ፋሲል ከነማ ተጫዋቾች እንዳያዘዋውር ታግዷል

ዐፄዎቹ ከስምንት ቀናት በኋላ በሚከፈተው የዝውውር መስኮት ተጫዋች እንዳያስፈርሙ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሳኔ አሳልፏል።

\"\"

ያለፉትን ዓመታት በፋሲል ከነማ ምክትል አሠልጣኝነት ግልጋሎት ሲሰጡ የነበሩት ኃይሉ ነጋሽ ዓምና ከሁለተኛው ዙር ውድድር ጀምሮ ክለቡን በጊዜያዊ ከዛም በዋና አሠልጣኝነት ሲመሩ እንደነበር ይታወሳል። ዘንድሮ አሠልጣኙ ከ12 ሳምንታት በላይ ሳያሰለጥኑ የ7ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታቸውን ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ከማድረጋቸው ከአንድ ቀን በፊት ከክለቡ እንዲለያዩ መደረጉ አይዘነጋም።

ከክለቡ የስንብት ደብዳቤ የደረሳቸው አሠልጣኙ ጉዳዩን ወደ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ወስደውት የነበረ ሲሆን ኮሚቴውም ክለቡ አሠልጣኙ ላይ ያስተላለፈውን ውሳኔ ውድቅ በማድረግ ለአሠልጣኙ ያልተከፈላቸው ደመወዝ እንዲሰጥ እና ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ አልያም እስከ ውላቸው ማብቂያ ድረስ ያላቸው ደመወዝ እንዲከፈላቸው ወስኖ ነበር። ይህ ውሳኔ አግባብ አይደለም በሚል ክለቡ ይግባኝ ቢጠይቅም ይግባኙ ውድቅ ሆኖም ነበር።

\"\"

አሁን ደግሞ በፍትህ አካል የተወሰነውን ውሳኔ ክለቡ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ተፈፃሚ ባለማድረጉ ከተጫዋቾች የዝውውር መስኮት እንደታገደ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ ገልጿል።