የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 1-1 አርባምንጭ ከተማ

\”እኛ በጭቃ ሁለት ጊዜ ሁለት ቀን ሙሉ በተለያየ ቀን በተጫወትናቸው ጨዋታዎች ድካም አለብን\” ሥዩም ከበደ

\”ባለንበት ቦታ ተጫዋቾች በመጠኑ ስሜታዊ ሆነዋል\” በረከት ደሙ

ሥዩም ከበደ – ሲዳማ ቡና

ስለ ጨዋታው…?

\”ለእኛ በተለይ ወሳኝ ነው። ለእነርሱም ወሳኝ ነው። ከእኛ በበለጠ ትልቁ ነገር ሜዳችን ላይ አራት ጨዋታ አሸንፈናል ሁለት ጨዋታ አቻ ወጥተናል ይህ ትልቅ ስኬት ነው ሌላው ቀርቶ ከእኛ በታች እንኳን ያሉትን አርባምንጭ ዛሬ ቢያሸንፍ የበለጠ የመጠጋት ነገር ይኖረዋል የአዳማውን ቆይታ ሊያበላሽብን ስለሚችል እና ከእኛ በታች ያሉትን አምስት ነጥብ መራቅ በራሱ ትልቅ ኮንፊደንስ የሚሰጥ ነው። የሀዋሳ ውሏችን በአጠቃላይ ጥሩ ነው። የዛሬውም ጨዋታ ለሁላችንም አስፈላጊ ስለሆነ ያንን ጠብቆ ለመሄድ የተካሄደው እንቅሰቃሴ ትልቅ ነው ብዬ አስባለሁ።
\"\"
ከዕረፍት መልስ ስለ ነበራቸው የማጥቃት ድክመት…?

\”ፕላናችን በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ የበለጠ ብዙ ነገር አድርገን ለመጨረስ ነበር ያሰብነውና በሁለተኛው አጋማሽም ይሄንን ለማስቀጠል ፍላጎቱ አለን። አንዳንድ ጊዜ በተጫዋቾች ውስጥ የሚያድር ነገር አለ። ለእኛ አቻም ያለውን ልዩነት ሊያስጠብቅልን ስለሚችል ብዙ ነቅለህ መሄዱም አድቫንቴጅ የለውም። ከእዛ አኳያ ነው። እነርሱ ያላቸው ምርጫ አንድ እና አንድ በይበልጥ ማጥቃት ላይ መሄድ አለባቸው ስለዚህ በእዛ ባላንስ መካከል የሚደረጉ ነገሮች ናቸውና በአጠቃላይ ጥሩ ነገር ነው ያለው። ማሰብ ያለብን እኛ በጭቃ ሁለት ጊዜ ሁለት ቀን ሙሉ በተለያየ ቀን በተጫወትናቸው ጨዋታዎች ድካም አለብን። አርባምንጭ በጣም ነው የጠበቀን ይሄም በራሱ አንድ ተፅዕኖ አለው።\”

በረከት ደሙ – አርባምንጭ ከተማ

ከዕረፍት በፊት ስለ ነበራቸው ብልጫ እና ስለ አጠቃላይ እንቅስቃሴያቸው…?

\”ጨዋታውን ስገመግመው ሲዳማ ቡና ጠንካራ ተፎካካሪ ነው። ሰሞነኛ አቆሙም ይሄንን ይገልጻል። በተጨማሪም ደግሞ 12ኛ ተጫዋች ሆኖ የሚያግዘው ጠንካራ ደጋፊ አለው። ከእነርሱ ጋር ተጫውቶ በተገኘው አንድ ነጥብ ብዙም አልተከፋንም። እኛ የጨዋታ አቀራረባችን አሸንፎ ለመውጣት ነው። ማሸነፍ ለእኛ በጣም ወሳኝ ስለ ነበር አሸንፈን ለመውጣት ነበር ወደ ሜዳ የገባነው። በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ሀያ ደቂቃ ያንን የሚያሳይ ነገር አሳይተናል ጎልም አግብተናል። በተቃራኒው ሁለተኛ ጎል አግብተን ደጋፊውንም ሲዳማ ቡናንም ለማውረድ ያደረግነው ጥረት ባለ መረጋጋት አልተሳካም የትኩረት ማነስ በመጨረሻ ሽርፍራፊ የመጀመሪያ አርባ አምስት ሊያልቅ ጥቂት ሰከንዶች በቀሩበት ውስጥ የእኛ ተጫዋች በራሳችን ላይ አግብቷል። ይሄ በእግር ኳስ የሚሆን ነገር ስለሆነ እንቀበለዋለን።
\"\"
የሚስተዋሉ ያለመረጋጋቶች በቀጣይ ስለሚፈጥረው ስጋት…?

\”ያለ መረጋጋቶች ነበሩ በመጠኑ። ያለንበት ቦታ እጅግ አደገኛ ስለሆነ ከእዛ ለመውጣት ካለን ጥልቅ ጉጉት አንፃር አንዳንድ ጊዜ ስሜታዊ ያደርጋል ያለንበት ቦታና ተጫዋቾች በመጠኑ ስሜታዊ ሆነዋል። ሆኖም ከዕረፍት በኋላ ያንን ነገር አስተካክለን ተረጋግተን ተጫውተን ጎል ለማስቆጠር ጥረት አድርገናል። የእነርሱ የማጥቂያ መንገድ የቆመ ኳስ ላይ ብቻ ስለሆነ ያንን በደንብ እየተከላከልን መልሰን ለማግኘት ሞክረናልና በጨዋታው የተወሰነ ብልጫ ነበረን ብዬ አስባለሁ። ይሄንን ነገር ካስቀጠልን በዕርጋታ እየተጫወትን ነጥቦችን በደንብ በማግኘት ሊጉ ላይ ለመቆየት ጥረት እናደርጋለን።\”