ሪፖርት | የጣና ሞገዶች አስደናቂውን የውድድር ዓመታቸው በድል አገባደዋል

ባህርዳር ከተማ ወላይታ ድቻን አንድ ለባዶ በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን የብር ሜዳሊያ በመረከብ አጠናቋል።

ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ በርካታ የተጫዋቾች ለውጥ አድርገው በጀመሩት ጨዋታ በርካታ የግብ ሙከራዎች ያስመለከተ ነበር። በፈጣን እንቅስቃሴዎች ታጅቦ የጀመረው ይህ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ብልጫ ለመውሰድ ጥረት ያደረጉት የጦና ንቦች የተሻለ በተንቀሳቀሱባቸው ደቂቃዎች ሁለት ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገዋል። ስንታየሁ መንግስቱ በረጅሙ የተሻገረለትን ኳስ አመቻችቶ ለመሳይ ኒኮ አቀብሎት አማካዩ ከርቀት ያደረጋት ሙከራ እና አበባየሁ ከመስመር ሰብሮ ገብቶ መቷት ይገርማል መኳንንት የመለሳት ኳስም ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

\"\"

በአጋማሹ የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ የተሻሉ የነበሩት የጣና ሞገዶቹ አደም አባስ በተሰለፈበት የግራ መስመር አማካኝነት በርካታ የግብ ዕድሎች ፈጥረዋል። ከነዚህም ሳላአምላክ ከመስመር ያሻገረው ኳስ አደም አባስ አግኝቶ መቶት ቢንያም ገነቱ የመለሰበት ሙከራ እና አደም ከመስመር አሻማቷት ፍቅረሚካኤል በግንባሩ ገጭቶ የሞከራት ኳስ ለግብ የቀረበች ነበረች። የጣና ሞገዶቹ ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውጭም የአብስራ ተስፋዬ ከቅጣት ምት አሻምቷት ፍቅረሚካኤል በግንባሩ ባደረጋት ሙከራ ግብ ለማግኘት ጥረት አድርገዋል።


በአርባ አራተኛው ደቂቃም በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው አደም አባስ ግብ አስቆጥሯል። ተጫዋቹ የአብስራ ከመአዘን ያሻማውን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችላል። ከግቡ በኋላም ወላይታ ድቻዎች በጥሩ ቅብብል ወደ ግብ ደርሰው በዘላለም አባቴ አማካኝነት አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ተጫዋቹ ኬኔዲ በጥሩ መንገድ ያመቻቸለትን ኳስ ቢመታውም ቋሚው መልሶበታል።


ከዕረፍት መልስ የአቀራረብ ለውጥ አድርገው ተጭነው ለመጫወት የሞከሩት ወላይታ ድቻዎች በአጋማሹ ሙሉ ብልጫ መውሰድ ችለዋል፤ በሁለት አጋጣሚዎችም አቻ ለመሆን ለቃርበው ነበር። በተለይም መሳይ ኒኮል አክርሮ መቷት ተከላካዮች ተረባርበው ያወጧት ኳስ ቡድኑን አቻ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች። አበባየሁ ሀጅሶ ያደረጋቸው ሙከራዎችም ሌሎች የሚጠቀሱ ናቸው። በተለይም ከመአዘን የተሻማውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባሩ ያደረገው ሙከራ እና ከርቀት አክርሮ መቶት የግቡን አግዳሚ የመለሰበት ኳስ እጅግ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

በሁለተኛው አጋማሽ የተጋጣሚን የማጥቃት እንቅስቃሴ ከመግታት ውጭ የተቀዛቀዘ የማጥቃት እንቅስቃሴ የነበራቸው ባህርዳር ከተማዎችም የተወሰኑ ሙከራዎች አድርገዋል። ከነዚህም ሀብታሙ ታደሰ ከመአዘን የተሻገረውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳል።


ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አስተያየታቸው የሰጡት የባህርዳር ከተማ አሰልጣኝ ደግአረግ በጨዋታው ያሰለፏቸው ወጣት ተጫዋቾች ያሳዩት እንቅስቃሴ እንዳስደሰታቸው ገልፀው ከውድድር ዓመቱ ብዙ ልምድ እንደቀሰሙ ተናግረዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም ቀጣይ በአፍሪካ ውድድር የሚሳተፈው ቡድናቸው በአጭር ጊዜ አጠናክረው እንደሚቀርቡ እና በውድድሩም የተሻለ ርቀት ለመሄድ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

\"\"

ቀጥለው ሃሳባቸው የሰጡት የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ጨዋታው ጥሩ እንደነበር ገልፀው የውድድር ዓመቱ ብዙ እንደተማሩበት ገልፀዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም \”በአቅማችን ልክ ክለቡን ተፎካካሪ ለማድረግ ሞክረናል ውድድሩም ጥሩ ነበር\” ብለዋል።

ከጨዋታው በኋላ 2ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ባህር ዳር ከተማ የብር ሜዳሊያ ተረክቧል።