ድሬዳዋ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅት የሚጀምርበት ቀን ታውቋል

በአሰልጣኝ አስራት አባተ የሚመራው ድሬዳዋ ከተማ በሀሮማያ ዩኒቨርስቲ ዝግጅት የሚጀምርበት ቀን ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ያለፉትን ተከታታይ የውድድር ዘመናት ከወገብ በላይ ከፍ ብሎ ሊጉን ለማጠናቀቅ ሲቸገሩ ከምንመለከታቸው ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ድሬዳዋ ከተማ ለቀጣዩ የውድድር ዓመት በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት በአሰልጣኝ አስራት አባተ መሪነት ተመስገን ደረሰ ፣ ሔኖክ አንጃው ፣ ቴዎድሮስ ሀሙ ፣ ኤፍሬም አሻሞ ፣ ዳግማዊ አባይ ፣ ሀምዲ ቶፊክ እና ካርሎስ ዳምጠውን የስብስባቸው አካል ያደረጉ ሲሆን ለ2016 የፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎአቸው ተጨማሪ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ዜጋ ተጫዋቾችን ከማስፈረማቸው አስቀድሞ የቅድመ ውድድር ዝግጅት የሚጀምሩበትን ቀን ዝግጅት ክፍላችን አውቋል።

ከፊታችን ረቡዕ ነሀሴ 10 ጀምሮ የክለቡ አባላት በድሬዳዋ ከተማ ከተሰባሰቡ በኋላ በማግስቱ ነሀሴ 11 ዕለተ ሐሙስ በሀሮማያ ዩኒቨርስቲ ቅጥር ጊቢ ውስጥ ዝግጅታቸውን በይፋ እንደሚጀምሩ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።