድኑ መውረዱን አረጋግጦ ነገ ወደ ሜዳ ስለሚገባ ምናልባት ከጫና ነፃ ሆኖ ሊጫወት ስለሚችል የአርባምንጭን ጊዜ ከባድ ሊያደርግም ይችላል።

የዘንድሮውን ጨምሮ ሁለቱ ቡድኖች 15 ጊዜ ተገናኝተዋል። ኤሌክትሪክ 6 ሲያሸንፍ አርባምንጭ 4 አሸንፏል። አምስት ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ኤሌክትሪክ 20 ሲያስቆጥር አርባምንጭ ከተማ 15 ማስቆጠር ችለዋል።