መከላከያ 0-0 አርባምንጭ – ታክቲካዊ ትንታኔ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር-ሊግ 3ኛ ሳምንት

እሁድ ጥቅምት 30 2007 ዓ.ም 9፡00 – አዲስ አባባ ስታዲየም

መከላከያ 0-0 አርባምንጭ

ታክቲካዊ ትንታኔ – በሚልክያስ አበራ

በአርባምንጭ ደጋፊዎች ደማቅ ህብረ ዝማሬ በተጀመረው የእሁዱ 9 ሰአት የአዲስ አባባ ስታዲየም 3ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየርሊግመርሀግብር ጨዋታ ከደቡብ ክልል የመጣው ቡድን 4-4-2 ዳይመንድን (4-1-2-1-2) ከጨዋታው መነሻ ጀምሮ ለመተግበር የሞከረ ሲሆንእንግዳውን ቡድን ተቀብሎ በሜዳው ያስተናገደው የሸገሩ መከላከያ ደግሞ ጠባቡን 4-4-2 በሙሉ የጨዋታው ክፍለ ግዜ ተጫውቷል፡፡

የቡድኖቹ የመጀመሪያ ቋሚ አሰላለፍ የሚከተለውን ቅርፅ የያዘ ነበር፡፡ (ምስል 1)

Mekelakeya 0-0 AMK (1)

ቡድኖቹ ፎርሜሽኑን የተገበሩበት መንገድ

አርባምንጭ – 4-4-2 ዳይመንድ

ዳይመንድ 4-4-2 ፎርሜሽን ብዙውን ግዜ ለተጋጣሚ ቡድን የሚሰጠው width እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ በብዛት ቡድኖች ይህንን የፎርሜሽን ክፍተት ለመቅረፍ በሁለቱ የኋላ መሽመር ፉልባኮቻቸው ላይ width የመሸፈን ሐላፊነትን እንዲወጡ ያደርጋሉ፡፡ በዚህም ዘዴ በተጋጣሚ ቡድን ሜዳ ላይ ፉልባኮች ከአማካዮች ጋር ብዙ የመቀባበያ አማራጮችን ለመፍጠር ይችላሉ፡፡ ሆላንዳዊው የታክቲክ አዋቂ አሰልጣኝ ሉዊስ ቫንጋልም ዳይመንድን ‹‹Mathematicaly ingeneious ›› ብለው ይጠሩታል ( በተጫዋቾች መካከል ብዙ ትሪያንግሎችን እና በርካታ የመቀባበያ መስመሮችን ያስገኛል የሚል እምነት አላቸው፡፡) በተጨማሬም የዳይመንድ ፎርሜሽን በሜዳው የመሀለኛው ክፍል የማጥቃት አጨዋወት ላይ አይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡

የፎርሜሽኑ ትልቁ ችግር ተደርጎ የሚቆጠረው ኳስ ከራስ ቡድን ቁጥጥር ውጪ ስትሆን ለሚፈጠረው የተጋጣሚ ቡድን የ counter attacking አጨዋወት በቀላሉ ተጋላጭ ማድረጉ ነው፡፡

ፎርሜሽኑን የሚጠቀሙ ቡድኖች ከማጥቃት ወደ መከላከል የሚያደርጉት ሽግግር ላይ ቶሎ የመከላከል ቅርፃቸውን የመያዝ ችግር ይስተዋልባቸዋል፡፡

ፎርሜሽኑ በአብዛኛው Ball-oriented shift (ኳስን ያማከለ የእንቅስቃሴ እና የአቅጣጫ ለውጥን) ስለሚጠይቅ ተደጋጋሚ የሚና መወሳሰብን ይፈጥራል፡፡ ለምሳሌ ተጋጣሚ ቡድን በግራ በኩል ቢያጠቃ ከቀኝ መስመር ያለው አማካይ የተከላካይ አማካይ እና በሚድፊልድ ጫፍ ያለው የአጥቂ አማካይ ተጫዋቾች የመከላከል ሚናቸውን እንዲወጡ እና የግራ መስመር አማካይ በመልሶ ማጥቃት ተሳታፊ እንዲሆን የሚያስችለውን ቦታ እንዲይዝ ይመከራል፡፡ ይህ በአንድ የጨዋታ moment የሚፈጠር የሚና መቀያየር ነው፡፡ ሁለቱ የፊት ለፊት መስመር ተሰላፊዎች ወይም አጥቂዎች ከማጥቃት በተጨማሪ የመከላከል ሚናቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ ታዋቂው ሆላንዳዊ አሰልጣኝ ዮሃን ክሩፍ ‹‹ የኔ ዳይመንድ ›› በሚለው ሲስተም አጥቂዎቹ ከማጥቃት ሚናቸው በተጨማሪ የተጋጣሚን ፉለባኮች stifle በማድረግ (አፍኖ በመያዝ) የሚጫወቱት ሚና ቀላል እንዳልሆነ ይተነተናል፡፡

