“ትልቅ ዋጋ ከፍለን ነው የገባነው ፤ ቀጣይም ምንም የምጠራጠረው ነገር የለኝም ” አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ

ሀምበሪቾ ዱራሜን ባለፈው ዓመት ተረክበው በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ካሳደጉት አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ ጋር ሶከር ኢትዮጵያ ቆይታን አድርጋለች።

ሀምበሪቾ ዱራሜ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ 2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ ቡድኑን በመምራት በሊጉ ላይ መታየት እንዲችል በዋና አሰልጣኝነት በመምራት ለስኬት አብቅተውታል። ሀምበሪቾ ዱራሜን ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ በዋና አሰልጣኝነት ተረክበው ለመውረድ ሲዳዳ የነበረው ቡድን በሊጉ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ እንዲያጠናቅቅ በማድረጋቸው በክረምቱ ክለቡን በዘንድሮው ዓመትም እየመሩ እንዲቀጥሉ በመመረጣቸው ቡድኑን እየመሩ በከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ስር ተደልድለው ከገላን ከተማ ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው በመጨረሻም ወደ ትልቁ የሀገሪቱ የሊግ ዕርከን ከፍ እንዲል አድርገውታል። ቡድኑን ከተረከቡ አንስቶ በ33 ጨዋታዎች አንድም ሽንፈት ሳይገጥመው ጥቂት ግቦችን አስናግደው ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማሳደግ የቻሉት አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ ስለ ውድድር ዓመቱ ጉዞ እና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታን አድርገዋል።

\"\"

ስለ ውድድር ዓመቱ ጉዞ…

\”በቅድሚያ ስለጋበዛችሁኝ አመሠግናለሁ። የውድድር ዓመቱ ከመጀመሪያው ጀምሮ በጣም ጥሩ ነው። 2014 ግማሽ ላይ ነው ቡድኑን የተቀላቀልኩት። በዛም ጥሩ ጊዜ አሳልፈን ከወራጅ ቀጠናው ተነስተን ሦስተኛ ወጥተናል። ዘንድሮ ደግሞ በጣም ጠንካራ ነው። ከፍተኛ ሊግ እንደሚታወቀው ሁሉም ክለብ ጠንካራ ነው። ዘንድሮ ደግሞ ለየት የሚያደርገው ወራጁ አምስት ቡድን ነው ፤ ውድድሩም ፈታኝ ነበር። በዚህ ውስጥም እግዚአብሔር ረድቶን ከባድ ውድድር ቢሆንም አሸንፈን ገብተናል።\”

ተፎካካሪያቸው ስለነበረው ገላን እና ሌሎችም ቡድኖች…

\”መጀመሪያ ላይ ጠንካራ ከላይ የነበሩት እነ ደሴ እነ አርሲ ነበሩ። ገላን እንደውም ወደ ታች ነበር። ከዛ ነው ወደ ፉክክር የመጣው ከመጀመሪያው ጀምሮ ስንመራ የነበረው እኛ ነን። ኮልፌም ከላይ ነበር በኋላ ነው ገላን የመጣው እና እውነትም ወደ መጨረሻ እኛን መከተል የጀመረው ገላን ነው እና በጣም ጠንካራ ቡድን ነው። ከምልህ በላይ ሁሉም ከፍተኛ ጥንካሬ አላቸው። የኛ በአብዛኛው 2014 ዓመት ላይ የነበረው ቡድን ነው የተወሰኑ ተጫዋቾች ጨምረን ወደዚህኛው ዓመት የመጣነው። የግድ አንድ ቡድን ብቻ እንደማለፉ ጥንቃቄ የግድ ነበርና ምንም ዓይነት ጨዋታ መሸነፍ የለብንም በሚል ተነጋግረን በዛም ጥሩ ዝግጅት አድርገናል። ጥሩ የመዘጋጃ ጊዜ አግኝተንም ሠርተናል። ውድድሩ እንደታየው ከመጀመሪያው ጀምሮ ፉክክር የነበረበት ነው። በኋላ ላይ ደግሞ እነ ገላን እና እነ ደሴ ነበሩ እና ግን በዛም ሁኔታ ውስጥ አንድም ቡድን በአንድ ነጥብ በልጦን ከላያችን አልሆነም። ከመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ጀምሮ መርተን መጨረሳችን ደሞ ጠንካራ ያደርገናል። ሁለተኛ ዙር ላይ ግን ገላን ጠንካራ ነው በብዙ መንገድ መጥቷል እንዲህ እንዲህ ማለት ባልፈልግም ጠንካራ ተፎካካሪ ነው። እሱን ስል ሌሎችን እየዘነጋሁ አይደለም። እነ ደሴ ፣ አርሲ ነገሌ ፣ ኮልፌ ሁሉም ጥሩ ቡድኖች ናቸው። በዚህ ውስጥ ግን መጨረሻ ላይ ገላን ተለይቶ ወደ ላይ መጣ እኛ ጋር አንድ ላይ ከላይ ነበርን። ዕኩል ሆነን በጎል በልጦንም ያውቃል። በዛ ውስጥ ግን ጥንቃቄ አድርገን የዋንጫ ጨዋታ ያልነው እና የሚገባውን የሚለየው ጨዋታ እኛ እና ገላን የምንገናኝበትን ጨዋታ ነው። ያንንም ጥሩ ተጫውተን ማሸነፋችን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ እንደምንገባ ፍንጭ የሰጠን ቀን ነው።\”

\"\"

