ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ታርቋል

ሀዋሳ ከተማ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት የመጀመሪያ ሦስት ነጥቡን ወላይታ ድቻን 3ለ1 በመርታት አስመዝግቧል።

ሀዋሳ ከተማ በመጨረሻ ደቂቃ ግብ ተቆጥሮበት ነጥብ ከተጋራው የመቻሉ ጨዋታ የአንድ ተጫዋች ለውጥ አድርጎ ጀምሯል። በለውጡም በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቶ በነበረው ግብ ጠባቂው መሐመድ ሙንታሪ ምትክ አላዛር ማርቆስን በብቸኝነት ሲለውጡ ከሲዳማ ቡና ጋር ያለ ጎል አጠናቀው የነበሩት ወላይታ ድቻዎች ምንም ቅያሪን ሳያደርጉ ለጨዋታው ቀርበዋል።

\"\"

የጨዋታው ሀያ ያህል ደቂቃዎችን በኮሪደር በኩል ለማጥቃት ይሞክሩ የነበሩት ድቻዎች በተሻለ የሜዳ ቆይታ ያደረጉበት ነበር ማለት ይቻላል። ጨዋታው ተጀምሮ 2ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ሁለት ቅብብል ከግራ በኩል አበባየው አጂሶ ያገኘውን ወደ ጎል ሲመታው ግብ ጠባቂው አላዛር ማርቆስ በጥሩ ቅልጥፍና ባወጣበት አጋጣሚ ጥራት ያላት አጋጣሚን ቡድኑ መፍጠር ችሏል። የሜዳውን ክፍል በአግባቡ በመለጠጥ በሒደት በመስመር ከሚደረጉ መነሻዎች አልፎ አልፎ ተሻጋሪ ኳሶችን ይጠቀሙ የነበሩት ድቻዎች በዘላለም ፣ ቢኒያም እና ቃልኪዳን የመጨረሻ ዕድሎችን በማግኘት ቀዳዳ ለመፈለግ ጥረት አድርገዋል። ኳስን ከራስ ሜዳ ለመጀመር አስበው ይጫወቱ የነበሩት ሀዋሳዎች በበኩላቸው የሚያደርጓቸው ቅብብሎች በተደጋጋሚ ወደ ወላይታ የሜዳ ክፍል ለመግባት ሲጥሩ በተደጋጋሚ ይቋረጡባቸው ስለነበር እነኚህም የሚቋረጡ ኳሶች ለወላይታ የሽግግር አጨዋወት አመቺ ነበሩ። 14ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ሳሙኤል ከርቀት የተገኘችን ቅጣት ምት ወደ ግብ አክርሮ ሲመታ ግብ ጠባቂው ቢኒያም በመሳሳቱ ተባረክ ሊያገኛት ሲቃጣ መልካሙ ደርሶ ያወጣበት የሀዋሳ ቀዳሚዋ ዕድላቸው ነበረች።


ከአንድ ደቂቃ በኋላ በረከት በድጋሚ ከቅጣት ሞክሮ ኤፍሬም በግንባር ገጭቶ ቢኒያም ከያዘበት ሙከራ በኋላ በተሻለ ጥቂት የማጥቃት ተሳትፎ የነበራቸው ሀዋሳዎች በሦስተኛው ሙከራ ግብ አስቆጥረዋል። ወላይታ ድቻዎች ከራሳቸው ሜዳ ለቀው በወጡበት ቅፅበት 26ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ዓሊ ሱሌይማን ከግራ ወደ ውስጥ ሲያሻማ ሙጂብ በግንባር ቢኒያም መረብ ላይ አሳርፏታል።


የዓሊን ግልጋሎት በደንብ መጠቀም ከጀመሩ በኋላ ወደ ጨዋታ በይበልጥ እየገቡ የመጡት ሀዋሳዎች 42ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስተናግደዋል። ከሀዋሳ ተከላካዮች ኳስን የታገለው ቢኒያም ፍቅሬ የሰጠውን ቃልኪዳን ዘላለም በቀላሉ ጎል አድርጓት ጨዋታው 1ለ1 ሆኗል። ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ ምላሽ ለመስጠት ሦስት ደቂቃ ብቻ የበቃቸው ሀዋሳ ከተማዎች ከዓሊ መነሻዋን አድርጋ ተባረክ የጨረፈለትን ሙጂብ ቃሲም ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አድርጎ ጨዋታው በ2ለ1 ተጋምሷል።


ከዕረፍት እንደተመለሰ ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ ወላይታ ድቻዎች ያስጀመሩ ቢሆንም ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር በመጠኑ መቀዛቀዞች ተስተውለውበታል። ጥንቃቄ አዘል የጨዋታ መንገድን ተከትለው ነገርግን ኳስን በሚይዙበት ወቅት መልሶ ማጥቃት የሚጠቀሙት ሀዋሳ ከተማዎች አጋማሹ እንደተጀመረ ከርቀት በዓሊ አማካኝነት ሙከራን አድርገው ነበር። ወላይታ ድቻዎች የጨዋታው ሰዓት እየገፋ ሲመጣ የአጥቂ ቁጥራቸው በማብዛት ተጫዋቾችን ቀይሮ በማስገባት ወደ አቻነት ለመሸጋገር በብርቱ ጥረት ቢያደርጉም የአጥቂዎቻቸው የውሳኔ አሰጣጥ ደካማ ይዘት ይታይባቸው ነበር።


በቃልኪዳን ፣ ስንታየው እና ዮናታን አማካኝነት በሚሻገር ኳስ ጥራት ያላቸውን ዕድሎች ለመፍጠር በመጨረሻዎቹ ሀያ ደቂቃዎች ቡድኑ በትጋት ቢጫወትም የሀዋሳን ጠጣር የመከላከል አጥር ሰብሮ ለመግባት ሲቸገሩ ተስተውሏል። በአንፃሩ እዮብ እና አዲሱን ቀይረው ወደ ሜዳ ካስገቡ በኋላ ወደ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች መነቃቃት ውስጥ የገቡት ሀዋሳዎች ጎል አስቆጥረዋል። 82ኛው ደቂቃ ላይ እዮብ አለማየሁ የሰጠውን ኳስ የወላይታ ድቻ ተከላካዮች ስህተት ታክሎበት በጨዋታው ልዩ የነበረው ዓሊ ሱለይማን ጎል አድርጓት በመጨረሻም በሀዋሳ 3ለ1 ድል አድራጊነት ጨዋታው ተቋጭቷል። ድሉም ለሀዋሳ ከሰባት ጨዋታዎች መልስ የተገኘች ድል ሆናለች።

\"\"