በዚህኛው ጨዋታ ግን መሰረታዊውን የፎርሜሽኑ ጥቅም የአርባምንጭን ቡድን ሲጠቀምበት ለማስተዋል አለታደልንም፡፡ ለዚያውም ተጋጣሚው ቡድን (4-4-2) ጠባቡን ተጠቅሞ፡፡ በሁለቱም መስመሮች ላይ የተሰጠውን ሰፊ ቦታ ለመጠቀም የተደረገን ጥረት መመልከት አልተቻለም፡፡ በእርግጥ በቡድኑ ከታዩት ተጫዋቾች 26 ቁጥሩ የተጋጣሚ ቡድን የመስመር ተከላካዮች ትተውት የሚሄዱትን ክፍተት ለመጠቀም ያደረገውን ጥረት ክሬዲት ልንሰጠው ይገባል፡፡ 22ኛው ደቂቃ ላይ ያደረጋት የጎል ሙከራም የዚህ ጥረቱ ማሳያ ነበረች፡፡ከኋላ ያለውን የተከላካይ መስመር ተሰላፊ በማገዝም ሆነ ወደ መሃል ሜዳው በመግባት ቡድኑ የመሃል ሜዳ የበላይነት እንዲኖረው ለማድረግ የተጫወተው ሚና ሳይጠቀስ ማለፍ አይኖርበትም፡፡ ነገር ግን ተጫዋቹ የተጠና እንቅስቃሴ እና ብልሃት የተከላበት ውሳኔዎች ላይ የበለጠ መስራት ይኖርበታል፡፡

ተጫዋቹ የቡድኑን የማጥቃትም ሆነ የመከላከል ተግባር በሚዛናዊነት ሲወጣ መታየቱ ሊያስመሰግነው ይገባል፡፡ የአርባምንጭ አጥቂዎች በጎነዮሽ በአንድ መስመር ላይ ሲሆኑ ከኋላቸው በመገኘት የማጥቃት አማራጮችን ፈጥራል፡፡

በቡድኑ የዳይመንዱ የኋለኛው ጫፍ ላይ የተሰለፈው 20 ቁጥሩ (አምበሉ ሙሉአለም መስፍን) ለተከላካዮቹ እጅግ ቀርቦ ነበር የተጫወተው፡፡ በእርግጥ ይህን ማድረጉ ለሁለቱ የመሃል ተከላካዮች ሽፋን ለመስጠት ይመስላል፡፡ የመስመር ተከላካዮቹ ወደ ፊት ተጠግተው በማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ የነበራቸው ተሳትፎ አናሳ መሆኑ ቡድኑ በ5 ተከላካይ እየተጫወተ የነበረ አስመስሎታል (የተከላካይ አማካዩ በጥልቀት ወደ ኋላ ተስቦ ነበር፡፡) ይህም ሆኖ የላይኛው የዳይመንዱ ጫፍ ላይ የተሰለፈው ተጫዋች ወደ ኋላ የበለጠ እየቀረበ ዳይመንዱ ሲጠብ ተመልክተነዋል፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ በተጋጣሚያቸው መከላከያ ቡድን የአጥቂዎችና የአማካዮችን ርቀት የበለጠ እንዲሰፋ አድርጓል፡፡ በዚህም ምክንያት አርባምንጭ የመሃል ሜዳ መጠነኛ በላይነት አሳይቷል፡፡ ይህም ቡድኑ ተደጋጋሚ የጎል ሙከራዎችን እንዲያገኝ ረድቶታል፡፡

