ሪፖርት | ፋሲል እና መድን ነጥብ ተጋርተዋል

በሁለት አጋማሾች ሁለት መልክ የነበረው የፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ መድን ጨዋታ ያለጎል አቻ ተደምድሟል።

\"\"

ባሳለፍነው ሳምንት ከወልቂጤ ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ የተለያየው ፋሲል ከነማ አስቻለው ታመነን ብቻ በዱላ ሙላቱ ተክቶ ወደ ሜዳ ሲገባ በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን 2ለ1 የረታው ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ ሦስት ነጥብ ካገኘበት ጨዋታ ምንም የተጫዋች ለውጥ ሳያደርግ ጨዋታውን ጀምሯል።

በቀዝቃዛማው የዐየር ሁኔታ ታጅቦ መደረግ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እንደ ዐየር ሁኔታው ቀዝቃዛ ነበር። በጨዋታውም በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ የጠሩ የግብ ማግባት ሙከራዎች ሲደረጉ አልነበረም። በአንፃራዊነት በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ከኳስ ጋር የተሻሉ የነበሩት ኢትዮጵያ መድኖች ከቆመ ኳስ ሁለት ሙከራዎችን ሩብ ሰዓት ሳይሞላ አድርገዋል። የጨዋታውን የኳስ ቁጥጥር ወደ ራሳቸው ያመጡት ፋሲል ከነማዎች ቀስ በቀስ የመድንን የአማካይ መስመር ብልጫ እየወሰዱ መንቀሳቀስ ቢጀምሩም ማጥቃቱ ላይ መሳሳት ነበረባቸው።

አሰልቺው ጨዋታ ምንም እንኳን ዒላማውን የጠበቀና ግብ ጠባቂን የፈተነ ባይሆንብ በ43ኛው ደቂቃ በአንፃራዊነት ደህና የሚባል ሙከራ አስተናግዷል። በዚህም የፋሲል ከነማ አምበል ሱራፌል ዳኛቸው ከርቀት የሞከረው ኳስ ለግብ በቀረበ ሙከራነት ተይዞ የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቋል።

አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያስተናግድ የቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ በፋሲል በኩል ጥቃት ታይቶበታል። በዚህም የመጀመሪያው አጋማሽ ሊገባደድ ሲል ሙከራ ያደረገው ሱራፌል በመድን የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ተገኝቶ ጥሩ ዕድል ፈጥሮ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ መልሶታል።

ጨዋታው 51ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ የመጀመሪያው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ተደርጓል። በተጠቀሰው ደቂቃም ባሲሩ ዑማር ከሳጥን ጫፍ አክርሮ የመታው ኳስ ለግብነት ቀርቦ ነበር። ፋሲሎች ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ወዲያው ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ምላሽ ሰጥተው ነበር። የአጥቂ አማካዩ ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ ከኦሴ ማውሊ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ልኮ ለጥቂት ወጥቶበታል።

ከመጀመሪያው ግማሽ ፍፁም የተሻሻለው ይህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በ60ኛው ደቂቃ መሪ ሊያገኝ ነበር። በዚህም ሳይመን ፒተር ፈጣን የተከላካይ ጀርባ ሩጫ አድርጎ ከሚኬል ሳማኪ ጋር ቢገናኝም የመጨረሻ ውሳኔው ላይ ግብ ጠባቂው እና አስቻለው ጫና አሳድረውበት ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ከአስር ደቂቃም በኋላ በቁጥር በዝተው የወጡትን ፋሲሎች ለመቅጣት በረጅን ኳስ የከድር ኩሊባሊ ስህተት ታክሎበት ሲሞን እና ሀቢብ ሌሎች ሙከራዎችን አከታትለው ሰንዝረዋል።

ከሱራፌል የሚነሱ ስል የማጥቃት አጨዋወቶችን በመጠቀም የመድንን ግብ ለመጎብኘት የጣሩት ፋሲሎች በ72ኛው ደቂቃ በአምበላቸው ጥብቅ ኳስ ቀዳሚ ሊሆኑ ነበር። በ82ኛው ደቂቃም ከቀኝ መስመር ሌላ ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ በዓለምብርሃን አማካኝነት ሰንዝረው ተመልሰዋል። ሙሉ ጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ ሦስት ደቂቃዎች ሲቀሩትም ተቀይሮ የገባው ያሬድ ዳርዛ የማሳረጊያውን ሙከራ አድርጓል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች እየተጋጋለ የነበረው ጨዋታው ኳስ እና መረብ ሳይገናኝበት በአቻ ውጤት ተፈፅሟል።

ከጨዋታው በኋላ የፋሲል ከነማው አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ በጨዋታው ለመሸናነፍ ጥሩ ትግል እንደነበረ አውስተው ግብ ጠባቂያቸው ሚኬል ሳማኪን በማድነቅ በማጥቃቱ ረገድ ያገኙትን የጎል ማግባት አጋጣሚ መጠቀም ላይ ችግር እንደነበረባቸው ገልፀዋል። የኢትዮጵያ መድኑ ምክትል አሠልጣኝ ለይኩን ታደሠ (ዶ/ር) በበኩላቸው ጨዋታውን ጥሩ ነው ካሉ በኋላ በሁለተኛው አጋማሽ ፋሲል የቅርፅ ለውጥ ካደረገ በኋላ በተለይ በማጥቃቱ ረገድ የተሻሉ እንደነበረ አመላክተው አስተያየታቸውን አገባደዋል።

\"\"