የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 3-1 ወላይታ ድቻ

\”ተጫዋቾቹ ነጥብ እያሰሉ ስለሚጫወቱ ከዛ ጫና መውጣት አለብን ብዬ ነው የማስበው።\” – አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም

\”ዛሬ ቡድናችን እጅግ በጣም ጥሩ ነበር።\” – አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወላይታ ድቻ

ስለ ጨዋታው…

\”የቡድናችን አጨዋወት በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ በጣም ጥሩ ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ የተቆጠረብን የሙጅብ ጎል ብዙ ነገር ቀይሮብናል። በዛ ተረብሸን ነበር ወደ መልበሻ ክፍል ያመራነው።\”

ተከላካይ መስመር ላይ ስለታየባቸው ክፍተት…

\”እነሱ የሚጫወቱት በመልሶ ማጥቃት እንደሆነ ስለሚታወቅ ተነጋግረን ነበር። በሚከፈቱ ቦታዎች ነው እነሱ የሚያጠቁት ያው እነዛን ቦታዎች ስለለቀቅንላቸው እና ያሰብነውን ስላልተገበርን ነው። ዞሮ ዞሮ ግን እንደ ቡድን የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ጥሩ ነበርን። ያ ጎል ብዙ ነገር ቀይሮብናል ብዬ ነው የማስበው።\”

\"\"
ስለታየባቸው አለመረጋጋት…

\”ያው እንግዲህ ውድድሩ እያለቀ ስለሆነ የሚያመጣው ጫና ይኖራል። ከዛ ውጪ ምንም የለም። እያለቀ ስለሆነ ተጫዋቾቹም ነጥብ እያሰሉ ስለሚጫወቱ ከዛ ጫና መውጣት አለብን ብዬ ነው የማስበው።\”

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

\”በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ባለፈው የነበረው በእንቅስቃሴ ያገኘነው አጋጣሚ ባለቀ ሰዓት ግብ ስለተቆጠረብን የተጫዋቾቹ ስነ ልቦና ላይ ፍርሃቱ ይታይ ነበር። ነገር ግን ተጫዋቾቻችንን በተደጋጋሚ እየጠራን አስተካክለነዋል። እየተስተካከሉ ሲመጡ ግን ባለፈው የነበረውን እንቅስቃሴ መልሰው ነው ያገኙት እና ከዚህ በላይም ማስቆጠር ይቻል ነበር። በአግባቡ ነበር ተጭነን የምንጫወተው በተለይም ከዕረፍት በኋላ ትክክለኛ እና ቡድናችንን የሚገልጽ ነበር። ስንከላከልም ቅብጠት የለም በትክክል ነበር የተከላከልነው። ከዛ ውጪ ሙጅብ ዛሬ የሰጠሁት ሚና ሦስት ዓይነት ነው። በመጀመሪያ ላይ የፊት አጥቂ ነበር። በሁለተኛ ደረጃ ግቦችን ሲያስቆጥር ግን ከአጥቂ ጀርባ ሆኖ ነው ሲጫወት የነበረው። መጨረሻ ላይ ደግሞ የተከላካይ አማካዩን ስንቀይር እሱን ነው በዛ ቦታ ያደረግነው እና የሙጅብ አስተዋጽኦ እጅግ የሚገርም ሆኖ የታየበት ነበር። እውነት ለመናገር ዛሬ በእንቅስቃሴ ሜዳው ላይ ብልጫውን ወስዶ ቡድናችን አሸናፊ እንዲሆን ያደረገው እሱ ነው። ቡድናችን ዛሬ የነበረው እንቅስቃሴ እጅግ በጣም አሪፍ እና ለማሸነፍ የነበረን ፍላጎት ከፍተኛ የነበር ሲሆን ደጋፊዎቻችን ፊት ቢያንስ በድል መጨረስ አለብን ብለን በሁለት ጨዋታዎች ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ደጋፊዎቻችን አዝነው ነበር የወጡት እና ዛሬ ቢያንስ በዛ ልክ ተደስተው እንዲሄዱ ነው ያደረግነው። ከዛ ውጪ ሌላው ፍርሃታችን በተደጋጋሚ ከወላይታ ድቻ ጋር በምናደርገው ጨዋታ ላይ ግብ እናስቆጥር እና በመጨረሻ ደቂቃ አግብተው አቻ ነበር የምንሆነው እና ያ ፍርሃቱ ነበር። ሦስተኛው ግብ እስኪገባ ያ ስሜት ነበር ግን ልክ ሦስተኛው ግብ ሲገባ ከዛ በላይ አራት እና አምስት ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ዕድሎችን አልተጠቀምንም እና ዛሬ ቡድናችን እጅግ በጣም ጥሩ ነበር ብዬ ነው የማስበው።\”

\"\"
ዛሬ ተሻሽሎ ስለቀረበው የአማካይ ክፍል…

\”አማካይ ክፍላችን ላይ ወንድማገኝ ኃይሉ እና ብርሃኑ አሻሞ መጎዳታቸው ቡድናችንን አጉድሎታል ምክንያቱም ቋሚ ተሰላፊ የነበሩ ናቸው። አሁን ያደረግነው ምንድነው አጥቂዎችን ወደ መሃል አስገባናቸው በሁለቱ ጨዋታ ላይ ሙጅብን ወደ መሃል አዘንብሎ እንዲጫወት ነበር ያደረግነው። ለዛም ነው መሃላችን አሁን እየተስተካከለ የመጣው ብዬ ነው የማስበው። ምክንያቱም በተደጋጋሚ ከሙጅብ ጎሎችን እንፈልግ ስለነበር ወደፊት ስንወስድ ኳሶች አይደርሱም ነበር ዛሬ ራሱ አድራሽ ሆኖ በሚያገኘው አጋጣሚ ሲሄድ ነበር እና የተስተካከለውም በዛ ምክንያት ነው።\”