ሀዲያ ሆሳዕና ከጎፈሬ ጋር ያለውን ውል ለተጨማሪ ዓመት አድሷል

​\”በዋናነት የክለባችንን የፋይናንስ ችግር ለመቅረፍ ስንል ከጎፈሬ ጋር ስምምነት እየፈጸምን እንገኛለን።\” አቶ አባተ ተስፋዬ (የክለቡ ሥራ አስኪያጅ)

\”ብዙ ሕዝብ ከሚደግፈው ክለብ ጋር በጋራ በመሥራታችን ትልቅ ኩራት ይሰማናል።\” አቶ ሳሙኤል መኮንን (የጎፈሬ መስራች እና ባለቤት)

ላለፉት ሁለት ዓመታት የጎፈሬን ምርት ሲጠቀሙ የነበሩት ነብሮቹ ከትጥቅ አምራቹ ጋር ያላቸውን ውል ለቀጣይ ሁለት ዓመታት አድሰዋል።

ዛሬ ከሰዓት በሆሳዕና ከተማ ስፖርት ሆቴል በተካሄደው ታላቅ የፊርማ ሥነ-ስርዓት ላይ በጎፈሬ በኩል የተቋሙ መስራች እና ባለቤት አቶ ሳሙኤል መኮንን፣ ምክትል ሥራ-አስኪያጁ አቶ አቤል ወንድወሰን እንዲሁም የማርኬቲንግ ዳይሬክተሩ አቶ ፍፁም ክንድሼ ሲገኙ በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ደግሞ ሥራ አስኪያጁ አቶ አባተ ተስፋዬ እንዲሁም የቦርድ አባል የሆኑት እና የሀዲያ ዞን የገቢዎች ጽ/ቤት መምሪያ ኃላፊ አቶ መሳይ ተስፋዬ፣ የሰላም እና ፀጥታ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ እና የደጋፊዎች ማኅበር አመራሮች ተገኝተዋል።


በስምምነቱ ወቅት በቅድሚያ ንግግር ያደረጉት የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ አባተ ተስፋዬ \”የዛሬ ፕሮግራማችን ከጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ አምራች ድርጅት ጋር ስምምነት ለመፈጸም ነው። በዋናነት የክለባችንን የገንዘብ አቅም በደንብ ለማጠናከር ነው።\” ብለው የስምምነቱን ዓላማ በመጠቆም ከዚህ በፊት በነበረው ሂደት ክለቡ በመንግስት በጀት ብቻ የሚደገፍ እንደነበር እና ከዛ በዘለለ ክለቡን ሕዝባዊ መሠረት ለማስያዝ የግድ እንዲህ ዓይነት ስምምነቶችን በመፈጸም የክለቡን አቅም ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸው በመግለጽ \”ዛሬ የመጀመሪያ ስምምነት የምንፈጽመው ከጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ አምራች ጋር ነው። ይህንንም ደግሞ ስፖንሰር ሲያደርጉልን በዋናነት የሚሰጡንን የማልያ ድጋፎች ስናሰላ ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ያደርጉልናል። ይሄ ብቻም ሳይሆን የደጋፊውን ፣ የክለቡን እና የስፖርተኛውን ፍላጎት ለማሟላት የታሰበ ነው። ከዕቅዳችን አንዱ ይህ ሲሆን በሌላ በኩል የማልያ ግዢ እና ሽያጭ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ስፖንሰሮችን ከጎፈሬ ጋር ተስማምተን ውድድሮችን ስፖንሰር የማድረግ እና ሌሎች ጥቅማጥቅሞችንም ለማግኘት የተጠናከረ ሥራ እንሠራለን ብለን አቅደን ይዘን እየሠራን እንገኛለን።\” ብለዋል።

አቶ አባተ አክለውም \”ወደፊት በተጠናከረ መልኩ ፕሮጀክቱን እያሰፋን የምንሄድ ነው የሚሆነው በዋናነት የክለባችንን የፋይናንስ ችግር ለመቅረፍ ስንል ከጎፈሬ ጋር ስምምነት እየፈጸምን እንገኛለን። በሂደት ደግሞ የተሻሉ ሥራዎችን እየሠራን እንሄዳለን። ከዚህ ጋር ተያይዞ የክለቡን የፋይናንስ አቅም ለማጠናከር በዋናነት ከስፖንሰሮች ጋር የጋራ ስምምነት የምናደርግ ነው የሚሆነው።\” በማለት ሀሳባቸውን አገባደዋል።

የትጥቅ አምራቹ ጎፈሬ መስራች እና ባለቤት አቶ ሳሙኤል መኮንን በበኩላቸው \”ዛሬ የተገኘንበት ትልቅ ዓላማ ከሀዲያ ሆሳዕና ስፖርት ክለብ ጋር የስፖንሰርሺፕ እና አብሮ በጋራ የመሥራት ስምምነት ለመፈራረም ነው።\” ብለው የዕለቱን ጉዳይ በመጠቆም \”እንደሚታወቀው ጎፈሬ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ይፋዊ ብራንድ ሲሆን ወደ 15 ከሚሆኑ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቡድኖች ጋር የሚሠራ ነው። ተጨማሪ ደግሞ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ከዚህ በፊት ለሁለት ዓመታት አብረን ሠርተናል። ይህም የማጠናከሪያ እና ቀጣዮችን ሁለት እና ሦስት ዓመታት አብረን የምንሠራበት ነው። በጎፈሬ በኩል ከዚህ ትልቅ ክለብ ጋር ብዙ ሕዝብ ከሚደግፈው ክለብ ጋር በጋራ በመሥራታችን ትልቅ ኩራት ይሰማናል። በጎፈሬ ወደፊት ብዙ ትላልቅ ያልተሠሩ ሥራዎችን ለመሥራት ሠፊ ዕቅድ ይዘናል። ከዚህም ውጪ በደቡብ አፍሪካም ይሁን በተለያዩ ሀገሮች የሚገኙ የሀዲያ ሆሳዕና ደጋፊዎች ያላቸውን አስተዋጽኦ ከፍ የሚያደርግ ገቢ በማሰባሰብም ይሁን ቡድኑን ወስዶ ከማጫወትም እዚህም ደግሞ የሀዲያ ሆሳዕና ደጋፊ የናፈቀውን ቡድን ሆሳዕና ላይ በዚህ ዓመት በቅድመ ውድድር ዝግጅት ላይ ህዝቡ እንዲያይ እናደርጋለን\” በማለት ከውጪ አንድ ቡድን ጋብዘው ይህንን ጨዋታ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል። በመጨረሻም ስለተሰጣቸው ዕድል በማመስገን የፊርማ ስነስርዓቱ ተከናውኗል።