ሪፖርት | አዳማ ከተማ የሀዋሳ ቆይታውን ከአምስት ጨዋታ በኋላ ባሳካው ድል ቋጭቷል

አዳማ ከተማ በሁለተኛው አጋማሽ ከጥሩ እንቅስቃሴ ጋር ታግዞ ከመመራት ተነስቶ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ድሬዳዋ ከተማን አሸንፏል።

ድሬዳዋ በፋሲሉ ድል ላይ ይዞት የገባውን አሰላለፍ ሳይለውጥ ለጨዋታው ሲቀርብ በአንፃሩ በለገጣፎ ሽንፈት ያስተናገዱት አዳማዎች የአምስት ተጫዋቾችን ቅያሪ አድርገዋል። እዮብ ማቲዮስ ፣ ዳንኤል ደምሱ ፣ አማኑኤል ጎበና ፣ ቦና ዓሊ እና ቢኒያም አይተንን በአዲሱ ተስፋዬ ፣ አድናን ረሻድ ፣ ፉዓድ ኢብራሂም ፣ ዮሴፍ ታረቀኝ እና አሜ መሐመድ ተክተዋቸዋል።

\"\"

አሰልቺ የጨዋታ መልክ የነበረው እና ግልፅ የግብ ዕድልን ለመመልከት ሰላሳ ደቂቃዎች ለመሻገር የተገደድንበት የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያው አርባ አምስት ተመሳሳይ የጨዋታ ቅርፅን ቡድኖች ሲከተሉ የተስተዋለ ሲሆን በአንፃራዊነት ስህተት ይሰሩ የነበሩት የአዳማ ተከላካዮች ድሬዳዎች ኳስን በሚይዙበት እና ለማጥቃት በሚዳዱበት ወቅት ይበልጥ ተጋላጭነቸው ጎልቶ ይነፀባረቅ ነበር። በቅብብል ወቅት የሚፈጠሩ ክፍተቶች ለመጠቀም ካልሆነ በስተቀር ልዩነቶች ጎልተው ባልወጡበት ጨዋታ አዳማዎች አቡበከር በተሰለፈበት የቀኝ የሜዳው ክፍልን ለመጠቀም አልመው የነበረ ቢሆንም የመጨረሻው የኳሱ መድረሻ ግን የሚባክን ነበር።

\"\"

በአንፃሩ ጨዋታው 30ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ በተሻለ እየነቁ የመጡት ድሬዎች ጎል አስቆጥረዋል። ሱራፌል ጌታቸው በጥሩ ዕይታ ወደ ግራ የለቀቀለትን ኳስ አብዱለጢፍ መሐመድ ወደ ግብ ክልል መሬት ለመሬት ሲልካት ዩጋንዳዊው አጥቂ ቻርለስ ሙሰጊ ወደ ጎልነት ለውጧታል። ይህቺ ግብን በአጋማሹ ብቸኛ ሙከራ ሆና ወደ ጎልነት የተለወጠች አጋጣሚም ነበረች። ድሬዎች ዳዊት እስጢፋኖስን በጉዳት ካጡ በኋላ ቢኒያም ጌታቸውን ቀይረው በማስገባት ከለውጡ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ በተቀያሪው የግብ ዕድልን አግኝተው ኳሷ ወጥታበታለች። በብዙ ረገድ አቀራረቡ ወረድ ያለው አጋማሽም በድሬዳዋ 1ለ0 በሆነ ውጤት ወደ መልበሻ ቤት አምርቷል።

\"\"

ጨዋታው ከዕረፍት መልስ ሲቀጥል አዳማ ከተማዎች በብዙ ረገድ ከመጀመሪያው አጋማሽ ድክመታቸው በሚገባ ተሻሽለው ቀርበዋል። ኳስን ከመሐል ክፍሉ ወደ መስመር በመለጠጥ ወደ ውስጥ በጥልቅ አጨዋወት ለመጫወት የሚጥሩት አዳማዎች ተደጋጋሚ ጫናዎችን ጥንቃቄን መርጠው ለመጫወት በሞከሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ላይ ወስደዋል። በመጀመሪያ ሙከራቸው 51ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ በጥሩ የጨዋታ ፍሰት የደረሰውን ወደ ጎል ሲመታ በተከላካዮች ተደርባ ስትመለስ መስዑድ ጋር ደርሳ ወደ ውስጥ ተጫዋቹ ሲያሻግር ዮሴፍ ታረቀኝ በግንባሩ ገጭቶ ተከላካዮች ተደርበው ወደ ውጪ አውጥተውበታል። በቀዳሚው አጋማሽ በተሻለ የጥቃት ተሳትፎ የነበራቸው ድሬዳዋ ከተማ በዚህኛው አጋማሽ ኳስን ሲያገኙ ከሚያደርጉት የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ውጪ የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴያቸው የተበራከተ ሆኗል። በአንፃሩ በዳዋ እንዲሁም ዮሴፍ በግራ እግሩ ወደ ጎል ከላካት እና ዳንኤል ከያዛበት ሙከራ በኋላ እንዳደረጉት ጥረት ጎል አስቆጥረዋል።
\"\"

ከማዕዘን ዮሴፍ አስጀምሮ አድናን ወደ ውስጥ ያሻማለትን ኳስ ተጠቅሞ አቡበከር ወንድሙ በግንባር ከመረቡ ጋር ቀላቅሏታል። ከቆመ የቅጣት ምት ኳስ 72ኛው ደቂቃ ላይ ጋዲሳ መብራቴ ሲያሻማ እያሱ ለገሠ በግንባር ገጭቶ ወደ ጎል እየተንደረደረች ያለችን ኳስ የድሬዳዋው አጥቂ ቢኒያም ጌታቸው ቡድኑ ወደ መሪነት ሊመጣ የሚችልበትን አጋጣሚ ከጎል ስር አውጥቷታል። ጨዋታውን በራሳቸው ቁጥጥር ስር አድርገው የቀጠሉት አዳማዎች 78ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ወደ ጎል መቶ ዳንኤል ሲተፋት በድጋሚ ቢኒያም አግኝቶ አስቆጠረ ሲባል ተከላካዮች ተጋግዘው አውጥተዋታል። የአዳማን ጥቃት መከላከል በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ፍፁም እየከበዳቸው የመጡት ድሬዳዎች 82ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ፣ ቢኒያም እና አድናን በጥሩ ፍሰት ጎል ጋር የደረሰችን ኳስ ሦስቱም አከታትለው ሞክረው ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ መመከት ቢችሉም በአራተኛ ሙከራ ዮሴፍ ታረቀኝ ጎል አድርጓታል። ከጎሏ በኋላ ጉዳት የገጠመው ግብ ጠባቂው ዳንኤል በፍሬው ተተክቶ ወጥቷል።

\"\"

በመጨረሻዎቹ የጨዋታ ደቂቃዎች ከዳኛ ጋር ሰጣ ገባ ውስጥ የገባው የአዳማው አድናን ረሻድ በሁለት ተከታታይ ቢጫ ከሜዳ በቀይ ከወጣ በኋላ ጨዋታው በአዳማ 2ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።