ሪፖርት | ሀድያ ሆሳዕና በታሪኩ ከፍተኛ ነጥብ አስመዝግቦ ዓመቱን አጠናቋል

ሀድያ ሆሳዕና በሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ በሠመረ ሀፍታይ እና ተመስገን ብርሀኑ ግቦች ኢትዮጵያ መድንን በመርታት በደረጃ ሰንጠረዡ 6ኛ ቦታን ይዞ አጠናቋል። መድንም 3ኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቁ የነሀስ ሜዳሊያውን ተረክቧል።

በአዳማ መድኖች ሽንፈት ከገጠመው ስብስባቸው ቴዎድሮስ በቀለ ፣ ሐቢብ መሐመድ ፣ አብዱልከሪም መሐመድ ፣ ወገኔ ገዛኸኝ ፣ እዮብ ገብረማርያም እና ሲሞን ፒተርን በተካልኝ ደጀኔ ፣ ፀጋሰው ድማሙ ፣ አሸብር ደረጀ ፣ ዮናስ ገረመው ፣ ያሬድ ዳርዛ እና ዳግም ሠለሞንን ሲተኩ በተመሳሳይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተሽንፈው በነበሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች በኩል ሔኖክ አርፊጮ ፣ ዳግም በቀለ ፣ ተመስገን ብርሀኑ ፣ ግርማ በቀለ እና ፀጋዬ ብርሀኑን በቃልአብ ውብሸት ፣ ፍሬዘር ካሳ ፣ እያሱ ፈጠነ ፣ እንዳለ አባይነህ እና ሠመረ ሀፍታይ ለውጠው ለጨዋታው ቀርበዋል።

\"\"

ጨዋታውን በቁጥጥራቸው ስር በማድረግ በይበልጥ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ፈጠን ባሉ እንቅስቃሴዎች ለመድረስ ገና ከጅምሩ ያልተቸገሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች ግብ ማስቆጠር የቻሉት ገና 7ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ከእጅ የተጣለን ኳስ ባዬ ገዛኸኝ ከቀኝ ወደ ግብ መሬት ለመሬት ሲያሻግር ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ ለማውጣት ሲዳዳ ከፊቱ የነበረው ሠመረ ሀፍታይ ተደርቦ ኳሷ መረብ ላይ አርፋለች። በብዙ ረገድ ብልጫን ወስደው በጥልቀት ሲጫወቱ የተስተዋሉት ሀድያ ሆሳዕናዎች በድግግሞሽ የመድንን የግብ ክልል ማንኳኳት ቢችሉም የግብ ጠባቂው አቡበከር ብቃት ተጨማሪ ጎሎች እንዳይቆጠሩ በትጋት ሲመክት መመልከት ችለናል። በተደረጉ ሙከራዎች12ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ሁለት ቅብብል ያገኛትን ኳስ ብሩክ ማርቆስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ አቡበከር ሲመልሳት በድጋሚ ባዬ ለሠመረ ሰጥቶ ተጫዋቹ ሳይረጋጋ ያመከናት የቡድኑ አደገኛ ሙከራዎቻቸው ናቸው።


ወደ ጨዋታ ለመመለስ በእጅጉ መቸገራቸውን ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ልናስተውል የቻልንባቸው መድኖች አብዛኛውን የጥቃት መነሻቸውን ከመስመር አድርገው ለመጫወት ቢጥሩም በቀላሉ የተጋጣሚን አጥር ሰብረው ለመግባት ተፈትነዋል። ቡድኑ ካደረው ሙከራ መካከል 20ኛው ደቂቃ ዳግም ከቀኝ ምቹ ቦታ ለነበረው አሸብር ሰጥቶት ተጫዋቹ በፍጥነት ወደ ውስጥ ሲያሻግር ብሩክ ሙለጌታ አግኝቶ የነበረ ቢሆንም ፔፔ አድኖበታል። ሀድያ ሆሳዕናዎች በቀሩት የጨዋታ ደቂቃዎች አከታትለው አጋጣሚዎችን ፈጥረዋል። ብርሀኑ በቀለ በጥሩ መንገድ የደረሰውን አክርሮ መቶ አቡበከር የመለሰበትን እንዲሁም ከተመሳሳይ ርቀት ባዬ እና ሠመረ ራቅ ካሉ ቦታዎች በጨዋታ መንገድ ያገኙትን ኳስ አክርረው መተው በዕለቱ ድንቅ የነበረው አቡበከር ኑራ ካዳናቸው በኋላ ባሉ ደቂቃዎች ግቦችን ሳያስተናግድ አጋማሹ በሀድያ መሪነት ተገባዷል።


ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ መድኖች በመጀመሪያው አጋማሽ ይታይባቸው የነበረውን ድክመት ለማስተካከል ያለመ ቅያሪን አድርገው ወደ ሜዳ ተመልሰዋል። ዳግም ሠለሞን እና አሚር ሙደሲርን በወገኔ ገዛኸኝ እና ሳይመን ፒተርን መተካት ከቻሉ በኋላ ቡድኑ ኳስን በመቆጣጠር ከተጋጣሚው ሻል ቢልም ሙከራዎች በማድረጉ ረገድ ግን በሽግግር ሲጫወቱ የታዩት ሀድያ ሆሳዕናዎች የተሻለ ነበሩ። ጨዋታው 55ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ የመድኑ ተከላካይ ፀጋሰው ድማሙ ብርሀኑ በቀለ ላይ በሳጥን ውስጥ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የዕለቱ ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ የሰጡትን የፍፁም ቅጣት ምት ባዬ ሲመታው አቡበከር መትፋቱን ተከትሎ በድጋሚ ሠመረ የማግባት ቢያገኝም አቡበከር ዳግም መልሷት ጨዋታው ቀጥሏል።


በሙከራ ያልደመቁት ቀጣዮቹ ደቂቃዎች መድኖች ተጨማሪ የተጫዋች ለውጥን አድርገው ጎል ፍለጋ ላይ በይበልጥ ቢሰማሩም ጥራት ያላቸው ዕድሎችን ግን ማግኘት አልቻሉም። ከተደረጉ ሙከራዎች መካከል 77ኛው ደቂቃ ላይ ወገኔ ገዛኸኝ ወደ ውስጥ ኳስን ይዞ ገብቶ የመታውን ቃልአብ ሳይቸገር ያወጣበት የቡድኑ ቀዳሚ ሙከራ ሆናለች። ኳስን ሲያገኙ በሚጣሉ ተሻጋሪ ኳሶች በቀላሉ የመድንን መከላከል የሚፈትኑት ሀድያዎች 85ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ጎልን አግኝተዋል። ካሌብ በየነ ከራስ ሜዳ በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ ዘካሪያስ ፍቅሬ በግንባር ገጭቶ ያመቻቸለትን ተመስገን ብርሀኑ የግብ ጠባቂው አቡበከርን አቅጣጫ አስቶ ከግራ አቅጣጫ መረብ ላይ ያሳረፋት ኳስ ነች የጎል መጠኑን ከፍ ያደረገችው ጨዋታው በመጨረሻም በሀድያ ሆሳዕና 2ለ0 ተጠናቋል። ድሉንም ተከትሎ ሀድያ በታሪኩ ትልቅ ነጥብን ሰብስቦ ዓመቱን ቆጭቷል።

\"\"

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የመድኑ ረዳት አሰልጣኝ ለይኩን ታደሰ ጨዋታው በተለይ የመጀመሪያ አጋማሽ ጥሩ የሚባል አይደለም ካሉ በኋላ ነገር ግን በጨዋታው ወደ ሜዳ የገቡ አዳዲስ ተጫዋቾች ተሽለው ማየት በመቻላቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው ዓመቱም የተሳካ እንደነበር በንግግራቸው ጠቁመዋል። በመቀጠል የሀድያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በዋና አሰልጣኝነት በፕሪምየር ሊጉ ላይ የመጀመሪያቸው ቢሆንም የተሰጣቸውን ሀላፊነት መቶ ፐርሰንት እንዳሳኩ ጠቁመው በዛሬውም ጨዋታ ቡድናቸው ጥሩ እንደነበር እና ያሰቡትም መሳካት መቻሉን በንግግራቸው ገልፀዋል።

ከጨዋታው በኋላ በሊጉ 3ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ኢትዮጵያ መድን የነሀስ ሜዳሊያውን ተረክቧል።

\"\"