መከላከያ ጠባብ 4-4-2

ይህ ፎርሜሽን በሜዳው የጎንዮሽ ክፍል በጥልቀት ወደ መስመሩ ተጠግተው የሚጫወቱትን wide midfielders በብዛት ሲያሳትፍ አይታይም፡፡ ፉልባኮቹ በዚህኛውም ሲስተም የጎንዮሽ ጨዋታ ሚናቸው የተሻለ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ የፎርሜሽኑ በጎ ጎን በመሃል ሜዳ በተጋጣሚ ቡድን የቁጥር ብልጫን መቀነስ ማስቻሉ ነው፡፡

መከላከያ በጨዋታው ባብዛኛው በመስመሮች በኩል ለማጥቃት (በፉልባኮቻቸው አማካኝነት) ሲጥር ውሏል፡፡ በተለይ የቀኝ መስመር ተከላካዩ 2 ቁጥር (ሽመልስ ተገኝ) ግዜውን የጠበቀ overlapping ሲያደርግ ተመልክተነዋል፡፡ በዚህ ግዜ ከእርሱ ቅርብ ላይ ያለው የመሃል ተከላካይ የሱን ቦታ በመሸፈን ድርብ ሚና ሲወጣ ነበር፡፡ ይህ የቡድኑን የመከላከል ቅርጽ የመጠበቅ ተግባር ላይ ጥሩ እንደነበሩ አመላካች ነው፡፡ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ከስህተት የፀዳ የመከላከል ስዓርት ነበራቸው ማለት አይቻልም፡፡ ተከላካዮች አልፎ አልፎ መጠነኛ የመናበብ ችግርም ሲስተዋልባቸውም ታይተዋል፡፡ በእርግጥ ለሁለቱ የመሓል ተከላካዮች ጥሩ መሆን የሁለቱ የተከላካይ አማካዮች እገዛ ከፍተኛ ነበር፡፡ ፉለባኮች ለማጥቃት የላይኛው ሜዳ ላይ ሲገኙ በጎንዮሽ ያለውን ሰፊ ክፍተት ለመድፈን ጥሩ ሲንቀሳቀሱ ተስተውለዋል፡፡ ነገር ግን የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ የነበራቸው ተሳተፎ እጅግ አናሳ ነበር፡፡ በተጋጣሚያቸው የመሃል ሜዳ የበላይነትም ሲወሰድባቸውም ተስተወለዋል፡፡ የመስመር አማካዮችም ተጋጣሚ ቡድን የሰጣቸውን ሰፊ ክፍተት ከመተቀምና ለቡደናቸው width ለማስገኘት ከመጣር ይልቅ ወደ መሃል ሜዳው በመግባት ኳስ ለማግኘት ሲንከራተቱ ነው ያመሹት፡፡ (ምስል2)

የመከላከያ ሁለቱ inverted wingers

ሁለቱም የመከላከያ የመስመር አማካዮች inverted wingers ነበሩ፡፡ ሚናው በዘመናዊው ዘግር ኳስ የቀኝ እግር ተጫዋችን በግራ የሜዳው አማካይ መስመር ፤ የግራ እግር ተጫዋችን ደግሞ በቀኝ የሜዳው አማካይ መስመር እንዲጫወቱ የሚጠይቅ ነው፡፡ አሰልጣኞች ብዙውን ጊዜ ሲስተሙን የሚጠቀሙት በ traditional wingers የሚገኘውን width ለመጠቀም ወይም ከመስመር ወደ ተጋጣሚ ቡድን የጎል ክልል የሚላኩ ኳሶችን በማሰብ ብቻ ሳይሆን ተጫዋቾቹ በተደጋጋሚ ወደ መሃለኛው ሜዳ ሰብረው እየገቡ (cut-inside) ለቡድን አጋሮቻቸው የመጫወቻ ክፍተትን እንዲፈጥሩ ነው፡፡

መከላከለያ በጨዋታው አጥቂዎቹ ከሁለቱ ተከላካይ አማካዮች ተነጥለውበት ታይተዋል፡፡ሁለቱ የመስመር አማካዮች ወደ መሃል እየገቡ link (በአጥቂዎችና በአማካዮች መካከል) ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡ ተጋጣሚያቸው ከሰጣቸው ሰፊ የመስመር የመጫወቻ ቦታ አንፃር ተጫዋቾቹ በተፈጥሯዊው ቦታቸው ቢሰለፉ የተሻለ ሊነቀሳቀሱ ይችሉ ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡

Mekelakeya 0-0 AMK (2)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *