እስማኤል ኦሮ አጎሮ የሞሮኮውን ክለብ ተቀላቀለ

ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተከታታይ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ያሳካው ቶጓዊው አጥቂ የሞሮኮውን ክለብ መቀላቀሉን ወኪሉ ለሶከር ኢትዮጵያ አሳውቋል።
\"\"
ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ መጥተው ስኬታማ መሆን ከቻሉ ጥቂት የውጪ ዜግነት ካላቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ የ28 ዓመቱ ቶጓዊ አጥቂ እስማኤል ኦሮ አጎሮ ይጠቀሳል። ባሳለፍነው ዓመት ክረምት ወር መጨረሻ የሀገሩን ክለብ ኤ ኤስ ሲ ካራን በመልቀቅ ቅዱስ ጊዮርጊስን በሁለት ዓመት የውል ኮንትራት በመቀላቀል ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ጋር የተገናኘው ተጫዋቹ በሁለት የውድድር ዓመታት ለክለቡ ወሳኝ ግቦችን ከማስቆጠር በዘለለ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ በተከታታይ ማሳካት ችሏል።
\"\"
የ2015 የፕሪምየር ሊግ ቆይታውን ከፈረሰኞቹ ጋር የሊግ ክብርን ከማሳካት በተጨማሪ በ25 ግቦች ከፍተኛ ግብ አግቢ በመሆን ዓመቱን ያጠናቀቀው ቶጓዊው አጥቂ 64 ዓመትን ያስቆጠረውን እና በያዝነውም ዓመት የሞሮኮው ቦቶላ ፕሮ ሊግን ዋንጫ በማንሳት ያጠናቀቀውን የሰራዊት ክለብ ኤፍ ኤ አር ራባት በሦስት ዓመት ውል መቀላቀሉን የተጫዋቹ ወኪል ለሶከር ኢትዮጵያ በላከው መረጃ አመላክቷል።