ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | ካፋ ቡና መውረዱ ሲረጋገጥ የካ እና ኦሜድላ አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 23ኛ ሳምንት የምድብ ለ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ተካሂደው የካ እና ኦሜድላ ወሳኝ ድል ሲያስመዘግቡ ካፋ ቡና ወደ አንደኛ ሊግ መውረዱ የተረጋገጠ የመጀመርያ ቡድን ሆኗል።

በእለቱ የመጀመርያ ጨዋታ የካ ክ/ከተማን ከ ሸገር ከተማ አገናኝቶ የካ 3-2 አሸንፏል። የካዎች ጨዋታው በተጀመረ በ16ኛው ደቂቃ ቀዳሚ መሆን የቻሉ ሲሆን በአንድ ሁለት ቅብብል ወደፊት ሲያመሩ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ቅጣት ምት ክብሮም ፅዱቅ ተሻምቶ አንተነህ ተሻገር በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ አድርጓል። ከጎሉ በኋላ በሁለቱም በኩል የጠራ የጎል እድል ሳንመለከት ወደ እረፍት አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ ሸገሮች የመጀመርያዎቹ 25 ደቂቃዎችን የአቻነት ጎል ፍለጋ ተጭነው መጫወት የቻሉ ሲሆን 69ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው ሀይከን ደዋሙ ከሳጥን ውስጥ ተጨራርፋ የደረሰችውን ኳስ አስቆጥሮ አቻ አድርጓል።

ከአቻ በኋላ ጥሩ የተንቀሳቀሱት የካዎች በ76ኛው ደቂቃ በድጋሚ መሪ መሆን የቻሉ ሲሆን ካሳሁን ሰቦቃ ከመስመር የተሻገለረለትን ኳስ በአግባቡ ተጠቅሞ አስቆጥሯል። ሆኖም መሪነታቸው የቆየው ለሁለት ደቂቃ ብቻ ሲሆን በፍጥነት ምላሽ የሰጡት ሸገሮች ባደረጉት የማጥቃት እንቅስቃሴ ከመስመር የተመቻቸለትን ኳስ ሳዲቅ ሴቾ አስቆጥሮ አቻ አድርጓል።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የካዎች አሸናፊ ሆነው ለመውጣት ጥረት ሲያደርጉ በጭማሪ ደቂቃ ላይ በሳጥን ውስጥ አንተነህ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣህ ምት ታከለ ታንቶ አስቆጥሮ በየካ 3-2 አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።

በሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ኦሜድላ ካፋ ቡናን አሸንፎ ከወራጅ ቀጠናው ፈቀቅ ሲል ካፋ ቡና በአንፃሩ ወራጅነቱ ተረጋግጧል።

በጨዋታው ጅማሬ ኦሜድላዎች የበላይነት በማሳየት ጫና ለማሳደር ጥረት ያደረጉ ሲሆን ጥረታቸውን በጎል ያሳመሩትም ገና በጊዜ ነበር። 14ኛው ደቂቃ ላይ ጌታቸው አርትሮ ያሻገረውን በረከት በቀለ ገጭቶ አስቆጥሮ ቡድኑን ቀዳሚ ሲያደርግ ከሦሰት ደቂቃ በኋላ ደግሞ ሰይፈ ዛኪር ከሳጥን ውጪ መትቶ በማስቆጠር መሪነታቸውን አስፍቷል።

በካፋ በኩል በአጋማሹ ተዳክመው የታዩ ሲሆን ይድነቃቸው ውበት ከሞከረው ውጪ ብዙም ወደ ግብ ሳይጠጉ አጋማሹ ተጠናቋል።

የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ በተመለከትንበት ሁለተኛው አጋማሽ ጎል ከመቆጠሩ ውጪ ብዙም ሙከራ ያልታየበት ሲሆን 72ኛው ሰይፈ ዛኪር የተሻገረለትን ኳስ ሲገጭ ግብ ጠባቂውን አልፋ ጌታቸው አርትሮ አግኝቶ በግንባሩ በመግጨት የማሳረጊያዋን ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በኦሜድላ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።