የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 0-0 ወላይታ ድቻ

\”ምንም እንኳን ዝናቡ ቆመ እንጂ ሜዳው ጉልበት እና ኃይል የሚጠይቅ ነው\” አሰልጣኝ ስዩም ከበደ

\”ሜዳው ከነበረበው ጭቃማነት አንፃር በጣም ጉልበት የሚጨርስ እና እልህ አስጨራሽ ነው\” አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም

ትናንት በዝናብ ተቋርጦ የነበረው እና ዛሬ ቀትር በሁለተኛው አጋማሽ በበርካታ ደጋፊዎች መካከል የተደረገው የሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ ያለ ጎል ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱም ቡድን አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታን አድርገዋል።

\"\"

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወላይታ ድቻ

ስለ ጨዋታው …

\”ጨዋታው ሁለት አርባ አምስት ደቂቃ ይሁን እንጂ ሜዳው ከነበረበው ጭቃማነት አንፃር በጣም ጉልበት የሚጨርስ እና እልህ አስጨራሽ ነው። ተጋጣሚያችን አራት ተከታታይ ጨዋታ አሸንፎ የመጣ ቡድን ነው ቀላል የሚባል አይደለም። ብዙ ደጋፊ ባለበት መጫወት በዕርግጥ የእኛም ደጋፊ አለ። ነገር ግን እልህ አስጨራሽ ነው እያሸነፈ የመጣ ሥነ ልቦና እና እኛ ደግሞ ትንሽ ነጥባችንን ከፍ ለማድረግ የምናደርግበት ስለ ነበረ የደርቢነት ስሜትም አለው እና ይህንን ታሳቢ አድርገን ነው ስንጫወት የነበረው እና ትላንትናም ዛሬም የተከተልናቸው ፎርሜሽኖች አሉ አዋጥቸውናል ከእኛ አንፃር ጥሩ ማለት ይቻላል\”።

ከትላንትናው አንፃር ዛሬ ስለ መዳከማቸው…

\”ትላንት አርባ አምስት ደቂቃ ይመስላል እንጂ ከዘጠና ደቂቃ በላይ ነው። 24 ሰዓት ሳናርፍ ነው የመጣነው እንግዲህ የማታ ጨዋታ ነበር ያደረግነው። ጫና አለ ከአመጋገብ አንፃር እነዚህ ሁሉ ሲደራረብ ፊዚካሊ ብቻም ሳይሆን የአዕምሮ ካልኩሌሽን ይኖራል የህዝብ አደራ ተሸክመን ነበር ስንጫወት የነበርነው። እነኚህም ግምት በማስገባት ነው ፤ ከእዚህ ጭቃስ ምን ይጠበቃል ? ከእልህ ከወኔ እና ከታታሪነት ውጪ ኳስ ተቆጣጥሮ መጫወት ምናምን ላይ የሚጠበቅብን አይመስለኝም።\”

ስለ ወራጅነት ስጋት …

\”እኛ ብቻ ሳይሆን 11 ክለቦች ይመለከተናል እኛ እንደውም ከዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ ወራጅ ቀጠና ውስጥ እየገባን አይደለም አራት ጨዋታ ነው የሚቀረው በካልኩሌሽን ደረጃ ከሆነ እያንዳንዱ ክለቦች ይመለከታቸዋል። ለብቻችን እኛ ላይ የደረሰ ነገር የለም እጃችን ላይ ያሉ ነጥቦች ናቸው አስተካክለን ውጤታማ እንሆናለን ፤ በዚህ ስጋት አይሆንብንም።\”

\"\"

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ – ሲዳማ ቡና

ስለ ጨዋታው…

\”ጨዋታው የአርባ አምስት ደቂቃ ህይወት ነው የነበረው ፣ ያለንን ነገር ማድረግ ነበር የፈለግውን አሸናፊነታችንን ማስቀጠል የተወሰኑ ጥሩ አጋጣሚዎችን አግኝተናል አላደረግነውም በአጠቃላይ የተደረገው እንቅስቃሴ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ።\”

የትላንቱ ጨዋታ ስለፈጠረው ተፅዕኖ…

\”በትክክል በሁለታችንም ደረጃ ከፍተኛ ፈክክር ነበር ፤ የወጣው ጉልበት ትልቅ ነው። ምንም እንኳን ዝናቡ ቆመ እንጂ ሜዳው ጉልበት እና ሀይል የሚጠይቅ ነው ይህንን ሁሉ ተቋቁሞ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ ትልቅ ነገር ነው ብዬ አስባለሁ።\”