የአሰልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 1-2 አዳማ ከተማ

\”ማሸነፍ አስበን ብቻ ነው የገባነው\”
አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ

\”እንደጠበቅነው ጨዋታው ጠንካራ ነበር\”
አሰልጣኝ አስራት አባተ

አዳማ ከተማ ከመመራት ተነስቶ ድሬዳዋ ከተማን ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱም ቡድን አሰልጣኞች ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጡት አስተያየት እንደሚከተለው ቀርቧል።

\"\"

አሰልጣኝ አስራት አባተ

ስለ ጨዋታው…

እንደጠበቅነው ጨዋታው ጠንካራ ነበር። በሁለታችን መካከል የነበረው የነጥብ ልዩነት ተቀራራቢ ስለነበር በአግባቡ ተዘጋጅተን ነበር። እንደ ዝግጅታችንም በግዜ ማግባት ችለናል። ሆኖም ጨዋታው ለማሸነፍ ከነበረው ጉጉት የማፈግፈግ ሁኔታዎች ታይተው ግብ ተቆጥሮብን ተሸንፈን ወጥተናል።

ከዕረፍት በኋላ ስለታየው መውረድ…

ከድክመት ሳይሆን ካለንበት የነጥብ ቅርርብ ውጤቱን ለማስጠበቅ ተጫዋቾቻችን አፈግፍገው በረጃጅም ኳሶች ሊያጠቁን ችለዋል። ያም ቢሆን ግን ከእነሱ የተሻለ ዕድሎች ፈጥረን ከግቡ ውስጥ የራሳችን ተጫዋች አውጥቶታል። ጨዋታውን የመግደል ዕድልም አግኝተን ነበር።

ወደ ክለቡ ከመጣ በኋላ ስለታየው ለውጥ…

ጥሩ ነው መጥፎ የሚባል አደለም። የዛሬው ጨዋታ ግን ማሸነፍ የምንችልበት ዕድል ነበር። ያ ባይሆን እንኳን አቻ ይገባን ነበር። ከግዜ ወደ ግዜ ግን ቡድኑ ላይ ዕድገት አለ።

አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ

ስለ ጨዋታው…

በመጀመርያው አጋማሽ የነበረው እንቅስቃሴያችን ጥሩ አልነበረም። ሁሌም የኛ ቡድን ከተነካ በኋላ ነው የሚነሳው ይሄ ደሞ ጥሩ ዕድል ነው። ማሸነፍ አስበን ብቻ ነው የገባነው። ሲገባብን ትንሽ ወርደን ነበር። ከዛ በኋላ ግን ከዕረፍት መልስ ያሳየነው ነገር ጥሩ ነው።

\"\"

ባለፉት ጨዋታዎች ስለነበረው ድክመታቸው…

ቡድናችን ሜዳ ይፈልጋል። ጥሩ ሜዳ ስያገኝ ጥሩ ይሆናል፤ አዳማም ባህር ዳርም ጥሩ ሜዳ ስለነበር ነው ጥሩ የነበርነው። አንዳንዴ ሜዳው መሰረት አድርገህ የአጨዋወት ለውጥ ማድረግ አለብህ። ከዚህ በፊት ከነበረው አጨዋወታችን ለውጥ አድርገን ነበር ስንጫወት የነበረው፤ ቀጥተኛ እና መከላከል ላይ ያዘነበለ። ዛሬ ግን ይህ አጨዋወት አዋጥቶናል።

ስለ ወጣት ተጫዋቾች…

ፉዐድ ከዚህ በፊት የተከላካይ አማካይ ላይ ተጫውቶ አያውቅም። ከዚህ በፊት ተከላካይ ነበር ፤ የቦታ ለውጥ አድርገውም ጥሩ ሲንቀሳቀሱ ከማየት የሚያስደስት ነገር የለም። ልምድ ያላቸውም ይረዷቸዋል፤ ሁሌም ወጣቶችን ማሰለፍ አትራፊ ያደርጋል።