የሀድያ ሆሳዕና ቀጣዩ አሰልጣኝ ታውቋል

ከአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ጋር የተለያየው ሀድያ ሆሳዕና ለቀጣዩ የውድድር ዘመን አዲስ አሰልጣኝ ለመሾም ከስምምነት ደርሷል።

\"\"

የ2015 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ 43 ነጥቦችን ሰብስቦ በደረጃ ሰንጠረዡ ስድስተኛ ላይ ተቀምጦ ያጠናቀቀው ሀድያ ሆሳዕና ከአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ጋር ያለው የአንድ ዓመት የኮንትራት ዕድሜ መጠናቀቁን ተከትሎ ቀጣዩ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ መሆናቸውን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ አባተ ተስፋዬ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ አሳውቀዋል።

ያለፉትን አንድ ዓመት ከሥልጠናው ርቀው የቆዩት የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ፣ ደደቢት ፣ ድሬዳዋ ከተማ ፣ መቐለ 70 እንደርታ ፣ ወልዋሎ አዲግራት እና መቻል አሰልጣኝ በመሆን የሰሩት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ሀድያ ሆሳዕና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በ29ኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታን ባደረገበት ወቅት በስታዲየም ተገኝተው ነበር።

\"\"

አሰልጣኙ ከክለቡ ጋር በጥቅማጥቅም ጉዳዮች ዙሪያ ከተነጋገሩ በኋላ ለቀጣዩ የ2016 የውድድር ዘመን ክለቡን በዋና አሰልጣኝነት ለማሰልጠን ስምምነት ፈፅመዋል። አሰልጣኙ እና ክለቡ በይፋ ከቀናት በኋላ የውል ስምምነታቸውን ፌዴሬሽን በመገኘት እንደሚያፀድቁም ይጠበቃል።