ሪፖርት | ዐፄዎቹ ከ 5 ጨዋታዎች በኋላ ድል አድርገዋል

ፋሲል ከነማ ከመመራት ተነስቶ በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠራቸው ግቦች ሀዲያ ሆሳዕናን 2ለ1 አሸንፏል።

በምሽቱ መርሐግብር ሀዲያ ሆሳዕና እና ፋሲል ከነማ ተገናኝተው ነብሮቹ በ22ኛው ሳምንት ከባህር ዳር ከተማ ጋር 0-0 ሲለያዩ ከተጠቀሙበት አሰላለፍ ባደረጉት የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ በየነ ባንጃ እና ኡመድ ኡክሪን አስወጥተው እንዳለ ዓባይነህ እና ተመስገን ብርሃኑን ሲያስገቡ ዐፄዎቹ በአንጻሩ ከአዳማ ከተማ ጋር 0-0 ከተለያዩበት አሰላለፍ ባደረጉት የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ መናፍ ዐዎል እና ዮናታን ፍስሃን አስወጥተው አምሳሉ ጥላሁን እና ፍቃዱ ዓለሙን አስገብተዋል።

12፡00 ሲል በዋና ዳኛ ዳንኤል ይታገሱ ፊሽካ በተጀመረው ጨዋታ ፋሲል ከነማዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ ጥሩ አጀማመር ሲያደርጉ 4ኛው ደቂቃ ላይም የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርገዋል። ሆኖም ፍቃዱ ዓለሙ ያደረገውን ሙከራ የኳሱ ኃይል የለሽነት ተጨምሮበት ግብ ጠባቂው ታፔ አልዛየር ይዞበታል።

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው መጫወትን የመረጡት ሀዲያዎች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው በመመለስ 31ኛው ደቂቃ ላይ በአጋማሹ የተሻለውን የግብ ዕድል ፈጥረው ዳዋ ሆቴሳ እና አስጨናቂ ጸጋዬ ያደረጓቸው ሙከራዎች በተከላካዮች ከተመለሱ በኋላ ኳሱን ያገኘው ብሩክ ማርቆስ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ዮሃንስ ደርሶ መልሶበታል።

የግብ ዕድሎች ብዙም ባልተፈጠሩበት ጨዋታ ነብሮቹ 38ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ኢዮብ ማቲያስ ለጃቢር ሙሉ ለማቀበል ሲሞክር በስህተት ለዳዋ ሆቴሳ አቃብሎት ዳዋም ያገኘውን ኳስ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ መሬት ለመሬት በመምታት በግሩም አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ከዕረፍት መልስ ቃልኪዳን ዘላለምን አስወጥተው አቤል እንዳለን በማስገባት ጨዋታውን የጀመሩት ፋሲል ከነማዎች የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ለማደራጀት ጥረት ቢያደርጉም ዳዋ ሆቴሳ እና ጌታነህ ከበደ ከረጅም ርቀት ካደረጓቸው ሙከራዎች ውጪ ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች አልተደረገም ነበር።

ይበልጥ እየተቀዛቀዘ የሄደውን ጨዋታ ዐፄዎቹ 65ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረው ነፍስ ዘርተውበታል። ሽመክት ጉግሳ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ከአንድ ንክኪ በኋላ ያገኘው ጃቢር ሙሉ ኳሱን በተረጋጋ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

አቻ ከሆኑ በኋላ ሁለቱም ቡድኖች ግለታቸውን በመጨመር ብርቱ ፉክክር ማድረግ ሲችሉ ፋሲል ከነማዎች 79ኛው ደቂቃ ላይ ከተመሪነት ወደ መሪነት የተሸጋገሩበትን ጎል አግኝተዋል። ሽመክት ጉግሳ በግራ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ጋቶች ፓኖም በግንባሩ ከጨረፈው በኋላ ኳሱን ያገኘው ምኞት ደበበ አስቆጥሮታል።

ግቦችን ካስተናገዱ በኋላ በየነ ባንጃ ፣ ኡመድ ኡክሪ እና ሰመረ ሀፍተይን ቀይረው ያስገቡት ነብሮቹ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቶ ጨዋታው በፋሲል ከነማ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በመጀመሪያው አጋማሽ እንደፈለጉት እንደተጫወቱ ጠቁመው በትኩረት ማጣት ምክንያት እንደተሸነፉ በመናገር በሁለተኛው አጋማሽ የጠበቁትን እንቅስቃሴ በቡድናቸው ላይ እንዳልተመለከቱ ሀሳባቸውን ሲሰጡ የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እንዳልነበሩ እና ያንንም በሁለተኛው አጋማሽ እንዳሻሻሉት በመናገር ያደረጉት የተጫዋች ቅያሪ እና የቦታ ሽግሽግ ውጤታማ እንዳደረጋቸው በመጠቆም የጃቢር ሙሉን እንቅስቃሴ እንደሚያበረታቱት በመግለጽ ያገኙት ድል የትንሣኤውን በዓል ከድብርት ነጻ ሆነው እንዲያከብሩ እንደሚያደርጋቸው ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።