የዋልያዎቹን የአሜሪካ ጉዞ በተመለከተ መግለጫ ተሰጥቷል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሳምንቱ መጨረሻ ለወዳጅነት ጨዋታዎች ወደ አሜሪካ የሚያደርገውን ጉዞ በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

በጊዜያዊ አሠልጣኙ ኢንስትራክተር ዳንኤል ገብረማርያም የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ አሜሪካ ለጉብኝት ጨዋታዎች እንደሚያመራ ይታወቃል። ብሔራዊ ቡድኑ ከእሁድ ጀምሮ መቀመጫውን አዳማ ላይ በማድረግ እየተዘጋጀ የሚገኝ ሲሆን በሁለት ዙር ነገ እና ከነገ በስትያ ወደ ስፍራው ለማቅናት እየተሰናዳ ይገኛል። የጉዞውን ሂደት እና የዝግጅት ጊዜውን በተመለከተ ዛሬ ከሰዓት በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

ጋዜጣዊ መግለጫውን ለመስጠት የፌዴሬሽኑ ዋና ሥራ-አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ፣ የቡድኑ አሠልጣኝ ኢንስትራክተር ዳንኤል እንዲሁም ጉዞውን ያሰናዳው ተቋም ወክለው አቶ ዳዊት ተገኝተዋል። በቅድሚያ ሀሳባቸውን የሰጡት የቡድኑ አሠልጣኝ ከሐምሌ 13 ጀምሮ 22 ተጫዋቾችን ይዘው ልምምዳቸውን በጥሩ ሁኔታ ሲሰሩ እንደነበር ጠቁመው ይህ ታሪካዊ አጋጣሚ ስለሆነ እንዲሁም በበርካታ መልማዮች ዕይታ ውስጥ ሊገቡ የሚችሉበት ዕድል ስላለ በሙሉ ትኩረት ጨዋታውን እንዲያደርጉ ከተጫዋቾቹ ጋር እንደተመካከሩ አስረድተዋል።
\"\"
በማስከተል አቶ ዳዊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ከዚህ ቀደም ከፊፋ፣ ካፍ ወይም ሴካፋ ጨዋታዎች ውጪ እንደዚህ አይነት የጉዞ የወዳጅነት ጨዋታዎችን አድርጎ እንደማያውቅ በመጥቀስ በሌላው ሀገር ግን እግርኳሱ ከመዝናኛነቱ በተጨማሪ ቢዝነስ እንደሆነ ጠቅሰው የሀገራቸው ቡድን እንደዚህ አይነት ጨዋታ ለማድረግ በመቻሉ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል። አያይዘውም ተጫዋቾች በዚህ የጉዞ የወዳጅነት ጨዋታዎች በሌሎች መልማዮች የሚታዩበት ዕድል እንዳለ አንስተው ለአብነትም በሜጀር ሊግ ሶከር የሚሳተፉት የዲሲ ዩናይትድ እና አትላንታ ዩናይትድ መልማዮች የብሔራዊ ቡድኑን ስም ዝርዝር ቀድመው እንደጠየቁ ይፋ አድርገዋል። በንግግራቸው መሐልም በጉዞ ታላላቅ ስፖንሰሮችን የማምጣት ሀሳብ ቢኖርም በቪዛ መዘግየት እና በተለያዩ ምክንያቶች ይህ እንዳልሆነ አመላክተው ድርጅታቸው ምናልባት የገቢ ማጣት ሊያጋጥመው እንደሚችል ተናግረዋል። በ2026 ኢትዮጵያ ወደ ዓለም ዋንጫው የምታልፍ ከሆነም ቡድኑ በድጋሚ ወደ አሜሪካ እንደሚያቀና ተናግረዋል።

በቀጣይ መድረኩን የተረከቡት አቶ ባህሩ እንደ ፌዴሬሽን ይህ የጉዞ ዕቅድ በመሳካቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው የጉዞው ፋይዳ ያሉዋቸውን ሦስት ዓበይት ሀሳቦች በስፍራው ለተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ተናግረዋል። በዚህም አንደኛው የስፖርታዊ ጥቅም ሲሆን ሁለተኛው የማርኬቲንግ ጥቅም እንዲሁም ሦስተኛው ብሔራዊ ቡድኑን አሜሪካ ካለው ማኅበረሰብ ጋር ማገናኘት እንደሆነ ጠቅሰዋል። የጉዞ ጉዳይንም በተመለከተ የቪዛ ፕሮሰሱ ረጅም ጊዜ እንደወሰደ በዝርዝር አስረድተው በዚህ ጉዞ የሚሄዱት በሞሮኮ በተደረገው የጊኒ ጨዋታ የተሳተፉ ተጫዋቾች እንደሆኑ ተናግረዋል። በቡድኑ የአሜሪካ ቆይታ እንደነ ጃማይካ ከመሳሰሉ ቡድኖች ጋር ጨዋታ እንዲያደርግ ቀድሞ ቢታቀድም በተለያዩ ምክንያቶች እንዳልተሳኩ አመላክተዋል።
\"\"
ከጉያና ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚደረገው ጨዋታ በፊፋ የተመዘገበ እንደሆነና በጥሪው የተካተቱት አራት ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች በሁለተኛው የአትላንያ ሮቨርስ ጨዋታ እንደሚሳተፉ ገልፀው ወደ አሜሪካ አጠቃላይ 37 የልዑካን ቡድን እንደሚያመራ ተናግረዋል። በዚህም ጉዞውን ያሰናዳው ተቋም የ32 አባላትን ወጪ ሲሸፍን የሌሎች 5 አካላት ወጪ በፌዴሬሽኑ እንደሚሸፈን ጠቅሰዋል። በንግግራቸው ማብቂያም ፌዴሬሽኑ ቤይ ማርት ከተባለ ተቋም ጋር ስምምነት ፈፅመው ማሊያዎችን እንዲሁም የተለያዩ ቁሳቁሶችን በቦታው በመሸጥ የማርኬቲንግ ገቢ ለማግኘት እንዳሰቡ ተናግረዋል።

ብሔራዊ ቡድኑ የአሜሪካ ቆይታውን እስከ ነሀሴ 2 አጠናቆ ወደ ሀገር ቤት እንደሚመለስ ሲገለፅ በዲሲ እና አትላንታ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንም ትኬቶችን እንዲገዙ ጥሪ ቀርቧል።