ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሷል

ምሽቱን በተደረገው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና 2-1 በሆነ ውጤት መቻልን በመርታት ደረጃውን ወደ አራተኛ ከፍ አድርጓል።

በሸገር ደርቢ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናዎች ከተጠቀሙት አሰላለፍ በሦስቱ ላይ ለውጥ ማድረግ አስፈልጓቸዋል። ሮቤል ተክለሚካኤል ፣ ሬድዋን ናስር እና መስፍን ታፈሰን በገዛኸኝ ደሳለኝ ፣ ይታገሱ ታሪኩ እና ጫላ ተሺታ ሲተኳቸው ሊጉ ለብሔራዊ ቡድን ከመቋረጡ በፊት መቻሎች ወልቂጤን ሲረቱ በወቅቱ ከተጠቀሙት መካከል በኃይሉ ግርማ እና ምንይሉ ወንድሙን በዮሐንስ መንግሥቱ እና እስራኤል እሸቱ ለውጠው ለጨዋታው ቀርበዋል።

\"\"

አመሻሹን የጀመረው የሁለቱ የመዲናይቱ ክለቦች የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ጊዜ በርከት ያሉ የሜዳ ላይ ቅብብሎች በአንፃሩ ጥቂት የግብ ዕድሎች የተፈጠሩበትን ሒደት ያስተዋልንበት ነበር። የጨዋታውን የመጀመሪያ አስር ደቂቃዎች ከራስ ሜዳ በሚደረግ ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በመግባት ዕድሎችን ለመፍጠር አልመው መንቀሳቀስ የጀመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከግብ ጋር መገናኘት የቻሉት ገና ከጅምሩ ነበር። 6ኛው ደቂቃ ከቀኝ የሜዳው ክፍል ከእጅ ውርወራ ብሩክ በየነ የደረሰውን ኳስ ጥሩ የቦታ አያያዝ ላይ ይገኝ ለነበረው ጫላ ተሺታ አቀብሎ የመስመር አጥቂው ሁለት ጊዜ ብቻ ገፋ በማድረግ ወደ ጎል የመታት ኳስ ከግቡ ቋሚ ጋር ተጋግዛ ቡናን መሪ ያደረገች ግብ ሆናለች።

ግብ ካስተናገዱ በኋላ የጥቃት መነሻቸውን ወደ መስመር ዘንበል በማድረግ አልፎ አልፎ ደግሞ መሐል ሜዳውን ተጠቅመው በመጨረሻም በሚጣሉ ኳሶች ወደ ጨዋታ በጥልቀት ራሳቸውን ያስገቡት መቻሎች 15ኛው ደቂቃ ላይ ከነዓን ከበረከት ጋር ጥሩ ቅብብል አድርጎ ወደ ጎል በሞከረው እና በረከት ባወጣበት አጋጣሚ ሙከራ ማድረግን ከጀመሩ በኋላ ወደ አቻነት የተሸጋገሩበትን ጎል አግኝተዋል። 22ኛው ደቂቃ ላይ ዮሐንስ መንግሥቱ ላይ የቡና ተከላካዮች በሳጥኑ ጠርዝ ጥፋት መስራታቸውን ተከትሎ የተሰጠውን የቅጣት ምት ሳሙኤል ሳሊሶ አክርሮ በመምታት ነበር ግብ ማድረግ የቻለው። ቡድኖቹ አቻ መሆን ከቻሉ በኋላ ያሉት ቀሪዎቹ ደቂቃዎች ሜዳ ላይ ከሚደረጉ ያልተሳኩ ቅብብሎች ውጪ ሙከራን ማየት የቻልነው ከቆመ ኳስ ነበር። መቻሎች 44ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ከቅጣት መቶ በረከት በጥሩ ቅልጥፍና ካወጣት ኳስ በኋላ ጨዋታው በ1ለ1 በሆነ የአቻ ውጤት ተጋምሷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስን በራሳቸውን ቁጥጥር ስር በማድረግ ብልጫውን በመያዝ ቢንቀሳቀሱም ቡድኑ በጥሩ ቅብብል በጥልቀት የተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ በሚደርስበት ወቅት የመጨረሻ ውሳኔዎቻቸው ደካማ በመሆኑ ጥራት ያለውን የግብ ሙከራ በቀላሉ እንዳያደርጉ ሲያደርጋቸው አስተውለናል። ከመስመር የጥቃት መነሻቸውን በማድረግ ወደ ውስጥ በሚጣሉ አልያም በሽግግር ለመጫወት የሚዳዱት መቻሎች ልክ እንደ ቡና ሁሉ ያገኟቸው የነበሯቸውን ያለቀላቸውን ኳሶች ከነበረባቸው የውሳኔ ድክመት አኳያ ከጎል ጋር ለማገኘት ከብዷቸው መመልከት ችለናል። ሜዳ ላይ ተበራክተው ይታዩ ከነበሩት በርካታ ቅብብሎች ውጪ በቀላሉ በሙከራዎች ያልታጀበው ይህ አጋማሽ መቻሎች በግሩም ሀጎስ ከርቀት ካደረጋት ሙከራ መልስ ኢትዮጵያ ቡናዎች እንደነበራቸው ጥሩ የጨዋታ ብልጫ ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል።

\"\"

77ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ሰይፈ በጥሩ ዕይታ ለአማኑኤል ዮሐንስ ሰጥቶት አማካዩ በአግባቡ ያደረሰውን ኳስ ብሩክ በየነ ሳጥን ውስጥ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ዳግም ተፈራ መረብ ላይ ያሳረፋት ኳስ ነች ቡድኑን መሪ ያደረገችው በቀሩት የጨዋታ ደቂቃዎች ሜዳ ላይ ከሚንሸራሸሩ ኳሶች ውጪ ተጨማሪ ዕድሎችን በቡድኖቹ በኩል ተፈጥረው መመልከት ሳንችል ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና የ2ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች በቅዶሚያ ሽንፈት ያስተናገዱት አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በጨዋታው ብልጭ ድርግም የሚሉ እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ ጠቁመው በሚፈለገው መልኩ ኳስ መጫወት እንዳልቻሉ በማንሳት መሐል ሜዳ ላይ ተጋጣሚያቸው ብልጫ መውሰዳቸውን ከተናገሩ በኋላ በነበረው መዘናጋት የሚፈልጉትን ውጤት እንዳላገኙ ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ በበኩላቸው ጨዋታው እንደተጀመረ ተጋጣሚያቸው ጫና እንደፈጠሩባቸው ቀስ በቀስም ወደ ሪትም መምጣታቸውን ጠቁመው ስድስት ቋሚ ተጫዋቾች በተለያየ ምክንያቶች ባይኖሩም ወጣት ተጫዋቾችን ተጠቅመው ውጤቱ በመገኘቱ ትልቅ ድል ነው ሲሉ ገልፀውታል።