ጎንደር አራዳ የክልል ክለቦች ሻምፒዮና አሸናፊ ሆኗል

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት ወደ 2016 የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ውድድር ለማደግ ከሰኔ 14 ጀምሮ በሀዋሳ ከተማ ሲደረግ የነበረው የክልል ክለቦች ሻምፒዮና በጎንደር አራዳ የበላይነት በዛሬው ዕለት ተጠናቋል።

\"\"
በሀገሪቱ የእግር ኳስ የበላይ አካል በሆነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት የሚደረገው የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና በዛሬው ዕለት ፍፃሜውን አግኝቷል። ከሰኔ 14 ጀምሮ በስምንት ምድቦች ተከፍሎ በ31 ክለቦች መካከል ወደ አንደኛ ሊግ የሚያድጉ ክለቦችን ለመለየት በሀዋሳ ከተማ ሲከናወን የሰነበተው ይህ ውድድር በዛሬው ዕለት በተደረጉ የደረጃ እና የፍጻሜ ጨዋታዎች ነው የተጠናቀቀው።

\"\"

7 ሰዓት ሲል በተደረገው የደረጃ ጨዋታ ሱሉልታ ቢ ከመታፈሪያ ክፍሌ ኮንስትራክሽን ጋር ያደረጉት ጨዋታ መደበኛው የጨዋታ ደቂቃ ያለ ግብ መጠናቀቁን ተከትሎ በተሰጠው የመለያ ምት የኦሮሚያው ተወካይ ሱሉልታ ቢ 4ለ2 በማሸነፍ ሦስተኛ ደረጃ ወጥቶ የነሃስ ተሸላሚ ሆኗል።

\"\"

በመቀጠል 9 ሰዓት ላይ ሁለቱን የአማራ ክልል ክለቦች ያገናኘው የደምበጫ ከተማ እና እና ጎንደር አራዳ ክፍለከተማ ጨዋታ በጎንደር አራዳ የ2ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል። ለጎንደር አራዳ ሁለቱን የማሸነፊያ ግቦች ሸጋው ሲሳይ በጨዋታ አቤል ብርሀኑ ደግሞ በፍጹም ቅጣት ምት ግቦችን ሲያስቆጥሩ የደምበጫን ብቸኛ ጎል ክብረት ካሳሁን በራሱ ላይ ማስቆጠር ችሏል።

 

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የተለያዩ የሽልማት ስነ ስርዓቶቾ  ሲሄዱ በሽልማት አሰጣጥ ስነ ስርዓቱ ላይ ዶ/ር ዳኛቸው ንግሩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ፣ አቶ ባህሩ ጥላሁን የፌዴሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፣ አቶ ሸረፋ ደለቾ የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ፣ አቶ ክፍሌ ዋሬ የሀዋሳ ከተማ ስፖርት ኮሚሽነር እንዲሁም የሲዳማ እግር ኳስ ፌድሬሽን ም/ል ፕሬዝዳንት አቶ ማርቆስ ኤልያስ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ሽልማቶቹን አበርክተዋል። አስቀድሞ ለውድድሩ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት እና ተቋማት የምስክር ወረቀት የተበረከተ ሲሆን ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ላጠናቀቀው ሱሉልታ ቢ የነሃስ ፣ ሁለተኛ ያጠናቀቀው ደምበጫ ከተማ የብር እና ቻምፒዮኑ ጎንደር አራዳ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸልመዋል። በመጨረሻም ለአዘጋጁ ሲዳማ ክልል የዋንጫ ፣ ጎንደር አራዳ የፀባይ እና የውድድሩን ሁለት ዋንጫዎች ካነሳ በኋላ ውድድሩ ፍፃሜውን አግኝቷል።

\"\"

በዚህም ጎንደር አራዳ ፣ ደምበጫ ከተማ ፣ ሱሉልታ ቢ እና መታፈሪያ ክፍሌ በ2016 የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ላይ ተሳታፊ መሆናቸው የታወቁ አራቱ ቡድኖች ሆነዋል።
\"\"

በሴቶች ደግሞ አምቦ ጎል ፕሮጀክት እና ደብረማርቆስ ከተማ ወደ ሴቶች ከፍተኛ ሊግ ያደጉ ቡድኖች ናቸው።