ቡድናችሁ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የማደጉ ሚስጥር ምንድን ነበር…

\”የቡድናችን ጥንካሬ አንድነታችን ነው። ከምልህ በላይ ፍቅር አለ ቡድኑ ውስጥ እና ሌሎች ቡድኖችም የኛን ፍቅር በማየት የሚያመሰግኑበት አጋጣሚ ነበር። ሌላው ተጫዋቾቹ ሜዳ ውስጥ ዲስፕሊንድ ናቸው። ሜዳ ላይ ስንገባ መሥራት ያለብንን ነው የምንሠራው ማንም ከእንቅስቃሴያችን የሚወጣ አይኖርም። ቡድናችን የሚፈልገውን ነገር ለመሥራት ሁሉም ዝግጁ ናቸው። ከዛ ባለፈም ከሜዳ ውጪ ያለን ህብረት በጣም ጥሩ ነው። ለስኬታችንም ከዝግጅት ጀምሮ ቡድኑ ጠንካራ እንዲሆን የአቋም መለኪያዎች ተዘጋጅተውልን በደንብ ተዘጋጅተናል። ምናልባት እዛ ጋር የተሠራው ትልቅ ሥራ ዞኑም የቡድኑ አመራሮችም አጠቃላይ ሁሉም ዝግጅታችንንም ዝዋይ ነው ያደረግነው። የከተማ ዋንጫ ዝዋይ መጥተን ተጫውተናል። እነዚህ እነዚህ ምናልባት ዘንድሮ ላመጣነው ውጤት ተደማምረው ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ። በዚህ አጋጣሚ ይህንን ሁሉ ነገር ላመቻቹልን አመራሮች ፣ ዞኑ ፣ ቦርዱ ሁሉንም ማመስገን እፈልጋለሁ።\”

በፕሪሚየር ሊጉ ላይ ተጠናክሮ ለመቅረብ መሰራት ስላለባቸው ነገሮች…

\”በአብዛኛው ጊዜ ከላይ ሲመጣ በዚህኛው መንገድ አይደለም የምትሄደው እና ፕሪምየር ሊግ ራሱን የቻለ ፎርማት ነው። ስለዚህ ይህንን ለማስተካከል ቅድመ ዝግጅቶች በጊዜ መሆን አለባቸው ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ጥሩ ስብስብ ጥሩ ዝግጅት ሊኖርህ ይችላል ግን ሥራው ደግሞ አሁን ጨርሻለሁ ብለህ የምትቀመጥበት አይደለም። አሁኑኑ የቡድን ስብስብ ማስተካከል በዚህ አጋጣሚ ቡድናችን ሀምበሪቾ ብዙ ጠንካራ ተጫዋቾች ያሉት ነው። ምክንያቱም ውድድሩም ላይ በሦስቱም ምድቦች ካሉት 41 ቡድኖች ትንሽ ግብ የተቆጠረበት የኛ ቡድን ነው። ቡድናችን ጠንካራ መሆኑን ለመግለጽ ነው እና ፕሪምየር ሊግ ደግሞ ከዚህ የተሻለ መቅረብ ያለብህ ውድድር ስለሆነ ምናልባት ይሄን ሥራ እየሠሩ ነው ብዬ አምናለሁ። ለዚህ ደግሞ ሥራው በቶሎ መጀመር ካልቻለ ትንሽ ሊከብድ ይችላል እና ምናልባት እዛ ላይ አሁን እየሠሩ ነው እላለሁ ምክንያቱም የዝግጅት ወቅትን በጊዜ አድርገን የወዳጅነት ጨዋታዎችም አድርገን ጨርሰን ነው ወደዛ መሄድ ያለብን እንጂ ምናልባት መጨረሻ ላይ የምታደርገው ነገር እንደ ለገጣፎ እና ኤልፓ ሊገጥም ይችላል። ያ እንዳይሆን ግን ሁሉም ነገር ተስተካክሎ የሚሆንበትን መንገድ ከቡድኑ ጋር አውርተናል። ምናልባት ይሄም በቶሎ ይከውናሉ ብዬ አስባለሁ። በዚህ አጋጣሚ ግን ቅድም ያልጠቀስኩት የቡድናችን ጥንካሬ የደጋፊዎች ድባብ ምናልባት ፕሪሚየር ሊግ ላይ የሚታይ ደጋፊ ድባብ ያለው ከፍተኛ ሊጉ ላይ ሀምበሪቾ ነው። እነሱንም በጣም በጣም አመሠግናለሁ።\”

\"\"

ከሀምበሪቾ ጋር በፕሪምየር ሊጉ…

\”እስካሁን ቡድኑ ጋር ውል አለኝ። ቡድኑን አስገብቻለሁ ያም የሆነው ሠርተን ነው። ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ በቀላሉ የምትገባበት አይደለም። ትልቅ ዋጋ ከፍለን ነው የገባነው ቀጣይም ምንም የምጠራጠረው ነገር የለኝም። ከሀገር ውስጥም ከውጪም ላሉት የተሻለውን ሀምበሪቾ ለመሥራት እኔ በበኩሌ ዝግጁ ነኝ። በእርግጠኝነት የምናገረው ሕዝቡም ጥሩ ነገር ነው ያለው። ምክንያቱም ይህንን የምልህ ፕሪሚየር ሊግ ስንገባ ያየነው ነገር አለ ፤ በአካልም ጭምር ያወራነው ነገር ስላለ በጣም ጥሩ ነገር ነው። ሌላው ትልቁ ደግሞ የዞኑ አስተዳደርም በጣም ለስፖርቱ ቅርብ የሆነ ነው። ሁሉንም ነገር እያደረገ ለዚህ ውጤት አብቅቶናል። ሁሉንም አካላት ማመስገን እፈልጋለሁ ስለዚህ ቀጣይም ከሀምበሪቾ ጋር ጥሩ ነገር እሠራለሁ ብዬ ነው የማስበው።\”