ሪፖርት | መቻል ወሳኝ ድል ተቀዳጅቷል

ላለመውረድ በሚደረገው ትንቅንቅ ብዙ ትርጉም የነበረው የወልቂጤ ከተማ እና የመቻል ጨዋታ በመቻል 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ወልቂጤ ከተማ እና መቻል ሲገናኙ ሠራተኞቹ ከፋሲል ከነማ ጋር ያለ ግብ ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ተመስገን በጅሮንድን አስወጥተው ኤፍሬም ዘካሪያስን በማስገባት ለጨዋታው ሲቀርቡ መቻሎች በአንጻሩ በባህር ዳር ከተማ 3ለ2 ከተረቱበት አሰላለፍ የስድስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ ፣ በኃይሉ ግርማ ፣ ግርማ ዲሳሳ ፣ የአብሥራ ሙሉጌታ ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ እና ምንይሉ ወንድሙ በግብ ጠባቂው ውብሸት ጭላሎ ፣ ቶማስ ስምረቱ ፣ አህመድ ረሺድ፣ ተስፋዬ አለባቸው ፣ ተሾመ በላቸው እና እስራኤል እሸቱ ተተክተው ጀምረዋል።

\"\"

ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ትልቅ ትርጉም ያለው ጨዋታ በዋና ዳኛው ዮናስ ካሳሁን ፊሽካ በተጀመረ በአንድ ደቂቃ ውስጥ መቻሎች ወርቃማ የግብ ዕድል ፈጥረው ነበር። ከነዓን ማርክነህ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል የገባው ሳሙኤል ሳሊሶ ኳሱን በትክክል ሳይመታው ቀርቶ በመነሳቱ የግብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።


በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን ለመውሰድ በሚደረጉ ፍልሚያዎች ታጅቦ በቀጠለው ጨዋታ ወልቂጤዎች 18ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ የግብ ዕድላቸውን ፈጥረዋል። በጥሩ ቅብብል የወሰዱትን ኳስ በመጨረሻም አቡበከር ሳኒ ለጌታነህ ከበደ አሾልኮለት ጌታነህ ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። በአንድ ደቂቃ ልዩነትም ከራሳቸው የግብ ክልል የተሻገረውን ኳስ የመቻሉ የመሃል ተከላካይ የአብሥራ ሙሉጌታ ሳይቆጣጠረው ቀርቶ ኳሱን ያገኘው አቤል ነጋሽ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ወጥቶበታል።

በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር እያስመለከተን በቀጠለው ጨዋታ በአጋማሹ የመጨረሻ 20 ደቂቃዎች የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል መቻሎች የበላይነቱን ወስደዋል። 28ኛው ደቂቃ ላይ ምንይሉ ወንድሙ በድንቅ ሩጫ በቀኙ የሳጥኑ ክፍል ላይ ይዞት የገባውን ኳስ ለበረከት ደስታ አመቻችቶ ሲያቀብል በረከትም ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል። ኳሱን በትክክል እንዳይጠቀምበትም የተከላካዩ ሳሙኤል አስፈሪ ጥረት ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው። በአምስት ደቂቃዎች ልዩነትም ሳሙኤል ሳሊሶ በቀኝ መስመር ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ምንተስኖት አዳነ ኳሱን በግንባሩ ሳያገኘው ቀርቶ አይጠቀምበት እንጂ ሌላኛው የግብ ዕድላቸው ነበር።


ጨዋታው 43ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግን  መቻሎች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ግርማ ዲሳሳ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ የወልቂጤዎቹ አሥራት መገርሣ እና አዲስዓለም ተስፋዬ በትክክል ሳያርቁት ቀርተው ኳሱን ያገኘው ከነዓን ማርክነህ ለምንይሉ ወንድሙ አመቻችቶ ሲያቀብል ምንይሉ በቀላሉ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ከዕረፍት መልስ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ሠራተኞቹ በሁለት አጋጣሚዎች ለጌታነህ ከበደ በተሻገሩ ኳሶች የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር። ሆኖም ብዙ የሚጠብቁበት ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪያቸው በዛሬው ጨዋታ በተከላካዮች መሸፈኑ ሳጥን ውስጥ ደካማ አድርጓቸው ተስተውሏል።

መቻሎች በጨዋታው መሪ ቢሆኑም ተጨማሪ ግብ ፍለጋ ወደ ማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ሲመለሱ 64ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ሳሙኤል ሳሊሶ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ፋሪስ አለዊ በደካማ ጊዜ አጠባበቅ ለማስወጣት ሲሞክር እሱ በእጁ የመለሰው ኳስ የመቻሉን ግሩም ሀጎስ ጀርባ ገጭቶ ግብ ሆኗል።


እየተቀዛቀዘ የሄደው ጨዋታ በመጨረሻ 10 ደቂቃዎች በድጋሚ ተነቃቅቶ ማራኪ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ተደርገውበታል። 84ኛው ደቂቃ ላይ ወልቂጤ ከተማዎች የተሻለውን የግብ ሙከራቸውን ሲያደርጉ በቀኝ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ ያገኘው ተከላካዩ ተስፋዬ መላኩ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ የግቡን የቀኝ ቋሚ ገጭቶ ተመልሶበታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ መቻሎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ተቀይሮ የገባው ዮሐንስ መንግሥቱ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ምንይሉ ወንድሙ ጥሩ ሙከራ አድርጎ የግቡ የቀኝ ቋሚ ሲመልስበት ያንኑ ኳስ በድጋሚ ሞክሮትም ግብ ጠባቂው ፋሪስ አለዊ አግዶበታል። የጨዋታው መጠናቀቂያ 95ኛው ደቂቃ ላይም እስራኤል እሸቱ ጥሩ የግብ ዕድል አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ጨዋታውም በመቻል 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም መቻል በ 37 ነጥቦች ወደ 9ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ወልቂጤ ከተማ በ 33 ነጥቦች ባለበት የወራጅ ቀጠና ቀጥሏል።

\"\"

ከጨዋታው በኋላ አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በጨዋታው በተለይ በመጀመሪያው ጎል በሰሩት ስህተት ጎል ተቆጥሮባቸው ለማስቆጠር ሲወጡ ተጨማሪ ጎል እንደተቆጠረባቸው ገልፀው ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ጠንክረው ከተጫወቱ ያለው የደረጃ መቀራረብ ቦታ መቀያየር እንደሚያስከስት አመላክተዋል። አሸናፊው አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በበኩላቸው የሚፈልጉትን ነጥብ እንዳገኙ በመግለፅ ቡድናቸው ዛሬ የተሻለ እንደነበር እና የተጋጣሚ ቡድን ወሳኝ ተጫዋች የሆነውን ጌታነህን በሚገባ እንደተቆጣጠሩ አስረድተው የዛሬው ሦስት ነጥብ እጅግ አስፈላጊ እንደነበር ተናግረዋል